አማለደ፣ በግእዙ ግስ «ተንበለ» ማለት ሲሆን ትርጉሙም መለመን፣መጸለይ፣ማማለድ አማላጅ መሆን፣ማላጅ፣አስታራቂ፣
እርቅ ፍቅር ይቅርታ መለመን ማለት ነው። for PDF (Click Here )
አማላጅ ሲል አንዱ ለሌላው ይቅርታን፣እርቅን ሰላምን
ለማስገኘት በአድራጊውና በተቀባዩ መካከል የሚያገናኝ መስመር ማለት ነው። ይህም ተቀባዩ ከአድራጊው ጋር የሚኖረውን ግንኙነት የተስተካከለ
እንዲሆን በመካከለኛነት አገኛኝ ድልድል በመሆን ማገልገል የማማለድ አገልግሎት ይሰኛል።
የአማላጅነትን ወይም የማማለድን ርእሰ ጉዳይ ለማብራራት
ከማምራታችን በፊት እስኪ ስለሰውኛነታችን ጥቂት እንበል።
የሰው ልጅ በዚህ ምድር ሲኖር ከተለየው ሰማያዊ ጸጋ የተነሳ ደካማ ፍጥረት ሆኗል። ሥራው ሁሉ የሚከናወነው በድካምና በመከራ
ብቻ ነው። አሜከላ እሾህ የሚወጉትና ጸሐይ የሚያጋየው ደካማ ፣ ይፈሩት የነበሩትን እንስሳት የሚፈራ ፈሪና ድንጉጥ ሆኗል። ሸኰናው
የሚነከስ የደዌና የሞት ሰው በመሆኑ አኗኗሩን አስቸጋሪ አድርጎታል። ስለዚህ ከዚህ ዓይነት አሰልቺ አኗኗር ለመገላገል ወይም የኑሮውን
የክፋት ኃይል ለመቀነስ ልዩ ልዩ መንገዶችን ለመጠቀም ተገዷል። የሰው ልጅ ዛሬ ካለበት ስልጣኔ ደረጃ ለመድረስ የቻለው ለመኖር
አዳጋች የሆነበትን የውደቀት ምድር የተሻለችና ድካሙን የምትቀንስለት ለማድረግ ከመፈለግ የተነሳ መሆኑ ይታወቃል። ያማ ባይሆን ኖሮ በእሾክና በእግር መካከል ጫማን፣
በአቧራና በጸሐይ መካከል መነጽርን፤ በጊዜ ክፍልፋይ መካከል ሰዓትን፤ በእርዛትና በመጠለያ ግኝት መካከል ቤትን፣ በህመምና በደዌ መካከል መድኃኒትን በመፍጠር የሚያስማማ
ነገርን ለመስራት ባልቻለነበር።
የኑሮው መጠን እየሰፋና ቁጥሩ እየጨመረ በሄደ
ጊዜ ደግሞ አንዱ አንዱን የማገዝ፣ የመረዳዳት፣ የመደጋገፍ አስፈላጊነቱ እያየለ በመምጣቱ ሰው ያለሰው ለመኖር አለመቻሉ ገሃድ እየሆነ
መጥቶ ዛሬ ላለንበት የማኅበራዊ መስጋብሮቻችን ትስስር ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረስ አብቅቶናል። የሉላዊው ዓለም (Globalization) ነባራዊ ኩነትም ይህንን በግልጽ ያሳየናል።
እያንዳንዱ ሰው እርሱ የማይችለውን ለመስራት ወይም
ለመፈጸም በሌላው ላይ ጥገኛ የመሆን ወይም የሌላውን አጋዥነት የመፈለግ ሁኔታ በእለት ከእለት ኑሮው ውስጥ በመስተዋሉ ጉልበትን
በገንዘብ በመግዛት ወይም የሌላውን እውቀት ለጥቅም በማዋል ወይም
በእውቀትና ጥበብ ሌላውን በመጨበጥ ወይም የማያገኘውን ለማግኘት በመሞከር ከአቅሙ በላይ ለሆነው ተግዳሮት ሁሉ ድጋፍ
የሚፈልግበት ዓለም ውስጥ በመገኘቱ የተነሳ ሰጪና ተቀባይ፣ ለማኝና ተለማኝ፣ ኃያልና ደካማ፣ ሀብታምና ደሃ፣ ገዢና ተገዢ፣ መሪና
ተመሪ የመሆን ክስተቶች ሊስተዋሉ የግድ ሆኗል። እናም የሰው ልጅ ችግሮቹን፣ እንቅፋቶቹንና መሻቱን ለመቋቋም መደገፊያ አስፈልጎታል።
ከሰፊውና ውስብስቡ ነባራዊ ሁኔታዎቻችን ውስጥ ለማሳያነት ብንጠቅስ፤ አንድ ሰው በአንድ መሥሪያ
ቤት የሚኖረውን ጉዳይ በአቋራጭ ለማስፈጸም ቢፈልግ ከጉዳዩ ባለቤት ጋር ቅርበት ወይም የጠበቀ ግንኙነት ያለውን ሰው እንዲያስፈጽምለት
በአገናኝነት ይልካል። ብዙ ውጣ ውረድ ሳያስፈልገው ጉዳዩን በላከው መካከለኛ ሰው ድጋፍ በኩል ያስፈጽማል ማለት ነው። ያንን ድጋፍ
ለማግኘት ባይችል ዓላማው ላይፈጸም ይችል ይሆናል ወይም በሌላ ወገን ሊበላሽ ይችላል። ሰዎች እርስ በእርሳቸውን ያላቸውን ግንኙነት
ከሁኔታዎች ስፋት አንጻር የተራራቀ ሲሆን ስፋቱን የሚያጠ’ቡ’ ድልድዮችን
ሊዘረጉ ይገደዳሉ።
ዛሬ በእለት ኑሮአችን ውስጥ ከምናያቸው ነገሮች
መካከል ለጋብቻ ሽማግሌ፤ ለቤት ኪራይ ደላላ፣ ለሥራ እውቀት፣ ለጸብ አስታራቂ፣ ለጦረኞች ጠብመንጃ አስማሚና አገናኝ ኃይል ሆነው ሲያገለግሉ እናያለን። ቤት ተከራይንና ኪራይ
ቤትን በመካከል የሚያገኛኝ መንገዱ ደላላ መሆኑ ሰው ለችግሮቹ መፍትሄ ማግኛና ጥቅም ማስገኛ እንዲሆን የፈጠረው መላ ስለመሆኑ አይጠፋንም።
እንግዲህ በዚህ ምድር ላይ የሰው ልጅ ተገቢ የሆነ አገልግሎት ለማግኘት ይሁን ያልሆነ ጥቅም ለማግኘትም ጭምር ቢሆን በዘመዱ፤ በገንዘቡ፣ በወዳጁ፤ ከጉዳዩ
ጋር ቅርበት ባላቸው ሰዎችም በኩል አሸማጋይ፣ አስታራቂ፣ አማላጅ በማዘጋጀትና በመላክ እርሱ በቀጥታ ማድረግ ወይም ማስደረግ የማይችለውን
ነገር በሌላ በሦስተኛ ወገን ጉዳዩን ከፍጻሜ ሲያደርስ ኖሯል፤ ወደፊትም
ይኖራል።