(መነሻ ሃሳብ በደግፌ ጃክሰን)
ነጠላ ያስረዘሙ ፈሪሳዊ ሰልፈኞች ከመጻሕፍቱ ጀርባ በኦርቶዶክሳዊ አቋቋም አደግድገው ቆመዋል። ከድንኳኑ ውጨኛው ክፍል "5ኛው የማኅበረ ቅዱሳን የመጻሕፍት ኤግዚቢሽን"የሚል ጽሑፍ በጉልህ ተጽፎ ተሰቅሏል። ሰይጣንም፣ ክፉውም፣ ጠማማውም፣ ነፍሰ ገዳዩም፣ ወንበዴውም፣ ሟርተኛውም ሰው "ቅዱስ ነኝ"ቢል በዚህ ዘመን የሚጠይቀው ስለሌለ (አሁን ጥያቄ የለም ማለት እስከመጨረሻው ጥያቄ የለም ማለት አይደለም) በቅድስና ማኅበር ስም የተጻፈውን ማስታወቂያ ካነበብኩ በኋላ ስለቅድስናው የሚመሰክር ፍንጭ ፍለጋ ወደድንኳኑ ጎራ አልኩ። እዚህ ላይ አንባቢን ላስገነዝብ የምፈልገው ነገር እኛ ለራሳችን የምንሰጠው ስም ሳይሆን የምንሰራው ሥራ ነው የዋጋችንን ሚዛን ሊወስን የሚችለው። ጠንቋይ ቤት የሚካኤልና የማርያም ስዕል ተሰቅሎ መገኘቱ ወይም የገብርኤልን ዝክር እንድትደግስ በማለት ባለሀድራው በማጓራቱ ጠንቅ ዋይነቱን ወደቅድስና ማዕረግ አይለውጠውም።
ወደፍሬ ነገሩ ስመለስ፣ ከቅዱሳኑ ማኅበር ድንኳን ጎራ ብዬ የእግዚአብሔርን ቅድስና የሚያውጁ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን መድኃኒትነት የሚናገሩ፣ ዓይን ሁሉ ወደቀራንዮ እንዲመለከት የሚያሳስቡ መጻሕፍት ፍለጋ አማተርኩ። ጠላታችሁ ይፈር፣ አንድም መጽሐፍ በማጣቴ አፈርኩ። ይልቁንም እልክ የተጋቡ በሚመስል መልኩ ከዚህ በተቃራኒ የሰዎችን እይታ ከቀራንዮ በማስኮብለል ወዳልሆነ ቦታ የሚነዱ፣ ክርስቶስን በሰዎች ማንነትና ትልቅነት የሚጋርዱ ሆነው አገኘኋቸው። ካየሁት የመጻሕፍት ዐውደ ርእይ የተረዳሁት ነገር የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት፣ ብቸኛ አዳኝነት፣ መንገድና ሕይወትነት ከመስበክ ይልቅ ቅጠልም፣ አፈርም፣ ዳቦም፣ ንፍሮም፣ ጠላም፣ ቅራሪም፣ አተላም፣ ተራራ ለተራራ መዞርም ሳማ ሰንበትም፣ አርሴማም፣ የግሼኗ ማርያምም፣ ኩክየለሽ ማርያምም፣ ግንድ አንሳውም፣ ሺህፈጁም፣ ጭሱም፣ ጠበሉም፣አመዱም፣የባህር ዛፍ ቅጠሉም፣ ጥንጁቱም፣ ቅርንፉድ መታጠንም፣ ቅማልና አይጥ ስእለት ማድረስም ገነት፣ መንግሥተ ሰማያት ሰተት አድርገው ያስገባሉ ትባላለህ። በቃ ያስገባሉ ከተባልክ አሜን ብለህ መቀበል ነው። የኢየሱስስ ማዳን ምን ሊሆን ነው? ብሎ መጠየቅ፣ ማጉረምረም አይቻልም። መናፍቅ፣ ተሀድሶ፣ ጴንጤ ገለመሌ ካልሆንክ በስተቀር በክርስቶስ ላይ ተጨማሪ ልዩ ልዩ ተስፋዎች ሲቀርቡልህ አልቀበልም ማለት አትችልም። "መንፈስን ሁሉ አትመኑ፣ ነገር ግን መንፈስ ከእውነት እንደሆኑመርምሩ" የሚለውን ትምህርት ከማንበብ ውጪ ወደተግባር መለወጥ ክህደት ነው። ይህንን በመቃወም ፉከራው የገፋው ሰይጣን፣ አሹልኮ ያስገባቸውና በዘመናት ሂደት ጠፍተውና ቁጥራቸው ተመናምኖ የቆዩ መጻሕፍትን ይኼ ቅዱስ ነኝ የሚለው ማኅበር በባትሪ ፈልጎ በማሰባሰብ አራብቶና አባዝቶ አገልግሎቱን ማጠናከሩን በአግራሞት ተመለከትኩ። ሰይጣን በዚህ አገልግሎት ከመቼውም በላይ ደስተኛ ሳይሆን አይቀርም። ማንነቱን መርምረው እንዳያውቁ በዘመቻ እየደፈቀ፣ ክህደቱን ለማግነን የሰራባቸው እንደዚህ የሰራባቸው ዘመናት አልታዩም። ኢየሱስ ክርስቶስ የንፍሮ ውሃ የጠጣልህን እስከ ዐሥር ትውልድ እምርልሃለሁ የሚል ቃል በ33 ዘመነ መዋዕለ ሥጋዌው ለማንም አላስተማረም። ይልቁንም ሌላ የመዳኛ መንገድ እንደሌለ አስረግጦ መናገሩን እናውቃለን።
ዮሐንስ 14፣6
"ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም"
ማኅበረ ቅዱሳን ግን የለም፣ ወደአብ መግባት የሚቻልባቸውንና ሰዎች በቀላሉ ከፈፀሟቸው የሚድኑባቸው ልዩ ልዩ ብልሀቶች አሉኝ የሚሉ መጻሕፍትን በአደባባይ ይሸጣል። በዚያ ኤግዚብሽን ላይ ከተደረደሩት መጻሕፍት መካከል “ወናሁ ትመውት በሕማመ ብድብድ እኩይ ሞት፣ ወእሬሲ ለከ ኪያሃ ከመ ስቅለትየ ወከመ ደመ ሰማዕት እለ እምቅድሜከ አኮ ለባሕቲትከ አላ ደቂቅከኒ እለ ይወውቱ በሕማመ ብድብድ በውስተ ዛቲ ገዳም እኌልቆሙ ምስለ ሰማዕታት ወአወፍዮሙ ለከ መንግሥተ ሰማያት”
ትርጉም፦ “እነሆ በክፉ ሞት በተቅማጥ ትሞታለህ፣ እሷንም እንደ ስቅለቴና ከአንተ በፊት እንደነበሩት ሰማዕታት ደም እቆጥርልሃለሁ ነገር ግን ለብቻህ አይደለም በዚች ገዳም በተቅማጥ በሽታ የሚሞቱትን ልጆችህንም ቁጥራቸውን ከሰማዕታት ጋራ አደርጋለሁ፣ መንግሥተ ሰማያትንም እሰጣቸዋለሁ” የሚለው ገድለ ተክለ ሃይማኖትን ገለጥ አድርጌ እንደገዢ ሰው አየሁት። ስድስት ክንፍ እንደተተከለለት የተቆረጠ እግር አለፍ ብሎ ወድቆ በስዕል ይታይ ነበር።
አቡነ አረጋዊ በዘንዶ ሲንሸራሸሩ፣ ለማርያም ድግስ የተቆላ አሻሮ የሸተተው ገነት እንደገባ፣ የሴት ብልት ስሞ ማርያም አፈወርቅ እንዳለችው የሚያትት፣ እግዚአብሔርን ክዶ በማርያም እንደዳነ የሚተርክ፣ ሰይጣን መነኮሰ፣ 30 ትውልድ ተማረ፣ ሎጥን ያዳነችው ማርያም ናት፣ መርቆሬዎስ ፀሐይና ፈረቃን ፈጠረ፣ ገብርኤልና ሚካኤል ሠለስቱ ደቂቅን አዳኑ፣ ሲኦልን የሞሉት ጋላና ሻንቅላ፣ የአርሴማ ድንግል ድንጋይ መካን አስወለደ፣ የአድዋን ጦርነት ጊዮርጊስ አሸነፈ ወዘተ ወጎችን የሚጠርቁ መጻሕፍት እንደጉድ ሲቸበቸቡ ተመለከትኩ። የሆኖስ ሆኖ ጊዮርጊስ አድዋ ላይ ከተዋጋ ጀግኖች አርበኞች ምን ሰሩ ሊባል ነው? የሞቱትና የቆሰሉት ምን ሲያደርጉ ኖሯል? ነው ወይስ መቁሰልና መሞት አልነበረም?
"የጉድ አገር ገንፎ እያደር ይፋጃል" እንዲሉ ሰዎቹ ጊዮርጊስ ባይኖር ጣልያንን ባላሸነፍንም ነበር ይሉናል። ኢህአዴግ ደርግን ያሸነፈው ማንን ይዞ ይሆን?
ማኅበሩ እያራባ ከሚሸጣቸው መጻሕፍት አብዛኛዎቹ ወንጌልን የሚቃወሙ፣ ባዶ ተስፋ የሚሰጡ፣ ሰው ከወንጌል ይልቅ እነዚያን እንዲያነብ የሚገፋፉ፣ የክርስቶስ ኢየሱስን የማዳን ሥራ አስትተው በትርኪ ምርኪ ቃል ኪዳን ላይ እንዲታመኑ የሚያበረታቱ መጻሕፍት ብቻ ድንኳኑን ሞልተው አይቻለሁ። ታዲያ ይህንን የስሁታንን ሥራ የሚሸጠው ማኅበር ራሱን "የቅዱሳን" ሲል ያሞካሸዋል።
ሰይጣን አስርጾ ያስገባቸውና በዘመናት ብዛት ተቀዳደውና ተመናምነው የሚያባዛለት አጥቶ በደነገጠበትና ተስፋ በቆረጠበት ሰዓት ማኅበሩ ድንገት ደርሶ እንደታደገው ማረዳት አይከብድም። ሊወገዙ የሚገባቸው የባዶ ተስፋ መጻሕፍትን ከወንጌል በላይ አሳትሞ ማሰራጨት ከቶ ምን ይባላል?
ከኤግዚቢሽኑ መጻሕፍት እንዲህ የሚል ቃል ያለበት መጽሐፍም ነበር።
«ወሶቤሃ አውስአ ወይቤላ ንስኢ ወሐብኩኪ ዐሥራተ ብዙኀ ነፍሳተ መጠነ ነጠብጣብ ዝናም ዘ፬ቱ አውራኅ ለእለ አሐዱ ዕለት»
ትርጉም «ጌታም እንዲህ አላት። በዐራት ወራት ውስጥ በየቀኑ የሚወርደውን የዝናም ነጠብጣብ ያህል ነፍሳትን ዐሥራት አድርጌ ሰጥቼሻለሁ» ገድለ ክርስቶስ ሰምራ
በዓለም ላይ በየቀኑ የሚዘንበውን የአራት ወራት ያህል የዝናብ ነጠብጣብ ውሃ ያህል ሰው ከአዳም ጀምሮ አልተፈጠረም። ገድሉ የተፈጠረውንም፣ ያልተፈጠረውንም ክርስቶስ ሰምራ ታድን ዘንድ ቃል ተገብቶላታል ይለናል። በዚህ ቃል መሠረት ኦርቶዶክስ በክርስቶስ ሰምራ በኩል የዓለሙ ሁሉ መድኃኒት ናት ማለት ነው።
በሮሜ 10፣3 እንደተመለከተው
"የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውንም ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ፥ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም" የሚለው ቃል ከሚፈፀም በቀር እንኳን ለዓለሙ አዳኝ ልትሆን ቀርቶ ራሷም ከቆመችበት የአበው አስተምህሮ ተንሸራታ ተስፋ በሌለው ተረታ ተረት ተሸፍናለች። ማኅበሩ የመጋረጃውን አገልግሎት በማስፋት ሰዎችን ወደጥፋት እንዳይነዳ እንደሄሜዎስና እስክንድሮስ ለሰይጣን ተላልፎ የተሰጠ ይሁን! ብኩርናውን ለጥቅም፣ ትጋቱን ለስሁት አገልግሎት፣ ሐዋርያትም ከሰበኩት ስብከት የተለየውን የሰበከ የተረገመ ይሁን! አሜን።