Friday, February 20, 2015

«ኃጢአት፤ ይቅርታና ተሐድሶ»

አንዳንድ የዋህ የሆኑ ሰዎች የልበ ደንዳኖችን አሳብ ተከትለው ወይም እልከኞቹ የዋሃንን እየነዱ «ቤተ ክርስቲያን አትታደስም» ሲሉ ይደመጣሉ። እነዚህን ሰዎች ስለኃጢአት፤ ንስሐ፤ ይቅርታና ተሐድሶ በማስተማር የሕይወትን መንገድ ማስረዳት ከባድ ነው። ምክንያቱም መነሻቸው እውነትን ላለመቀበል እልክ የገባ መንፈስና የተዘጋ ልብ ስላላቸው እያዳመጡ አይሰሙም። እግዚአብሔርን ከማንም በተሻለ እንደሚያውቁ ይናገራሉ። ነገር ግን እግዚአብሔር ካዘዘው ትዕዛዝ ውስጥ አንዱንም አይሰሩም። ምክንያቱም ሁል ጊዜ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር የሚያስተያዩትና የሚመዝኑስለሆነ እውነትን ወደማወቅ ሊደርሱ አይችሉም። በራሳቸው እውቀት ያለልክ ይመካሉ። ነገር ግን እውነት በማደግ ካልተገለጸ በስተቀር በራሱ በተመካ እውቀት ሊሰፋና ወደሌሎች ሊደርስ ባለመቻሉ ዕለት ዕለት ያሽቆለቁላሉ። እድሜአቸውንና ብዙኅነታቸውን እንደእውነት ምስክር አድርገው ለራሳቸው ያቀርባሉ። ራስን ከራስ ጋር የማስተያየት በሽታ አደገኛ ነው። በዚህ ድርጊት አይሁዳውያን በብዙ ተበድለዋል።አይሁዳውያን የእምነት መሠረቶች እንደነበሩ ግልጽ ነው። ነገር ግን ሕግና መጻሕፍት ይዘው መቆየታቸው በራሱ ወደእውነት አላደረሳቸውም። ምክንያቱም ራሳቸውን ይለኩ የነበረው ከራሳቸው ጋር ነበርና ነው።  በምድረ በዳ ውስጥም የ40 ቀን መንገድ 40 ዓመት ያዞራቸው ያ እልከኛ ልባቸው ነበር። በዚያ ብቻ ሳያበቃ እልከኛ ልባቸው ወደእረፍቱ እንዳይገቡ ከለከላቸው።
«ዛሬ ድምጹን ብትሰሙት፥ በማስመረር እንደሆነ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ። ሰምተው ያስመረሩት እነማን ነበሩ? በሙሴ ተመርተው ከግብጽ የወጡ ሁሉ አይደሉምን? አርባ አመትም የተቆጣባቸው እነማን ነበሩ? ሬሳቸው በምድረ በዳ የወደቀ፥ ኃጢአትን ያደረጉት እነርሱ አይደሉምን? ካልታዘዙትም በቀር ወደ እረፍቱ እንዳይገቡ የማለባቸው እነማን ነበሩ?» ዕብ3፤15-18
ራስን ከራስ ጋር ባለመመዘንና ራስን ከራስ ጋር ባለማስተያየት ችግር ካልተያዙ ዛሬ ያለውን የእግዚአብሔር ድምጽ ለመስማት ካለመፈለግ እልከኝነት ነጻ መሆን ይቻላል። የአባቶች አምላክ መንፈስ ቅዱስ ዛሬም ስለሚናገር «በየት በኩል አልፎ ወደእናንተ ደረሰ?» ከሚል እልከኝነት መውጣት እስካልተቻለ ድረስ ወዳዘጋጀው እረፍት መግባት ከባድ ነው። በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን እንደተናገረው «እምነት እያደገ፤ ወደሌላው ሰውና ሀገር ሁሉ በሥራው እየጨመረ ካልሄደ በእግዚአብሔር ላይ ያለው መመካትና ምሥጋና ፈተናውን የተወጣ አይደለም ይለናል። ምክንያቱም ራሱን ከራሱ ጋር የሚያስተያይ ራሱን የሚያመሰግን ከመሆኑ የተነሳ ነው። 2ኛ ቆሮ 10፤12-18
እልከኝነትና ደንዳናነት ከኃጢአተኝነት ነጻ ነኝ ከሚል ስሜት የሚመጣ ነው። እልከኝነት የልብን አሳብ ትቶ እውነት የሆነውን ነገር ለመስማት ፈቃደኛ አለመሆን ነው። ደንዳናነት ደግሞ እንደብረት የጠነከረ ግትርነትና ከማንአህሎኝ ድፍንነት የሚነሳ ነው። እልከኛ በኃጢአቱ ከሚመጣ ቅጣት ይማራል። ደንዳና ግን ሳይሰበር ከኃጢአቱ መማር አይችልም ።  የደነደነ ልብ የተሸከመው ፈርዖን በፊቱ የተደረጉትን ተአምራት አይቶ ከመማር ይልቅ ቀይ ባህር ውስጥ ሰጥሞ እስኪቀር መመለስ እንዳልቻለው ማለት ነው። ሁለቱም በደል የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደሆነ በሚነገርለት በእስራኤል ላይ ታይቷል። ወደዚህ ያደረሳቸው ነገር ኃጢአት ነው። በእልከኝነታቸው ተቀጥተውበታል፤ በደንዳናነታቸውም ተሰብረውበታል።  ኃጢአትን መተው ፤ ንስሐ ማድረግን፤ ይቅርታን መጠየቅና በተሐድሶ አዲስ ሰው የመሆን ስጦታን ያለመቀበል ውጤት ምንጊዜም በእልከኝነትና በደንዳናነት ውስጥ ይጥላል። ከዚያም የዘሩትን የኃጢአት ፍሬ በፍርድ ማጨዳቸው ደግሞ አይቀሬ ነው። ለዚህም ነው በዚህ ጽሁፋችን መታደስን ስለሚጸየፉ ሰዎች ጥቂት ማለትን የወደድነው። መታደስን መጥላት ኃጢአትን የመውደድ ውጤት እንደሆነ ቅዱስ መጽሐፋችንን ዋቢ አድርገን እንገልጣለን።

1/ ኃጢአት

ሥጋ ከለበሰ ከአዳም ልጆች ውስጥ ከክርስቶስ በቀር ከኃጢአት ነጻ መሆን የተቻለው ማንም የለም። ኃጢአት በአንዱ በአዳም በደል ወደሁሉ ደርሷል። ከሰማይ ወረደው ሁለተኛው አዳም የኃጢአትን በደል በመስቀል ላይ ጠርቆ ካስወገደው በኋላ በውርስ ወደሁሉ ይደርስ የነበረው ኃጢአት ተወግዷል። ከእንግዲህ በወል በኃጢአት ቀንበር ሥር መውደቅ ቀርቶልናል።  በክርስቶስ አዲስ ሰው የሆነ ማንም ቢሆን ኃጢአትን እንዳያደርግም ተነግሯል። ነገር ግን ሰው በክርስቶስ አምኖ ከዳነ በኋላ ከሥጋ ድካም የተነሳ ኃጢአትን ቢያደርግ ከኃጢአቱ እንዴት ሊነጻ ይችላል? ኃጢአት በተፈጥሮው ተጠያቂነት አለበት። ኃጢአት የፈጸመ ማንም ቢኖር ዋጋ ሳይከፍል መንጻት አይችልም። በመጽሐፉም ስለኃጢአት ደም ሳይፈስ ስርየት የለም እንደተባለ ለዚህ የምናቀርበው ዋጋ ምንድነው? እኛ ምንም የለንም።ነገር ግን ኃጢአትን አንድ ጊዜ በመስቀሉ ላይ በደሙ የደመሰሰ ክርስቶስ ለእኛ ከኃጢአት የምንድንበት ዋስትናና ጠበቃችን ነው። 1ኛ ዮሐ 2፤1

ጥብቅና ሲባል የክርስቶስን አምላክነት አሳንሶ እንደምድራዊ ችሎት ሙግትና ክርክር የሚገባ የሚመስላቸው ሞኞች አሉ። በቅድሚያ ኃጢአት በተፈጥሮው  ተጠያቂነትን ማስከተሉን ማመን የግድ ይለናል። በዚህም የተነሳ በኃጢአቱ ማንም በእግዚአብሔር ዘንድ ሳይጠየቅ የሚቀር የለም።  ደም ሳይፈስ ስርየት ስለሌለ በክርስቶስ አምነን ለተመጠቅን ሁሉ በኃጢአት ምክንያት ለሚመጣ ተጠያቂነት መልስ መስጠት የቻለ የክርስቶስ ደም ብቻ ነው። ሰዎች ኃጢአት ስለሚያመጣው ጥያቄ መልስ መስጠት ስለማንችል ስለእኛ ምትክ ሆኖ በቤዛነቱ ደም ያዳነን በኃጢአት ምክንያት ለሚመጣ ጥያቄ መልሳችን የሆነው ክርስቶስ ጠበቃችን የምንለው ያንን ነው። ኃጢአት ዋጋ እንደማስከፈሉ መጠን ንስሐ ስንገባ ስለፈጸምነው ኃጢአት የምንከፍለው ዋጋ ስለሌለን የክርስቶስ ሞት ስለእኛ ምትክ ወይም ጠበቃ ሆኖ ይቅርታን ያስገኝልናል ማለት ነው። በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረና በኃጢአት የመጣውን ጥል ተከራክሮ በሞቱ ያሸነፈ ጠበቃ በሰማይ አለን የምንለውም ለዚህ ነው።  ወንጌላዊው ዮሐንስም በመልእክቱ የነገረን ያህንኑ ነው። እንዲህ እንዳለ፤
«ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ» 1ኛ ዮሐ 2፤1-2
ኃጢአትን የሚያስተሰርየው ክርስቶስ ብቻ ነው። ከሰው ልጅ ይህንን ማድረግ የተቻለውና የሚቻለው ማንም የለም። ኃጢአትን የሚደመስሰው 41 ስግደት ወይም መስቀል መሳለም አይደለም። ስለኃጢአት ንስሐ ለሚገቡ አስተማማኝ ይቅርታን ማስገኘት የተቻለው መስዋዕት ክርስቶስ ብቻ ነው። «ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን» በማለት ወንጌላዊው የነገረን ያንን የደም ስርየት ነው።

2/ ይቅርታ

 «ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና» 1ኛ ዮሐ3፤8  የኃጢአትም ዋጋው ሞት ነው። (1ኛ ቆሮ 15፤56) ከዚህ ሞት ለመዳን ኃጢአትን ስለመፈጸሙ የተጸጸተና ዳግመኛ ወደንስሐ የቀረበ ማንም ቢኖር የሞት ስርየቱ ያው አንዱ የቀራንዮው መስዋዕት ብቻ ነው። በዚያም ይቅርታን ያገኛል። «ኃጢአታችንን ይቅር በለን» ብለን እንጸልይ ዘንድ ተነግሮናል። ምክንያቱም « በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው» 1ኛ ዮሐ 1፤9
 ሲሞን መሰርይ የተነገረውን ትእዛዝ ከመፈጸም ይልቅ ጉዳዩን ወደሐዋርያው ሲመልስ ከማየታችን ውጪ ሐዋርያው ጴጥሮስም ለሲሞን በትክክል ስለኃጢአት የነገረው ቃል ይህንኑ ነበር። «እንግዲህ ስለዚህ ክፋትህ ንሰሐ ግባ፥ ምናልባትም የልብህን አሳብ ይቅር ይልህ እንደ ሆነ ወደ እግዚአብሔር ለምን» የሐዋ 8፤22
ስርየት የንስሐ ውጤት ነው። በዚህም የይቅርታን ጸጋ ይጎናጸፋል። ስርየታችንም የክርስቶስ ደም ነው። ኃጢአታችንን ስንናዘዝ በክርስቶስ የይቅርታን ሕይወት እናገኛለን።  «አሁን ግን ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ተገዝታችሁ፥ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው» ሮሜ 6፤22 ንስሐ የገባ ሕይወት ከእምነት በሆነ መጸጸትና መመለስ ከእግዚአብሔር ይቅርታን ያገኛል። ንስሐ የጨፈገገ ልብ ነው። ሀዘን የተጎዳኘው። ይቅርታ ተስፋ ነው። ከሀዘን ወደ ሕይወት ፍካት የመመለስ ጎዳና። ተሐድሶ ዋስትና ነው። በገባው ንስሐና በተገኘ ይቅርታ ላይ የሚኖሩት አዲስ የለውጥ መንገድ ነው።

3/ ተሐድሶ

ተሐድሶና አዲስ ነገር መፍጠር የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን መለየት ይገባናል። ተሐድሶ የነበረው ማንነት ሲያረጅ፤ ሲፈርስ ወይም ሲበላሽ ወደቀድሞ ማንነቱ የመመለስ ወይም የማስተካከል አካሄድን ያመለክታል። በበደል ከንጽሕና የመጉደል ማንነት ደግሞ ኃጢአተኝነት ነው። ከኃጢአት የመንጻት ማንነት ደግሞ ወደቀደመው የሕይወት ማንነት መመለስ ማለት ነው። ይህም አሠራር መታደስን፤ መለወጥን፤ መስተካከልን፤ ዳግም መመለስን ያመጣል።
አዲስ መሆን ማለት ግን ያልነበረ አዲስ ግኝት፤ አዲስ ነገርን መጎናጸፍን፤ መፍጠርና መሥራትን ያመለክታል። ብዙ ጠማማዎች መታደስንና አዲስነትን በማምታታት የዋሃንን ለማሳሳት ሲሞክሩ ይስተዋላል። ስለተሐድሶ ምንነት መጽሐፍ ቅዱሳችን በደንብ አድርጎ የተናገረ ቢሆንም ያንን እውነት በጥመት እየተረጎሙ ከእግዚአብሔር ቃል ውጪ ሲያፈነግጡ እናያቸዋለን።  ከላይ በመግቢያችን ላይ ለመጠቆም እንደሞከርነው «ቤተ ክርስቲያን አትታደስም» የሚሉ ወገኖች መታደስን አዲስ ነገር ከመፍጠር ጋር በማያያዝ ቃሉን በማጣመም የመተርጎም ግትርነት የተነሳ ነው። ቤተ ክርስቲያን ወይም ኤክሌሲያ ማለት የክርስቲያን ጉባዔ ማለት ነው። የክርስቲያኖች ጉባዔ ደግሞ በክርስቶስ ያመኑ ሰዎች ማኅበር ማለት ነው። ጉባዔ ክርስቲያን ለግል ጸሎት፤ ለማኅበሩ ለራሱ፤ ለሀገርና ለዓለሙ ኃጢአት ስለይቅርታው ይጸልያሉ። በግል የበደሉ ሰዎች በንስሐ ይታደሳሉ። የጎደለው እንዲመላ፤ የጠመመው እንዲቀና፤ የስህተት መንፈስ እንዲወገድ ምህለላና ልመና ያደርጋሉ። የእግዚአብሔር ፈቃድ ያለበት ተሐድሶቱ እንዲመጣ አበክረው ይጸልያሉ። መታደስን ከሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ጋር የሚያያዙ ካሉ የማትታደስ ህንጻ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ምድር የለችም።በአክሱም ያለችው የታቦተ ጽዮን ማደሪያ ቤት እንኳን ስንት ጊዜ ታደሰች? እነሆ አሁንም እየታደሰች ነው። የሳር ክዳን በቆርቆሮ ክዳን ይታደሳል። የጠመመው ግድግዳ፤ የፈረሰው ጣሪያ ይቃናል። ይታደሳል። በክርስትናው ዓለም ሰውም፤ ቤተ ጸሎቱም ይታደሳል። ቤተ ክርስቲያን ማለት ሰውም፤ ቤተ ጸሎቱም ማለት ከሆነ የማይታደሰው ምኑ ነው? እስከሚገባን ድረስ ቤተ ጸሎቱም ቤተ ሰዎቹም ይታደሳሉ። ዘማሪው ዳዊት «ነፍሴ ሆይ» በሚለው ዝማሬው እንዲህ ይላል።
«ኃጢአትሽን ሁሉ ይቅር የሚል፥ ደዌሽንም ሁሉ የሚፈውስ፥
ሕይወትሽን ከጥፋት የሚያድናት፥ በምሕረቱና በቸርነቱ የሚከልልሽ፥
ምኞትሽን ከበረከቱ የሚያጠግባት፥ ጕልማስነትሽን እንደ ንስር ያድሳል» መዝ 103፤1-5

ማደስ የእግዚአብሔር ሥራ መሆኑን ልንክድ አይገባም።
ሕዝበ እስራኤል ከባቢሎን ምርኮ ይመለስ ዘንድ በተፈቀደለት ጊዜ ነህምያ የቤተ መቅደሱን ቅጥር ለማደስ ከተወሰኑት ጋር ከባቢሎን ወደፈረሰችው ኢየሩሳሌም ወጥቶ ነበር። (ነህምያ 2፤1-20) ነገር ግን  ቅጥሩን የማደስ ሥራ እንቅፋት ገጠመው። ገሚሱ ፈቃድ ከሰጠው ከንጉሡ ጋር ለማጋጨት ሞከረ፤ ገሚሱም ጠላት ሆኖ መታደስ የለበትም በማለት በቀጥታ ጦርነት ገጠመ። የነህምያ የተሐድሶ ሥራ ፈተናው የጠፋውን ቅጥር ወደነበረበት መመለስ ብቻ ሳይሆን ከተቃዋሚዎች ጋር መዋጋትም ነበረው።
«ቅጥሩንም የሚሠሩትና ተሸካሚዎቹ በአንድ እጃቸው ይሠሩ ነበር፥ በአንድ እጃቸውም የጦር መሣሪያቸውን ይይዙ ነበር። አናጢዎቹም ሁሉ እያንዳንዱ ሰይፉን በወገቡ ታጥቆ ይሠራ ነበር ቀንደ መለከትም የሚነፋ በአጠገቤ ነበረ» ነህምያ 4፤17-18
የቤተ መቅደሱ መታደስ ፈተና በዚህ ብቻ ያበቃ አልነበረም። የራሱ ሰዎች ዘመነ ድርቁን ተገን አድርገው የተቸገሩ ሰዎቻቸውን በወለድና በአራጣ ብድር አስጨንቀው ያዟቸው። ንብረቶቻቸውን በወለድ አገድ በመያዝ ባዶ አስቀሯቸው። ለንጉሥ የሚከፈለውን ግብር መክፈል እስኪያቅታቸው ድረስ ግድ አሏቸው። በዚህም የተነሳ የቤተ መቅደሱ መታደስ ፈተና ላይ ወደቀ። ለመታደሱ የእግዚአብሔር እጅ ስለነበረበት በሰዎች ወጥመድ ተስተጓጉሎ የሚቀር አልነበረም።
«በወንድሞቻቸውም በአይሁድ ላይ ትልቅ የሕዝቡና የሚስቶቻቸው ጩኸት ሆነ። አያሌዎቹም። ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ብዙዎች ናቸው በልተንም በሕይወት እንድንኖር እህልን እንሸምት ይሉ ነበር። አያሌዎቹም። ከራብ የተነሣ እህልን እንሸምት ዘንድ እርሻችንና ወይናችንን ቤታችንንም አስይዘናል ይሉ ነበር። ሌሎቹም። ለንጉሡ ግብር እርሻችንንና ወይናችንን አስይዘን ገንዘብ ተበድረናል አሁንም ሥጋችን እንደ ወንድሞቻችን ሥጋ፥ ልጆቻችንም እንደ ልጆቻቸው ናቸው እነሆም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ባሪያዎች ይሆኑ ዘንድ ሰጥተናል፥ ከሴቶችም ልጆቻችን ባሪያዎች ሆነው የሚኖሩ አሉ ታላላቆችም እርሻችንና ወይናችንን ይዘዋልና ልናድናቸው አንችልም ይሉ ነበር። እኔም ጩኸታቸውንና ይህን ቃል በሰማሁ ጊዜ እጅግ ተቈጣሁ። በልቤም አሰብሁ፥ ታላላቆቹንና ሹማምቱንም። ሁላችሁ እያንዳንዳችሁ ወለድ ትወስዳላችሁ ብዬ ተጣላኋቸው ትልቅም ጉባኤ ሰበሰብሁባቸው። እኔ ለአሕዛብ የተሸጡትን ወንድሞቻችንን አይሁድን በፈቃዳችን ተቤዠን እናንተስ ወንድሞቻችሁን ትሸጣላችሁን? እነርሱስ ለእኛ የተሸጡ ይሆናሉን? አልኋቸው። እነርሱም ዝም አሉ፥ መልስም አላገኙም።  ደግሞም አልሁ። የምታደርጉት ነገር መልካም አይደለም ጠላቶቻችን አሕዛብ እንዳይሰድቡን አምላካችንን በመፍራት ትሄዱ ዘንድ አይገባችሁምን? እኔም ደግሞ ወንድሞቼም ብላቴኖቼም ገንዘብና እህል ለእነርሱ አበድረናል እባካችሁ፥ ይህን ወለድ እንተውላቸው። እርሻቸውንና ወይናቸውን ወይራቸውንና ቤታቸውንም ከእነርሱም የወሰዳችሁትን ገንዘቡንና እህሉን፥ ወይን ጠጁንና ዘይቱን ከመቶ እጅ አንድ እጅ እባካችሁ ዛሬ መልሱላቸው። እርሱም፦ እንመልስላቸዋለን፥ ከእነርሱም ምንም አንሻም እንደ ተናገርህ እንዲሁ እናደርጋለን አሉ። ካህናቱንም ጠርቼ እንደዚህ ነገር ያደርጉ ዘንድ አማልኋቸው። ደግሞም ልብሴን አራገፍሁና። ይህን ነገር የማያደርገውን ሰው ከቤቱና ከሥራው እንዲሁ እግዚአብሔር ያራግፈው እንዲሁም የተራገፈና ባዶ ይሁን አልሁ። ጉባኤውም ሁሉ። አሜን አሉ፥ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ ሕዝቡም እንደዚህ ነገር አደረጉ»  ነህምያ 5፤ 1-13
የመታደሱ ሥራ እንቅፋት ሌላ ሦስተኛ እንቅፋት ገጠመው። የአገሩ ገዢ ሆኖ በነጉሡ የተሾሙት ሰንባላጥና ዐረባዊው ጌሳም ነህምያን ለመግደል ቅድ ነደፉ።  ሰንባላጥም ከቆላውም ስፍራ እንገናኝ ብሎ አምስት ጊዜ መልእክት ጻፈለት። ነህምያ ንጉሥ ሆኖ በኢየሩሳሌም ተቀምጧል እያሉ ከንጉሡ ሊያጣሉህ ነውና ተገናኝተን መፍትሄ እንስጠው በማለት ለጻፈለት ደብዳቤ ነህምያ የሰጠው መልስ መታደሱን ለማስተጓጎል የተፈጠረ የአንተ ድርሰት ነው የሚል ነበር።
«እኔም አንተ ከልብህ ፈጥረኸዋል እንጂ እንደ ተናገርኸው ነገር ምንም የለም ብዬ ላክሁበት።  እነርሱም ሁሉ ሥራው እንዳይፈጸም እጃቸው ይደክማል ብለው ያስፈራሩን ዘንድ ወደዱ አሁንም፥ አምላክ ሆይ፥ እጄን አበርታ» ነህምያ 6፤ 8-9
የመታደስ አገልግሎት ወደቀመ ማንነት የመመለስ ጎዳና በመሆኑ ተቃዋሚው ብዙ ነው። በአሮጌው ሕይወት ወድቀው እንዲቀሩ፤ የቀደመ ክብራቸውና ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣቸውን ጸጋ እንዳያገኙ የሚያደርግ ተቃውሞ ፈታኝ ቢሆንም እግዚአብሔር ለተሐድሶት ያለው ዓላማ ሰዓቱ ከሆነ ማንም ሊያስቀረው አይችልም። በነህምያ ሕይወትም ያየነው እውነት ይህንኑ ነበር። የመታደሱ ሥራ ለእግዚአብሔር ቃል አገልግሎት እና ክብር እንጂ ለሰውኛ ጥቅም እስካልሆነ ድረስ ተሐድሶቱ እውን መሆኑ አይቀሬ ነው። ብዙ ሴራዎችና እንቅፋቶች ሊገጥሙ ይችላሉ። አሸናፊው ግን የእግዚአብሔር ዓላማ ነው። በእስራኤላውያንም የተሐድሶ ትግል ያየነው ነገር ይህንኑ ነበር። የቅጥሩ ሥራ እንደተፈጸመ የሕጉ መጽሐፍ ከተሸሸገበት ወጥቶ ይነበብ ጀመር። ነህ 7፤1-18 ያን ጊዜም «
ዕዝራም ታላቁን አምላክ እግዚአብሔርን ባረከ ሕዝቡም ሁሉ እጃቸውን እየዘረጉ። አሜን፥ አሜን ብለው መለሱ። ራሳቸውንም አዘነበሉ፥ በግምባራቸውም ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ» ነህ 7፤6
ከሞዓባውያንና አሞናውያን ጋር የተደባለቁ ሰዎች የእግዚአብሔር ሕዝቦች ሊባሉ እንደማይችሉ ከሕጉ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ ስለተገኘ እንዲለዩ ተደረገ። ተከድኖ የኖረው የሕጉ መጽሐፍ ሲገለጥ የተሸሸገው ስህተት ይፋ ይወጣ ጀመር። ተሐድሶቱ ሲመጣ እግዚአብሔር ብቻ ይከብራል።
«በዚያም ቀን የሙሴን መጽሐፍ በሕዝቡ ጆሮ አነበቡ አሞናውያንና ሞዓባውያንም ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ለዘላለም እንዳይገቡ የሚል በዚያ ተገኘ። የእስራኤልን ልጆች በእንጀራና በውኃ ስላልተቀበሉአቸውና ይረግማቸው ዘንድ በለዓምን ስለ ገዙባቸው ነው ነገር ግን አምላካችን እርግማኑን ወደ በረከት መለሰው። ሕጉንም በሰሙ ጊዜ ድብልቁን ሕዝብ ሁሉ ከእስራኤል ለዩ»  ነህ 13፤1-3
ካህኑ ዕዝራም ከቤተ መቅደሱ መታደስ በኋላ በመጽሐፉ እንደተጻፈው ይኖሩ ዘንድ ሕዝቡን ግድ ሲላቸው ነበር። የሕንጻው መታደስ እስራኤላውያንም ለእግዚአብሔር ቃል እንደሚሆን መታደስን ካላመጣ ምንም ስላልነበር ቃሉ በሚያዘው መንገድ እንዲታደሱ አድርጓቸዋል።
«ካህኑም ዕዝራ ተነሥቶ ተላልፋችኋል፤ የእስራኤልን በደል ታበዙ ዘንድ እንግዶችን ሴቶች አግብታችኋል። አሁንም ለአባቶቻችሁ አምላክ ለእግዚአብሔር ተናዘዙ፥ ደስ የሚያሰኘውንም አድርጉ፤ ከምድርም አሕዛብና ከእንግዶች ሴቶች ተለዩ አላቸው» ዕዝ 10፤10-11
እንግዳ ጋብቻን ከልዩ ልዩ አማልክት ጋር የሚፈጽሙና የሚያስፈጽሙ መጻሕፍትና አዋልድ እስካልተወገዱ ድረስ ንጹህ አምልኮተ እግዚአብሔር ሊኖር አይችልም። መዳን በአንዱ በእግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ እስካልተነገረ ድረስ የእንግዶች አማልክት ጋብቻ አደገኛ ነው። «ዐሥርቱ ቃላተ ወንጌልን ይሁን ስድስቱ ቃላተ ወንጌልን ከመጠበቅ ይልቅ ተአምሯን ለመስማት ተሸቅዳደሙ» ከሚለው አምልኮተ ጣዖት ጋር ውልን እስካላፈረሱ ድረስ እግዚአብሔርን ማምለክ አይቻልም። «ሥሉስ ቅዱስን የካደ ተአምሯን ሰምቶ ዳነ» ከሚል አጋንንታዊ ትምህርት እስካልተላቀቁ ድረስ እውነተኛ አስተምህሮ በጭራሽ አይታሰብም።  በሰዎች ላይ የመዳን ተስፋ እንድናደርግ በማበረታታት ከራሳችን አልፎ የማናውቃቸውን ሠላሳ እና ዐርባ ትውልድ ዘሮቻችንን እንደሚያስምሩ ቃል ተገባላቸው በተባለ፤ የቂጣ፤የንፍሮ፤ የአፈር፤ የፍርፋሪ፤ የተቅማጥ ወዘተ የተስፋ መንገዶች ሆነው ከእግዚአብሔር ተሰጥተውናል የሚሉ ቢኖሩ በቃለ ኤጲፋኒዮስ የተረገሙ ናቸው።
«ወኢኮነ ተስፋ መድኃኒትነ በሰብእ፤ ወኢክህለ ሰብእ ያድኅነነ እምአዳም እስከ ተፍጻሜተ ዓለም አላ ውእቱ እግዚአብሔር ቃል ዘተሠገወ። ከመ ኢይኩን ተስፋነ በሰብእ ወኢንኩን ርጉማነ ወዳእሙ በእግዚአብሔር ሕያው» ሃይማኖተ አበው ዘኤጲፋንዮስ 59፤9-12
«የድነታችን ተስፋ ፍጡር በሆነ ሰው የተገኘ አይደለም። ከአዳም ጀምሮ እስከፍጻሜ ዓለም ሊያድነን የተቻለው(የሚቻለው) የለም። ርጉማን እንዳንሆን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ ፍጡር በሆነው ሰው ላይ ተስፋ እንዳናደርግ።
ማጠቃለያ፤
ተሐድሶ ከውድቀት ለተነሳ፤ ወደእውነት ለመጣ ማንነት፤ ከስህተት ለተመለሰ ሕይወት የሚሰጥ ስያሜ ነው። መታደስ ጥንትም የነበረ፤ ዛሬም ያለ፤ ነገም የሚኖር ከእግዚአብሔር የሆነ ለሰዎች የተሰጠ መንገድ ነው። ኃጢአት በንስሐ ስርየትን ታመጣለች። ስርየት ይቅርታን ታስገኛለች። ይቅር የተባለ ደግሞ የታደሰ፤ የተስተካከለ ማንነትን ይጎናጸፋል። በሕጉ፤ በቃሉ እንደቀድሞው ለመኖር ዳግመኛ ቃል የሚገባበት ተስፋ ነው። በዚህ ተስፋ እስራኤላውያን መቅደሳቸውንም፤ ራሳቸውንም ከስህተት አድሰዋል።  ተሐድሶ የሚያስፈልገው የቀደመውን መንገድ መልሶ ለመከተል ነው። «መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ» በተባለ ጊዜ የተነገረው ቃል ይኸው ነበር። «የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና» ተባለ። ስለዚህም ምን እንዲያደርግ ተነገረው?
«እንግዲህ ከወዴት እንደ ወደቅህ አስብ ንስሐም ግባ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ፤ አለዚያ እመጣብሃለሁ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ» ራእይ 2፤4-5
የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ወደቀደመ ማንነቷ፤ ለእግዚአብሔር ብቻ ወደነበራት ቀናዒነትና ፍቅር እንድትመለስ በዮሐንስ በኩል በእግዚአብሔር የታየላት ራእይ ቢደርሳትም ለመስማት አልፈለገችም። ከጣዖት ጋር መሰሴኗን አልተወችም። እንደኤልዛቤልም እውነቱንና የዋሃኑን መግደል አላቆመችም። የንስሐ እድል ቢሰጣትም ከዝሙትና ግልሙትናዋ አልታቀበችም። ነገር ግን በውስጧ የነበሩ ትያጥሮናውያን የኤፌሶንን ቤተ ክርስቲያን ድርጊትና ሰይጣናዊ አስተምህሮ ላልተቀበሉት ተስፋ ተሰጣቸው። እስከመጨረሻውም ጽኑ ተባሉ። የተነገረውን ተቀብላ ተግባራዊ ማድረግ የተሳናት የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን መቅረዟ ተወስዶ ከነአነዋወሯ ከጠፋ እነሆ ሁለት ሺህ ዘመናት ሆነ። የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በኤጂያን ባህር ዳርቻ ፍርስራሾቿ የሚጎበኙ የቱርክ ኢስላማዊ ግዛት ከተማ ሆናለች።
የኛይቱ ኤፌሶንም ከትያጥሮን ቤተሰዎቿ የሚነገራትን ተሐድሶ ትቃወማለች። ነገር ግን በቁጥር መሳ ለመሳ እየሆናት ከመጣው ኢስላም ጋር በአንድ ወንበር ቁጭ ብላ ስለሰላም አወራለሁ ትላለች። እንዲያውም ከሕዝቡ ቁጥር 50-60% ኢስላም ነው እያለ የራሱን መንግሥት ናፋቂ ከሆነ ሃይማኖት ጋር ጊዜዋን ከምትገድል ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚጠበቅባትን ፈጽማ የቀድመ ኃይሏን ማደስ አይሻላትም ነበር? ዝሙትና የዝሙት ወሬ፤ ግፍና ቅሚያ፤ በደልና ዐመፃ፤ ስካርና ባዕድ አምልኮዋን ማስወገድ አይሻላትም ነበር? ከንቱ ተስፋና ስሁት ምክንያተ ድኂን ከምትዘራ ይልቅ እውነቱን በአደባባይ ብትመሰክርና የቀደመ የንጉሥ ፍቅሯን ብትመልስ አይሻላትም? ከንቱ ጋብቻቸውን እንዳፈረሱ እስራኤላውያን በሰዎች ላይ የተንጠላጠለ ከንቱ ጋብቻዋንና የጋብቻ መጽሕፍቶቿን ጥላ ልብን በሚያቃጥለው በንጉሡ መጽሐፍ ላይ መጣበቅ አይበጃትም ነበር?
 እምቢ አልሰማም ብትል ግን ንጉሥ በቃሉ ከተናገረው አንዳች አያስቀርም። እነዚያ ተሟጋች ነን ባይ ልጆችሽን ጨምሮ ስሁቱን አስተምህሮዋን እንደእውነት ለተናገሩ ሁሉ ዋጋቸውን ይሰጣቸዋል።  «ልጆችዋን በሞት እገድላቸዋለሁ» ራእይ 2፤23
«መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት ያለውን ይስማ» ማለቱ ለዛሬዋም ቤተ ክርስቲያንም ጭምር መሆኑን ልናስተውል ይገባናል።

Tuesday, February 3, 2015

የፓስተር ተከስተ ጌትነት የወሲብ ቅሌት በቪኦኤ

የዝሙትና የአፍቅሮ ንዋይ አንበሳ ያልሰበረውን መንፈሳዊ ሰው ማግኘት ከባድ እየሆነ ነው። በመጨረሻው ዘመን ላይ ሰይጣን እንደሚያገሳ አንበሳ እየዞረ ሰዎችን የሚሰብርበት ትልቁ መንጋጋው ትዕቢት፤ ዝሙትና ገንዘብን መውደድ ናቸው።
በየቤተ እምነቶቹ ትላልቅ የሚባሉት ሁሉ መንፈሳዊ አከርካሪያቸው የተሰበረው በነዚህ ወጥመዶች ነው። ጳውሎስም አለ፤ «ስመጣ፥ እንደምወደው ሳትሆኑ አገኛችሁ ይሆናል እኔም እንደምትወዱት ሳልሆን ታገኙኝ ይሆናል ብዬ እፈራለሁና፤ ምናልባት ክርክር ቅንዓትም ቁጣም አድመኝነትም ሐሜትም ማሾክሾክም ኩራትም ሁከትም ይሆናሉ፤
እንደ ገና ስመጣ በእናንተ ዘንድ አምላኬ እንዲያዋርደኝ፥ አስቀድመውም ኃጢአት ከሠሩትና ስላደረጉት ርኵሰትና ዝሙት መዳራትም ንስሐ ካልገቡት ወገን ስለ ብዙዎች ምናልባት አዝናለሁ ብዬ እፈራለሁ»
2ኛ ቆሮ 12፤20-21