Monday, April 3, 2017

ከእንግዲህ የክርስትና ኃይማኖት ተከታይ አትበሉኝ!


አይደለሁምና፤ አዎን አይደለሁም።
የፕሮቴስታንትም ኃይማኖት ተከታይ አትበሉኝ።
አይደለሁምና።
የሆነ ጊዜ መናፍቅ ትሉኝ እንደነበረም አስታውሳለሁ።
ለምን አላችሁኝ ብዬ አልከፋም!
ታላቁ የእምነት ሞዴላችን ቆራጡ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስም በአንድ ጠርጠሉስ በሚባል አእምሮ በደነዘዘው አይሁድ "መናፍቅ!" ተብሏልና።(የሐዋ.ሥራ 24:5)
ግድ የለም።
የክርስትና ኃይማኖት ተከታይ በመሆን መንግሥተ ሰማይ አይገባም።
ክርስቶስም ይህንን ቃል አልገባልንም፣ የአባቱን ፈቃድ የሚፈጽሙትን ነው እንጂ..።
ጌታ ጌታ ስላልክ፥ በሃሌ ሉያ ስላንጋጋህ፥ በፉጨት በእልልታ ስለቀወጥክ፥ ባይብል በእጅህ ስላልተለየ፥ኢየሱስ ኢየሱስ ስላልክ፣ በየማምለኪያ አዳራሽ ስለተገኘህ፥ በአዲስ ቋንቋ ስለተናገርክ፤ ፐ! አንተ የእግዚአብሔር ሰው ስላሉክ፣በሱፍ በከረባት በየአደባባዩ ስለተገለጥክ፥ ከባህር ማዶ ጀምሮ የአገልግሎትህ ኮሜንት "ተባረክ" ስለጎረፈልህ...በቃ ....እንዲያ በማለት ሰማይ የገባክ አይምሰልህ።
ይሄም ዋስትና አይደለም።
አርብ እሮብ ስለጾምክ፥ ይሄም ሳያንስህ ወራትን ሳምንታትን በመላምት ስያሜ እያቆላመጥክ ክርስትና አይሉት ግብዝና በመጾምህ የተመጻደቅክ ቢመስልህ፣በባዶ እግርህ ስለተጓዝክ፣ግሽን፤ ኩክ የለሽን ስለተሳለምክ፥ ደብረ ዳሞን ስለወጣክ፣ ስዕለትህን በሩቅ ሀገር ንግስ ስላደረስክ፣ ሰባት አመትኮ በአንድ እግሩ ቆሞ ፐ! ብለህ ተከታይህ ነኝ ስላልክ አይደለም፥ዳገት ቁልቁለቱን ወጥተህ ስለወረድክ አይምሰልህ።
በቀን 5 ጊዜ ስለሰገድክ፣ ጥፍርህን ስለሞረድክ፣አፍንጫህን አሻሽተህ ሼይጢያንን እያሳደድኩ ነው ብትልና፣ዘካ ስላወጣክ፥ ጁምአ ስለሰገድክ አይደለም መንግሥተ ሰማይ በዚህ አይገኝም።
በዉል ማንነቱን ባታውቅም የአንድ አምላክ ተከታይ ነኝ ስላልክ፣ ይህ ሁሉ የመንግሥተ ሰማይ ዋስትና ሊሆን አይችልም።
አመቱን እያሰላህ በጨረቃ ተመርተህ ወሩን ሙሉ ስለጾምክ፣ ሱሪህን ስላሳጠርክ፣ ቆቡን ስለደፋህ፣ አንቺም ከጥፍር እስከራስ ስለተከናነብሽ፤ በቀዳደa አጮልቀሽ ስላየሽ መንግሥተ ሰማይ መግባት እንዲያ እንዳይመስልሽ። ይህ ሀሉ እንኳን የምትወርሽበት ለመውረስ በሚደረገው ጉዞ አንድ እርምጃ እንኳን አይሸፍንም።

አይሁድ ነሽ ሙስሊም፣ቡዲዝም ነሽ ሂንዱዝም ኦርቶዶክስ ነሽ ጴንጤ ይህ ሁሉ የመደራጃ እድር ነው።

እኔ ግን የክርስትና የኃይማኖቱ ተከታይ አትበሉኝ እያልኩኝ አንድ ነገር የምለው አለኝ፣
ማንም ምንም ብትሆን ማንነትህና ምንነትህ ለኔ ምንምምም ነው።
ነገር ግን እውነት መንገድና ህይወት እነሰ ነኝ ያለውን፤ በእኔ በቀር ወደአብ የሚደርስ ማንም የለም ያለውን፣በእኔ የሚያምን ለዘላለም ይኖራል ያለውን፣በመካከላችን ያለውን የጥል ግድግዳውን በደሙ አፍርሶ የመጣበትን አላማ ጨርሶ ተፈጸመ በማለት ወደሰማይ ያረገውን፡መጥቼም እወስዳችኃለሁ፣ከእኔም ጋር ለዘላለም ትኖራላችሁ በማለት የማናችሁም አምላክ ያልገባላችሁን ታላቅ የማይታጠፍ የተስፋ ቃል የገባልንን ፥ ስለአንተና ስለእኔ ብሎ ወደምድር በመምጣት ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር ያልቆጠረውን፤ የአብ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን ያላመነ ፤ በእርሱም በቃሉ ያልኖረ፤ በወንጌሉም ያላመነ፤ እርሱ በደሙ በመሠረተው በመሠረቱ ያልቆመ፣ጌታና መዲኅን፣የነፍሱም ዋስትና አድርጎ ያልተቀበለ ሁሉ ምንም ዋስትና የለውም። ። ። ።

ምንም የህይወት ዋስትና የለውም። ።

ይህን ስታሟላ ብቻ ነው የመንግሥተ ሰማይን የመውረስ ዋስትና የሚኖርህ።
እኔም የክርስትና አምነት ተከታይ ሳልሆን የክርስትና እምነት የመሥራቹ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ነኝ።
ስለዚህ ከዚህ በኋላ ኢትዮ ቴሌኮምም ቢሆን ክርስቲያናዊ ለሆኑ በዓላት መልካም ምኞታቸውን ሲገልጹ "የክርስትና እምነት ተከታዮች" ከማለት ይልቅ "የክርስቶስ ኢየሱስ ተከታዮች"ቢሉን ደስ ይለናል።

አዎን የክርስቶስ ኢየሱስ ተከታይ ነኝ።
የእግዚአብሔር የመንግሥቱ ሰባኪ፣
የትንሣኤው መስካሪ፣
የክርስቶስ የወንጌሉ ዘማሪ፣
አዋጅ ነጋሪ፣
የአንድ መሪ፣የአንድ አምላክ የአንድ ጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ነኝ እንጂ ""የማንም ድርጅት ወይም ቸርች"" ተከታይ አይደለሁም።

በርሱ በማመኔ ብቻ በውድ ደሙ የታጠብኩ የማይሻር ኪዳን የተገባልኝ ምጽአቱንም በማራናታ የምጠባበቅ
እእእ የደሙ ፍሬ ነኝ!!!

( Fitsum @yalkbet )

Wednesday, February 1, 2017

ፈውስ!


Tsige Sitotaw

በሁሉም ቤተ እምነቶች ዘንድ የሚታየው የፈውስ ጉዳይ ብዙ ሰዎችን ጥርጣሬ ውስጥ እያስገባ ነው ።
እስቲ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንነጋገርበት
1. ፈውስ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ
ክርስቲያን ፦
በዚች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታየው የፈውስ ሥነ ሥርዓት ያለ ፀበል የሚከናወን አይደለም ። ስለዚህም በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ፀበል በምንጭም ይሁን ከቧንቧ በተጠለፈ ውኃ የሚጠመቁ በርካታ ናቸው ።
እንዲሁም ፀበል እየተባለ በተለያዩ ቦታዎች እየተዘጋጄ በብዙ ሰልፍ የሚጠመቅ ሕዝብ ቀላል አይደለም ። በዚያ ቦታ ላይ የሚታዩትን ትርዒቶች ማየት አስገራሚ ነው ።
በክፉ መናፍስት የተያዙ ሰዎች አእምሯቸውን እየሳቱ እየወደቁ ከልባቸው እያለቀሱ ራሳቸውን እየሳቱ በብዙ መኃላ እየተገዘቱ ሲወጡና የታመሙት ነጻ ሲወጡ ይታያሉ ።
ይህ ሁሉ የሚሆነው በተለያዩ ቅዱሳን ስም በተሰየሙ ፀበሎች ነው ። ስለሆነም ኦርቶዶክሳውያን ትክክለኛ እምነት እንዳላቸውና ቅዱሳን ያማልዳሉ ለሚለው ማረጋገጫቸው ይኸው ተአምራት የሚታይበት ፀበል ቦታ ነው ።
በተጨማሪም ፦ በክፉ መንፈስ የተያዘው ሰው ራሱን ስቶ መንፈሱ በላዩ ላይ ሆኖ ሲለፈልፍ ከየትና ምን ሲያደርግ እንደያዘው መናገር ይጀምራል ።
ከየት ያዝኸው ሲባል ከጴንጤ ቸርች ምን ሲያደርግ ሲባል ኢየሱሴ ኢየሱሴ እያለ ሲለፈልፍ ትክክለኛው ሃይማኖት የትኛው ነው ሲባል ኦርቶዶክስ ሌላውስ ሲባል የውሼት እያሉ ካስለፈለፉ በኋላ ያንን በካሴት ቀድተው እውነተኛዋ ሃይማኖት ሰይጣን እንኳ የመሠከረላት ቅድስት ተዋሕዶ እያሉ ከሰይጣን በሰሙት መረጃ ሃይማኖታቸውን የሚሰብኩ ሰዎች አሉ ።
እንደገናም ሰይጣኑ ተቃጠልሁ ነደድሁ ልሂድ ልውጣ እያለ ሲጮህ ምስህ ምንድን ነው ? ተብሎ ይጠየቃል እሱም አመድ ወይም አተላ ወይም ደም ወይም ሌላ ነገር እንዲመጣለት ይጠይቃል ያዘዘው ነገር ሲቀርብለት ያንን ጠጥቶ ለቀቅሁ ብሎ ሦስት ጊዜ ጮኸህ ውጣ ዳግም ላትመለስ የሚካኤል ሰይፍ ይቁረጠኝ ብለህ ምለህ ተገዝተህ ውጣ ተብሎ ያንን ቃል ፈጽሞ ሄድሁ ብሎ ይጮሃል ። ከዚያ በኋላ ሕመምተኛው ጤነኛ ሆኖ በአእምሮው ይሆናል ማለት ነው ።
እሺ ነገሩን ተመልክተናል የሚካድም አይደለም ። ግን በመንፈሳዊ ዓይን ሲታይ በእርግጥ ፈውሱ ተከናውኗል ወይ ? ብለን ጠይቀን መልስ ማግኜት አንችልም ።
ምክንያቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምናደርገውን ሁሉ በማን ስም ማድረግ እንዳለብን አዝዞናል ።
ለምሳሌ ፦ እንደዚህም ያለውን አንድ ሕፃን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል ። የማቴዎስ ወንጌል 18÷5
ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና ። የማቴዎስ ወንጌል 18÷ 20
የክርስቶስ ስለ ሆናችሁ በስሜ ጽዋ ውኃ የሚያጠጣችሁ ሁሉ፥ ዋጋው እንዳይጠፋበት እውነት እላችኋለሁ ። የማርቆስ ወንጌል 9÷41
ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፤ እባቦችን ይይዛሉ ። የማርቆስ ወንጌል 16÷17
በተጨማሪም የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 14, 15,16 ሁሉንም ብንመለከታቸው በኢየሱስ ስም ብቻ መለመን ወይም መጸለይ እንዳለብን ታዝዘናል።
አጋንንት የሚወጡት በእርሱ ስም ሙታን የሚነሡት ለምጻሞች የሚነጹት ማናቸውም ፈውስ የሚከናወነው በጌታ ስም ብቻ እንደሆነ ታዝዘናል ።
ታዲያ እንዲህ ከሆነ በፀበልና በቅዱሳን ስም እንደሚለቁ ሆነው የሚጮሁት ለምንድን ነው ?
እንግዲያው ሰይጣን እያታለለን እያዘናጋን እንደሆነ ልናውቅበት ይገባል ። ባልተሰበከልን ልዩ ወንጌል ታስረን ከእርሱ ጋር ወደ ገሃነም እንዳንገባ ።
ስለዚህ የምናደርገውን ሁሉ በኢየሱስ ስም ብቻ ። አሜን ። አሜን ። አሜን ። ወአሜን ለይኩን ለይኩን ።
2 . ፈውስ በወንጌላውያን ፦
በአሁኑ ሰዓት እርስ በእርሳቸው የማይተዋወቁ በፕሮቴስታንትነት የሚታወቁ በርካታ ቤተ እምነቶች እየተመለከትን ነው ። አንዳንዶች በሽማግሌዎች ሲመሩ አንዳንዶች ደግሞ በግለ ሰቦች ብቻ የሚመሩ ናቸው ።
በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተመሳሳይነታቸው ይበዛል ። በአደባባይ የሚፈጸመውን ሥርዓተ አምልኮ ስንመለከትም ጸሎቱ ዝማሬው ስብከቱ አለባበሱ ልሣኑ ትንቢቱ ጥምቀቱ ቊርባኑ ሁሉ አንዱን ከሌላው መለየት አይቻልም ።
ሁሉም ለኢትዮጵያ እንግዶችና መጤዎች የሚያስመስላቸውን እንግዳ ነገር ሲፈጽሙ ይስተዋላል ። ምንም እንኳ ገድልና ድርሳን ባይኖራቸውም አሁን ባሉት አገልጋዮቻቸው በእጅጉ ስለሚደገፉባቸው የተሳሳቱ መልእክቶችን ሊያስተናግዱ ይችላሉ የሚል የብዙ ሰዎች ስጋት አለ ።
ለምሳሌ ፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳንድ ትላልቅ የእግዚአብሔር ባሪያዎች የተጠሩበትን ስም በባለቤትነት መያዝ "የግዚአብሔር ሰው" እንዲባሉ መፍቀድና ከሌላው አማኝ ልዩነት ማሳየት ።
ሰውነታቸው ከሁሉም በላይ ወፍሮና ገዝፎ እየታየ እነሱ ግን ከሁሉ በላይ እንደሚጾሙና እንደሚጸልዩ ራሳቸውን መስበክ ቲፎዞ ማብዛት ።
መናፍስትን ከሰው ሲያስወጡ መንፈሱ ለእነሱ እውቅና እንዲሰጥ እድሉን ማመቻቸት ከዚያም ከሕዝቡ ሙገሳን ጭብጨባንና አድናቆትን መቀበል ።
የሚያሳፍረው ግን ሰይጣኑ ሲለቅ ሦስት ጊዜ ጮኸህ ውጣ እየተባለ መታዘዙ ነው "ዝም ብለህ ውጣ" መባል ሲገባው ብዙ ምሥክርነት እንዲሰጥና ሰው ሁሉ እንዲገረም ማድረግና አጋንንትን ለደቀ መዝሙርነት እንደመጠቀም ያስቆጥራል ።
ያልተፈወሱ ሰዎችን ተፈውሳችኋል በማለትና ሐኪም ያዘዘላቸውን መድኃኒት እንዲያቋርጡ በማድረግ ለበርካታ ሰዎች ሕልፈተ ሕይወት ምክንያት መሆናቸውና ይህም በሕግ ፊት ደርሶ እያነጋገረ መሆኑ በተጨማሪም የገንዘብ ብክነት ሁሉ ደርሷል መባሉና በጉዳዩ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባበት መገደዱ ሌላው ፈተና ሆኗል ።
እንግዲህ በዚህ ሁሉ ፉክክር እያንዳንዱ ቤተ እምነት ለመተራረም ፈቃደኛ ባለመሆኑ አንዱ በአንዱ እየሳቀ እውነተኛ ፈውስም እየጠፋ ክርስቶስን ከሚያምነው ይልቅ የሚተወው እየበዛ መጥቷል።
አሕዛብን ዝም የሚያሰኝ በሁሉም ዘንድ መገረምን የሚያመጣ ዓይን ለሌለው ዓይን እግር ለሌለው እግር የሞተንና የተቀበረን ከሞት ማስነሣት የተካተተበት ፈውስ እንጂ ጨጓራና አንጀት ብቻ እየተባለ አገልግሎቱ ጥርጣሬ ላይ ይወድቃል እንጂ የትም አይደርስም ።
ስለዚህ በሁሉም ቤተ እምነት የሚከሰቱትን ችግሮች ማስተካከልና እንደ እግዚአብሔር ቃል ማስሄድ ቢቻል ማለፊያ ነው ።
እናንተስ ምን ታዘባችሁ ?

Wednesday, October 5, 2016

"የጎርፍ ዘመን ላይ ደርሰናል"


ቀን 08/27/2016

ይድረስ
       
ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣
ለኢትዮጵያ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሙሉ ።

   በቅድምያ እናንተ በዚህ በአገራችን በኢትዮጵያ የሥልጣን ወንበር ላይ ለበጎም ይሁን ለክፉ ያስቀመጣችሁ ቸሩ አምላክ እግዚአብሔር እርሱ ባወቀው መንገድ እንደሆነ ስለማምን ለዚህም ኃላፊነትና ሥልጣን የተሰጣችሁ ናችሁና በእየ መዓርጋችሁ የከበረ የአክብሮት ሰላምታዬን አቀርባለሁ።

  ከዚህ በመቀጠል ሌላው
 ፩ኛ ሳሙ ፲፭፥፳ "....ሳሙኤልም እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት ዛሬ ከአንተ ቀደዳት፥ ከአንተም ለሚሻል ጎረቤትህ አሳልፎ ሰጣት...."ይላል።

 ይህንን ካልኩ በኋላ በእውነቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ የዛሬ ሃያ አምስት ዓመት የደርግን መንግሥት አስተዳደራዊ ሥርዓትን አስወግዳችሁ እናንተ በትረ መንግሥቱን በጨበጣችሁ ጊዜ ምናልባት ከደርግ የተሻለ ለአንድነት ለእኩልነትና ለነፃነት የሚያስብልን፣የብሔር ብሔረሰቦችና፣ሁሉን ያቀፈ፣በሕገ መንግሥቱ የሚተዳደር መንግሥት ይፈጠራል ብሎ ሲጠብቅ እናንተ ግን የሕገ መንግሥቱን ሥርዓት ባልጠበቀ መልኩ የኢትዮጵያን ሕዝብና የኤርትራን ሕዝብ ፍላጎት ባላካተተ፣ ባልጠበቀና፣ባላገናዘበ መልኩ የኹለቱን ሰላማዊ ሕዝብ አንድነት አጥፍታችሁ፣በአንድነቱ ፈንታ ኹለትነትን ፈጥራችሁ፣ ለያይታችሁ፣በኹለቱ ሕዝብ መካከል ጥቁር ነጥብ ጥላችሁ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት፣ነፃነትና እኩልነት ያልቆማችሁ ለመሆናችሁ የምልክት ማህተብ በአንገታችሁ ያጠለቃችሁባትን ቀን ሳስብ መቼ ይሆን ይህ ዘመን የሚያልፈው ብዬ አስብ ነበር። የሚመጣውም ዘመን ምን እንደ ሚመስልና እንደሚሆን ስገምት በጣም ያስፈራኛና ያስጨንቀኝ ነበር።ታዲያ ዘመናትም ተቆጥሮ ዕለታትም አልፎ ኢየዋለ ኢያደረ ልዩነቱ፣መከፋፈሉ፣መለያየቱ፣መናናቁ፣መተራረዱ፣መገዳደሉና፣መጠላላቱ...ወዘተ በዝቶ ተባዝቶ እነሆ ዛሬ ያለንበት የደም ጎርፍ ዘመን ላይ ደርሰናል።

  ቅዱስ መጽሐፍ በማቴ ፩፪፥፳፭ ላይ "....ኢየሱስ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው።እርስ በእርሷ የምትለያይ መንግሥት ሁሉ ትጠፋለች፤እርስ በእርሱ የሚለያይም ከተማም ወይም ቤት አይቆምም....."ይላልና ይህንን በአንድነት ሊያኖረን የማይችለውን ነገር አስወግደን ለሕዝብ የፈለገውን የመጠየቅ፣የመኖር፣ፍትህ የማግኘት እድል ካልሰጠን የኛም ሕልውና አጠራጣሪ ነው የሚሆነው።ሕዝብን ሁሉ በመግደልና፣በማሰር የምንመራው ከሆነ የሚቀረው ማነው?ሁሉም ከሞተ? ሁሉ ከታሰረ? በመንግሥት ስር የሚተዳደረው ማነው?ሕዝብ አልገዛም፣ አልተዳደርም፣እምቢ ካለ? ካመፀ? ።
ስለዚህ መንግሥት ለሕዝቡ ተማርኮ እጁን ሰጥቶና በቃኝ ብሎ መውረድና ሥልጣኑንም ለሕዝቡ መልቀቅ ላለፈው ላጠፋው ጥፋትና፣ በደል ይቅርታ ጠይቆ መቀመጥ አለበት።
   ምክንያቱም እስከ ዛሬ ድረስ ለተፈጠረው ጥፋት ሁሉ በየሚድያችሁ የመንግሥት የመልካም አስተዳደር ብሉሽነት ነው ኢያላችሁ ትናገራላችሁ።ሕዝቡም ያላችሁ ይህንኑ ነው።ትርፍ ነገርም አልጨመረም።መልካም አስተዳደር ከሌለ ያለው በተቃራኒው ክፉ አስተዳደር ነው ማለት ነው።ክፉ አስተዳደር ደግሞ ለሃያ አምስት ዓመታት ከመምረር አልፎ ይጎመዝዛል።አሁን ዛሬ የናንተን የመንግሥት አስተዳደር ማብቃት የሚፈልግና የሚጠይቅ ሁሉ ዕድሜ ተርፎትና በሚመጣው አዲስ የመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ገብቶ ተደስቶና ተንደላቆ ለመኖር ፈልጎ ሳይሆን ለቀሪውና ለተተኪው አዲስ ትውልድ መልካም አስተዳደር ይምጣለት ሲል ብቻ ነው እንጂ፤እርሱማ አስራ ሰባት ዓመታት በደርግ መንግሥት፣ሃያ አምስት ዓመታት በእናንተ/ኢህአዴግ/ በአጠቃላይ ከአርባ ዓመታት በላይ በጥይት ሲቆላና ሲታመስ፣አንጀቱ አሮና ከስሎ፣ተስፋው ተሟጦ፣የሞተው ሞቶ፣የቀረው ያለ ፍትህ በየእስር ቤቱ ታፍኖና፣ታስሮ፣ሌላውም በዘር፣በጎሳ፣ቋንቋና፣ክልል ተከፏፍሎና፣ተበትኖ፣በስደት የአውሬና የውቅያኖስ እራት ኢየሆነ ይገኛል።

      ስለዚህ እናንተ የኢትዮጵያ መንግስት ባለሥልጣን ሆይ፥እስቲ እናንተም አሁን ይብቃችሁና ይህንን ምስኪን ሕዝብ በተራው በቃህ በሉትና ዕረፍት ስጡት፤እናንተም ደግሞ ዕረፉ።ደክሞአችኋል፣ዝላችኋል።አሥራ ሰባት ዓመታት በጫካ ሃያ አምስት ዓመታት በሕዝብ ጫንቃ ላይ ሳትወርዱ ተንጠላጥላችሁ በጣም ብዙ ዓመታትና ዘመናት ነው ይከብዳል።ከዚህ በላይ ብዙ ብትደክሙ መልካም አስተዳደርን ለሕዝቡ ልታመጡ በፍፁም አትችሉም።ምክንያቱም ሃያ አምስት ዓመታትን በሙሉ ተደክሞበት ያልታየ መልካም አስተዳደር በአንድ ሌሊት ስብሰባና ግምገማ በተአምራት ልታመጡ አትችሉም፣አይሆንም።ጊዜያችሁና ዕድላችሁ ሻግቶ ተበላሽቶአል።ስለሆነም እናንተ በሰላማዊ መንገድ እውነተኛ ሰላምን ፈልጋችሁ መልካም አስተዳደራዊ መንግሥት ሊፈጠርበት የሚችለውን የሕዝብ የሆነ የሽግግር መንግሥት ይመሠረት ዘንድና ሥልጣናችሁንም ለአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ድርጅት ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስረክባችሁ በሰላም ውረዱና የዘመኑን ታሪክ ሥሩ።ያን ጊዜ የታሪክ ባለቤቶች ትሆናላችሁ።
አለበለዚ ግን ነቢየ እግዚአብሔር ሳሙኤል ለእስራኤል ንጉሥ ለሳዖል እንደ ነገረው ሳዖል በእስራኤል ሕዝብ ላይ መልካም አስተዳደርን አላመጣምና "... እግዚአብሔር መንግሥትህን ዛሬ ከአንተ ላይ ቀደዳት፣ለጎረቤትህም ሰው ሰጣት.." እንዳለው የዚህ ምስኪንና ደግ ሕዝብ እንባ
ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ወደ ፀባዖት ጌታ ደርሶ መንግሥታችሁን ከእናንተ ላይ በቀደደ ጊዜ ያን ሰዓት ወየውላችሁ፣ወዮታ አለባችሁ።ምክንያቱም ያን ወቅት እናንተ በሰፈራችሁበት መስፈሪያ፣በመዘናችሁበት ሚዛንና፣በፈረዳችሁበት ፍርድ መሰፈር፣መመዘንና መፈረድ አለና ነው።
ያን ጊዜ ጩኸት ይሆናል የማይጠቅም ጩኸት ነው፤ያን ጊዜ ልቅሶ ይሆናል የማይጠቅም ልቅሶ ነው።ይህ ሁሉ የብድራታችሁ ክፍያ ውጤት ነው።

    ጊዜያት ሁሉ የአምላክ ናቸው።ሰዎች የጊዜያት ባለቤቶች አይደሉም።ነገር ግን በተሰጣቸውና፣ በተወሰነላቸው ጊዜ ውስጥ ኖረው መልካምም ይሁን ክፉ ሠርተው ያልፋሉ።ያ የሠሩትም መልካምም ይሁን ክፉ ሥራቸው ለዘለዓለም ሲነገርና ሲዘከር ይኖራል።እናም ምናልባት እናንተም ሥልጣናችሁን ተመክታችሁ ያላችሁበትን ወቅትና ሰዓት ሁሉ የእኛ ብቻ ብላችሁ የምታስቡ ከሆነ ተሳስታችኋል።ትላንት ያልነበራችሁብትን፣ዛሬ ደግሞ ያላችሁበትንና ነገ ደግሞ በተራው የማትኖሩበትን ጊዜ እንዳለ ማስተዋል ያስፈልጋችኋል ነው የምለው።ነገር ግን
እናንተ የደነደነ ልባችሁን ሰብራችሁ በይቅርታ ከዚህ ንፁህ፣ቅዱስና፣ደግ ሕዝብ ጋር ባትደራደሩ ነገ የጊዜያት ባለቤት ቸሩ አምላክ በጊዜው ለዚህ የዋህ ሕዝብ እጁን አጥፎና፣አመሳቅሎ፣ኢየታሰረ፣ኢየተደበደ፣ኢየደማና፣ኢየሞተ፣ለነፃነቱ፣ለእኩልነቱ፣ለአንድነቱና፣ለፍትህ ለሚጮኸው እናንተ ጩኸቱን ባትሰሙትና፣ባትፈርዱለት የሰማይ አባታቸው ቸሩ አምላክ ግን እንኳን ወደ እርሱ ጮኸው ለምነውት ቀርቶ ያልለመኑትንና ያልጠየቁትን
ሳይለምኑትና ሳይጠይቁት ይሰማቸዋል፣
ይሰጣቸዋል፣ይፈርድላቸዋል።

ክቡር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለ ማርያም፥
ክቡራን የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለ ሥልጣናትና ኃላፊዎች በሙሉ፥
እስከ ዛሬ ድረስ ለሃያ አምስት ዓመታት እኛ ብቻ ነን የምንናገረው፣እኛ ብቻ ነን የምናውቅላችሁ ብላችሁ ስትናገሩልንና፣ስታውቁልን እውቀታችሁንም፣ንግግራችሁንም ሰምተናል፣ተቀብለናል።ዛሬ ደግሞ የእኛ ተራ ነው።እናንተም ስሙን።ስለ እናንተ እናውቅላችኋለን አድምጡን።
እግዚአብሔርን በማመን የሚሠሩት ሥራ ይባረካል፣ ይቀደሳል።
እግዚአብሔር በማመን የሚጓዙት መንገድ ቀና ነው።
እግዚአብሔርን በማመን ለሚቀርቡት ይቀርባልና እመኑበት።
እግዚአብሔርን በማመን የሚመሩት ሕዝብ
ታዛዥ ይሆናል።
ስለዚህ እስቲ እናንተ ደግሞ ዛሬ ላለፈው ጊዜና ዘመን በሕዝብ ላይ ለሠራችሁት በደልና ግፍ ምህረቱ ይደረግላችሁ ዘንድ ከልባችሁ ቸሩ እግዚአብሔርን በነገሮች ሁሉ ጠይቁት።ንስሐ ጠማማውን ያቀናል፣ኃጥኡን ጻድቅ፣ክፉውን መልካም፣
 መልካም አስተዳደርን፣ቅን ፍርድንና ሰላማዊ ሕይወትን ለሕዝቡና ለአገሩ ያጎናፅፍላችኋል። ለዚህ ሁሉ ጥፋት ጉስቁልና የመሪዎች ከእግዚአብሔር ሕግና መግቦቱ መራቅና ከእርሱ ጋር ያይደለ ድካም ለብቻቸው በክፉ መንፈስ ኃይል ስለሚድክሙ ጭምር ነው።
ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝሙሩ
መዝ፦፻፳፮፥፩-፫
"እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ
ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ፤
እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ
ጠባቂ በከንቱ ይተጋል፤
በማለዳ መግሥገሣችሁም ከንቱ ነው...."
ይላልና እናንተ መሪዎች ቸሩ አምላካችን በነገሮች ሁሉ ተጨምሮ ለአገሪቱና ለሕዝቡ ሥልጣናችሁን በማስረከብ መልካም አስተዳደርን የምታመጡበትን የንስሐ ዘመንን ይሰጣችሁ ዘንድ አምላኬን እለምነዋለሁ።ለዚህም ቅን ልቡናን፣ አስተዋይ አእምሮን፣እግዚአብሔርን የምትፈሩበትን፣ሰውንም የምታከብሩበት ሕሊናን ይስጣችሁ።አሜን።

ቅዱስ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር.
ተፃፈ
በቀሲስ አሸናፊ ዱጋ ዋቄ።

Saturday, September 17, 2016

ለምናምንቴ እረኛ ወየውለት!

ሕዝቅኤል 34
"የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ በእስራኤል እረኞች ላይ ትንቢት ተናገር፥ እረኞችንም እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ራሳቸውን ለሚያሰማሩ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች በጎችን ያሰማሩ ዘንድ አይገባቸውምን? ጮማውን ትበላላችሁ ጠጕሩንም ትለብሳላችሁ፥ የወፈሩትን ታርዳላችሁ፤ በጎቹን ግን አታሰማሩም። የደከመውን አላጸናችሁትም የታመመውንም አላከማችሁትም የተሰበረውንም አልጠገናችሁትም የባዘነውንም አልመለሳችሁትም የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም በኃይልና በጭቈናም ገዛችኋቸው።እረኛንም በማጣት ተበተኑ፥ ለምድርም አራዊት ሁሉ መብል ሆኑ፥ ተበተኑም። በጎቼ በተራሮች ሁሉና በረዘሙ ኮረብቶች ሁሉ ላይ ተቅበዝብዘዋል፥ በጎቼም በምድር ፊት ሁሉ ላይ ተበትነዋል፤ የሚሻም የሚፈልግም አልነበረም። ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና እረኛ ስለሌለ እረኞቼም በጎቼን ስላልፈለጉ እረኞችም ራሳቸውን እንጂ በጎቼን ስላላሰማሩ፥ በጎቼ ንጥቂያ ሆነዋልና፥ በጎቼም ለምድር አራዊት ሁሉ መብል ሆነዋልና"



Monday, September 12, 2016

ኦርቶዶክስ ሆይ ድምፅሽ ወዴት አለ?


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የወቅቱን የሀገሪቱን ቀውስ ከጸሎት ባሻገር በመምከርና በመገሰጽ ወደሰላማዊና የተረጋጋ ሁኔታ በመመለስ ረገድ ልትጫወተው የምትችለው ድርሻ ትልቅ እንደሆነ ይገመታል። ነገር ግን "መጽሐፉም ዝም፣ ቄሱም ዝም" እንዲሉ ሆነና እያየች እንዳላየች፣ እየሰማች እንዳልሰማች መሆንን የመረጠችው ለምን ይሆን?
ከሰማያዊው መንግሥት  ምድራዊውመንግሥት አስፈርቷት ነው? ወይስ ዝም እንድትል ከሰማያዊው መንግሥት መልእክት መጥቶላት ይሆን?
ቤተ ክርስቲያን ማእከላዊ ሆና ቤተ መንግሥቱንም፣ ሕዝቡንም ልትገስጽ፣ ልትመክር ካልቻለች ወደምድራዊ ውግንና ወይም ሥጋዊ ፍርሃት ገብታለች ማለት ነው። የተሰጣትን እውነት የመናገር ብርሃናዊውን መቅረጽ የምትቀማው መናገር ሲገባት ዝምታን ከመረጠችና ዝምታ በሚገባት ሰዓት መናገር ከፈለገች ብቻ ነው። እናም ዝምታዋ ዞሮ ዞሮ የተሰጣትን መንፈሳዊ ሃብት እንድትቀማ ያደርጋታል። ለሌላው አሳልፎ እንዲሰጥ ይሆናል። ለልክ እንደጥንታዊዋ የኤፌሶን ቤተክርስቲያን ማለት ነው። ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ሳይፈጸም አይቀርም። ደግሞም እያየን ያለንበት ወቅት ላይ ነን።
መንግሥት ሆይ፣ ሕዝብህን በሕግና በፍርሃት ግዛ። ሕዝብ ሆይ፣ ለመንግሥትህ በሕግና በፍርሃት ተገዛ ማለት የእርቅ አንደበት እንጂ ለማንም መወገን አይደለም። ምን ጊዜም ብጥብጥና ሁከት ለሕግና ለተአዝዞት ፈቃደኛ ካለመሆን የሚመጣ ስለሆነ የትኛውም አካል ለሕግ ተገዢ ይሁን ብሎ መናገር የሚያስፈራ ጉዳይ አልነበረም። ገዳይም፣ ሟችም፣ ሕግ አፍራሽም፣ ሕግ ደንጋጊም ሁሉንም እንደ ልጆቿ አድርጋ በማየት ለሕግ ተገዙ ልትል ሲገባት የኦርቶዶክስን አንደበት ሌሎች እየተናገሩበት ይገኛል። ልጆቿን ልጆቻቸው አድርገው አንደበቷን ወስደው እየተናገሩበት ይገኛሉ። ይሄ መነሳት የነበረበት ከእርሷ ቢሆንም የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጎዶሎ ወንጌል የሌላት ሆኖ ሳለ የወንጌል ሙሉ ነን የሚሉ ቀድመው የአስታራቂነት ሽምግልናውን ወስደዋል። ለመሆኑ የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ በሕይወት አለህ?




Thursday, September 8, 2016

"ሳይቃጠል በቅጠል"




by ኢትዮ - አፖሎጂስት

አክራሪ እስልምና አፋጣኝ መፍትሄ ይሻል

ይህ ጊዜ ዓለማችን በከፍተኛ ሁኔታ እየተናጠችና እየታመሰች ያለችበት ጊዜ ነው፡፡ ሰላሟን እያናጉ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ቢኖሩም አብይ መንስኤው ግን ለሰው ልጆች ሰላምና ደህንነት እንደቆመ የሚሰብከው የእስልምና ሃይማኖት መሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡ በሦርያ፣ በኢራቅ፣ በየመን፣ በሊብያ፣ በናይጄሪያ፣ በሶማሊያ፣ በፓኪስታን፣ በአፍጋኒስታንና በሌሎችም ብዙ የዓለም ሃገራት የሚታዩት ሁኔታዎች ይህንኑ የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ እስልምና “የሰላም” ሃይማኖት መሆኑ በተደጋጋሚ ይነገረናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ስብከቶች ከሙስሊሞች ዘንድ ብቻ ሳይሆን ሙስሊም ካልሆኑት እና እንዲያውም የሽብር ተግባራቱ ሰለባዎች ከሆኑት ግለሰቦችና ሃገራት ዘንድ መሰማታቸው ጉዳዩን አደናጋሪ ያደርገዋል፡፡ እስልምና የሰላም ሃይማኖት ከሆነ እምነቱን አክርረው የያዙ ሙስሊሞች ስለምን እጅግ ሰላማውያን ከመሆን ይልቅ እጅግ ነውጠኞች ሆኑ? እንዲህ ዓይነት ተግባራትስ ስለምን የእምነቱ መታወቂያዎች ሆኑ? በማለት ተገቢ የሆነውን ጥያቄ የሚሰነዝሩ ወገኖች “እስላሞፎብያ” የሚል “የአዕምሮ ህመም” ስም ይለጠፍላቸዋል፡፡ እስልምና የሰላም ሃይማኖት እንዳልሆነ በድፍረት የሚናገሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ለአደጋ ያጋልጣሉ፡፡ ታዋቂ ግለሰቦች እስልምና የሰላም ሃይማኖት አለመሆኑን ሲናገሩ ከተደመጡ ፅንፈኛ ሙስሊሞች አደባባይ በመውጣት ንብረት ያወድማሉ፣ የንፁኀንን ደም ያፈስሳሉ፣ በእምነት ተቋማት ላይ ቦምብ ይጥላሉ፣ የሰላም ሃይማኖት መሆኑን ለማሳመን ሰላምን ያደፈርሳሉ፡፡ የሙስሊሞች ተግባርና ስለ እምነቱ የሚሰበከው ስብከት አራምባና ቆቦ ሆኖብን ግራ ተጋብተን ሳናበቃ እስልምና የሰላም ሃይማኖት አለመሆኑንና “ካፊሮችን” ማሸበር እስላማዊ መሆኑን የሚናገሩ ሙስሊም ሊቃውንት ይገጥሙናል፡፡ በአንድ ወቅት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊዩ ቡሽ “እስላም ሰላም ነው” በማለት መናገራቸውን ተከትሎ አቡ ቀታዳ የተሰኘ በጂሃድ የሚያምን ሙስሊም አስተማሪ የሚከተለውን ብሎ ነበር፡- “ፕሬዚዳንት ቡሽ በእስልምና ስም የሚደረገውን የጂሃድ ሽብር የሚደግፍ ምንም ዓይነት ነገር በቁርአን ውስጥ አለመኖሩን መናገሩ በእጅጉ አስገርሞኛል፡፡ ለመሆኑ እርሱ የሆነ ዓይነት የእስልምና ሊቅ ነውን? እንደው በእድሜ ዘመኑ ቁርአንን አንብቦ ያውቃልን?”[1]
ሙስሊሞች በሚበዙባቸው ሃገራት ውስጥ የሚገኙት ብዙ ሙስሊም ሊቃውንት እስልምና የሰላም ሃይማኖት አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ በምዕራብ ሃገራት እና ሃገራችንን በመሳሰሉ የሙስሊሞች ቁጥር ከአጠቃላዩ የሕዝብ ቁጥር በሚያንስባቸው ሃገራት ውስጥ የሚገኙት ደግሞ እስልምና የሰላም ሃይማኖት መሆኑን ይሰብካሉ፡፡ የፖለቲካ መሪዎቻችንና የሃይማኖት አባቶቻችንም ከእነርሱ ጋር ይስማማሉ፡፡ እውነቱ የቱ ነው? ማንን እንስማ? የቱን እንቀበል? ከዚህ ግራ መጋባት ለመውጣት እስላማዊ የሃይማኖት መጻሕፍትን ማጥናት አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡
ከፊት ለፊታችን ከባድ አደጋ የተጋረጠ ቢሆንም ብዙዎቻችን የአደጋውን ግዝፈት ማየት አለመቻላችን ወይም ለማየት አለመፈለጋችን የሚያሳዝን ነው፡፡ በአክራሪ ሙስሊሞች በዚህች ሃገር ውስጥ ለደረሱት ጉዳቶች የኛ ቸልተኝነትና ዝምታ አስተዋፅዖ ማበርከቱን መካድ አንችልም፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ነገሮች ከልክ አልፈው ሃገሪቱ ከገደሉ አፋፍ ደርሳ ከመውደቋ በፊት እግዚአብሔር መንግሥትን ባያነቃ ኖሮ መፃዒ እጣ ፋንታችን ምን ሊሆን እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን የማስታገሻ እርምጃ እንደተወሰደ እንጂ ትክክለኛ መፍትሄ እንደተሰጠ በልበ ሙሉነት መናገር አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የህመሙ ምልክት እንጂ መንስኤው አልታከመምና፤ መንስኤው እስካልታከመ ድረስ ደግሞ ጊዜ ጠብቆ መልሶ ማገርሸቱ የማይቀር ሃቅ ነው፡፡ የአክራሪነት ሥረ መሰረት በቁርአን፣ በሐዲሳትና በሌሎችም እስላማዊ ምንጮች ውስጥ ሰፍረው የሚገኙት ትምህርቶች መሆናቸውን መካድ አያዋጣንም፡፡ ሽብርተኝነት የዛፉ ፍሬ በመሆኑ ሥራ መሰራት ያለበት ከፍሬው ይልቅ በግንዱ ላይ ነው፡፡ ይህንን የተረዱት የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ ኧል-ሲሲ የዓለም ግምባር ቀደም እስላማዊ ዩኒቨርሲቲ እንደሆነ በሚነገርለት በአል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲ ሙስሊም ሊቃውንት ፊት ያደረጉት ዓለምን ያስደመመ ንግግር ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ያለ ምንም መሸፋፈን ችግሩ የሚገኘው እድሜ ጠገብ በሆኑት እስላማዊ ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ መሆኑን በማስገንዘብ በዓለም ላይ ለሚገኘው የሽብርተኝነት ችግር መፍትሄ እንዲመጣ ከተፈለገ እነዚህ ቅዱሳት መጻሕፍት መስተካከል እንዳለባቸው ጥብቅ ማሳሰብያ ሲሰጡ ተደምጠዋል፡፡ ሙስሊሞች በዓለም ላይ የሚገኙትን ሕዝቦች ሁሉ በማጥፋት እራሳቸው ብቻ ለመኖር መፈለጋቸው የሚያስከትለውን አደጋ በመጠቆም የማስጠንቀቂያ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ የሚከተለው ከንግግራቸው ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው፡-
“… እዚህ ጋ እየተናገርኩ ያለሁት የእምነት አባቶችን ነው፡፡ እየተጋፈጥን ስላለነው ነገር በአንክሮ ማሰብ ያስፈልገናል – በእርግጥ ይህንን ጉዳይ ከዚህ ቀደም አንድ ሁለት ጊዜ አንስቻለሁ፡፡ በጣም ክቡርና ቅዱስ አድርገን የያዝነው አስተሳሰብ አጠቃላይ ኡማውን [እስላማዊውን ማሕበረሰብ] ለዓለም ማሕበረሰብ የጭንቀት፣ የአደጋ፣ የግድያ እና የጥፋት ምንጭ እንዲሆን ማድረጉ የማይታመን ነው፡፡ ይህ ሊሆን አይችልም!
ያ አስተሳሰብ – “ሃይማኖት” እያልኩ አይደለም ነገር ግን “አስተሳሰቡ” – ከእርሱ ማፈንገጥ የማይቻልበት ደረጃ ላይ እስክንደርስ ድረስ ለክፍለ ዘመናት አክብረን የያዝነው የመጻሕፍትና የአስተሳሰብ ስብስብ መላውን ዓለም እየተፃረረ ይገኛል፡፡ ዓለምን በሞላ እየተፃረረ ነው!
እነዚህን ቃላት እዚህ በአል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲ፣ በዚህ የሊቃውንትና የኡላማ ጉባኤ ፊት እየተናገርኩ ነው – አሁን እየተናገርኩ ያለሁትን ነገር በተመለከተ ሁሉን ቻይ የሆነው አላህ በፍርዱ ቀን ስለ እውነተኛነታችሁ ምስክር ይሁንባችሁ፡፡
እየነገርኳችሁ ያለሁትን ይህንን ሁሉ ነገር በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ተጠምዳችሁ የምትኖሩ ከሆነ ልትረዱት አትችሉም፡፡ በትክክል መገምገም እንድትችሉና የበለጠ አብርሆት ካለው ፅንፍ ማየት ትችሉ ዘንድ ከራሳችሁ ሁኔታ መውጣት ያስፈልጋችኋል፡፡
ደግሜ ደጋግሜ እላለሁ ሃይማኖታዊ አብዮት ያስፈልገናል፡፡ እናንተ ኢማሞች በአላህ ፊት ተጠያቂዎች ናችሁ፡፡ መላው ዓለም፣ እደግመዋለሁ መላው ዓለም የእናንተን ቀጣይ እርምጃ እየተጠባበቀ ይገኛል… ምክንያቱም ይህ ኡማ እየፈረሰ ነው፣ እየወደመ ነው፣ እየጠፋ ነው – እየጠፋ ያለው ደግሞ በገዛ እጃችን ነው፡፡[2]
በዚህ ንግግር ውስጥ ፕሬዚዳንት ኧል-ሲሲ በእስላማዊ ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የተሰገሰገው የነውጠኝነት አስተሳሰብ የዓለም ስጋት ምንጭ መሆኑን በግልፅ አስረድተዋል፡፡ በዚህ ገፅ ላይ በተከታታይ ስናወጣ እንደቆየነው የሽብርተኝነት ሥረ መሰረት እስላማዊ መጻሕፍት እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ (አይ ኤስ የተሰኘው የሽብር ቡድን እየፈፀማቸው የሚገኙት የሽብር ተግባራት በእስላማዊ ምንጮች የተደገፉ መሆናቸውን ማስረጃዎችን በመጥቀስ ያሳየንበትን ጽሑፍ ለአብነት ያህል ማየት ይቻላል፡፡) ካለማወቅም ይሁን ከፖለቲካዊ ትክክለኝነት (Political Correctness) በመነጨ አስተሳሰብ እስላማዊ መጻሕፍት ሰላምን እደሚያስተምሩ በመስበክ ለእስልምና ጥብቅና ሲቆሙ የነበሩ ወገኖች ይህንን ማድረጋቸው ምንም አልፈየደም፡፡ አንድን ከሥነ ምግባር የወጣ ሰው ሥነ ምግባሩ ጥሩ እንደሆነ ደጋግሞ በመንገር ፀባዩን እንዲያርም ማድረግ እንደማይቻል ሁሉ ሽብርን የሚሰብክ ሃይማኖት ሰላምን እንደሚሰብክ በመናገር ሰላማዊ ማድረግ አይቻልም፡፡ ይልቁኑ ስህተቱን ነቅሶ በማውጣት እንዲያስተካከል መንገር እንጂ መፍረግረግና መለማመጥ አጥፊው የልብ ልብ እንዲሰማው ማድረግ ነው፡፡ እውነትን ሸሽጎ ውሸትን በመናገር ችግሩን ማፈርጠም መፍትሄ አይሆንም፡፡ የፖለቲካዊ ትክክለኝነት ንግግሮች ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጡ ይቅርና ጊዜያዊ መፍትሄ እንኳ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ የሃይማኖት አባቶችና የፖለቲካ መሪዎች የእስልምናን ሰላማዊነት አጥብቀው ቢሰብኩንም ነገር ግን ችግሮች እየተባባሱ ሄዱ እንጂ ሲቀንሱ አልታዩም፡፡ እውነትን በመናገር ሊፈጠር የሚችለውን ጊዜያዊ ችግር በመፍራት ዝንተ ዓለም በሽብር እየተናጡ ከመኖር እውነቱን አፍረጥርጦ በመናገር ዘላቂ መፍትሄ መፈለግ ይበጃል፡፡ “ጅቡ እግሬን እየበላው ነውና እንዳይሰማን ዝም በል” እንዳለው ሞኝ ሰው መሆን ይበቃናል፡፡
ማሕበረሰባችንን ከዚህ አስከፊ የጥፋት ማዕበል ለመታደግ የመጀመርያው እርምጃ መሆን የሚገባው የችግሩን ምንጭ ለመረዳት ጥረት ማድረግ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የምንጊዜም ምርጥ ሳይንቲስት የሆነው አንስታይን ዓለምን ከጥፋት ለመታደግ አንድ ሰዓት ብቻ ቢሰጠው የተሰጠውን ጊዜ እንዴት እንደሚጠቀም ተጠይቆ ሲመልስ 55 ደቂቃዎችን ችግሩን ለመረዳትና 5 ደቂቃዎችን ብቻ መፍትሄ ለማፈላለግ እንደሚጠቀም ተናግሮ እንደነበር ይነገራል፡፡ የብዙ ችግሮቻችን መፍትሄ ያለማግኘት ምክንያቱ ችግሮቹን ራሳቸውን በትክክል አለማወቃችን መሆኑ እሙን ነው፡፡ ሽብርተኝነት በህዝባችን ላይ አደጋን የደቀነ የዘመናችን ችግር መሆኑን እናውቃለን፡፡ ነገር ግን የሽብርተኝነት ምንጭ ምን እንደሆነ ስለማናውቅ የችግሩ አሳሳቢነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ሃገራችን በዙርያዋ ከሚገኙት ጎረቤቶችዋ ጋር ሊነፃፀር በማይችልበት ሁኔታ ከሽብር አደጋዎች ተጠብቃ ትገኛለች፡፡ ነገር ግን የሽብርተኝነት ምንጭ የሆነውን የእስልምናን ትምህርት በትክክል ተረድተን መፍትሄ ካላፈላለግን በስተቀር ይህ አንፃራዊ ሰላም በዚህ ሁኔታ ለመቀጠሉ ምንም ዋስትና አይኖረንም፡፡ ስለዚህ ዜጎችም ሆንን መሪዎች እስልምና ሽብርተኝነትን በተመለከተ ምን እንደሚያስተምር፣ ምን እንደሚያቅድ፣ የአፈፃፀም ስልቶቹ እንዴት እንደሆኑ፣ ወዘተ. ማጥናት ያስፈልገናል፡፡ እውቀቱ ካላቸው፣ በተለይም ደግሞ በእስልምና ትምህርቶች ከሰለጠኑና እስልምናን ለቀው ከወጡ ሰዎች መማር እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡
አክራሪ እስልምና ለዓለምም ሆነ ለሃገራችን አዲስ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ የአክራሪ እስልምናን ተግዳሮቶች ስትጋፈጥ ኖራለች፡፡ አንዳንዶች አክራሪ እስልምና ፖለቲካዊ ችግር በመሆኑ መፍትሄው ፖለቲካዊ ነው ስለዚህ ችግሩ ለመንግሥት ብቻ መተው አለበት ይላሉ፡፡ ነገር ግን፡-
መንግሥት ሥልጣንና ጉልበት ቢኖረውም የትምህርቱን ውጤት እንጂ ትምህርቱን መጋፈጥ አይቻለውም፡፡ የመንግሥት አካላት ብዙ ጊዜ በሃይማኖት ካባ ተሸፍኖ ለክፍለ ዘመናት የኖረውን አይ የእስልምናን ፖለቲካ ለመረዳት ሲቸገሩ ይስተዋላሉ፡፡ ስለዚህ ትክክለኛ መፍትሄ ለመስጠት ይቸገራሉ፡፡
የመንግሥት አካላት የነገሩን ውስጠ ሚስጥር ቢረዱትም እንኳን መንግሥት ሁሉን አቀፍ በመሆኑ ገለልተኛነትን ይመርጣሉ፡፡ ስለዚህ የችግሩ መንስኤ የሆነውን የእስልምናን መሰረት መንካት አይፈልጉም፡፡
አክራሪ እስልምና አይዲዎሎጂ በመሆኑ በጉልበት አይቀለበስም፡፡ ስለዚህ መንግሥት አክራሪ እስልምና የጦር መሳርያ ይዞ አደባባይ ሲወጣ በጦር መሳርያ ማስታገስ ቢችልም ነገር ግን ትምህርቱን የሚጋፈጥበት ሥነ መለኮታዊ መሳርያ የለውም፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት እንደታዘብነው አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይባስ ብለው ከአክራሪ እስልምና ጋር በመተባበር አጀንዳውን ሲያራግቡና ጥብቅና ሲቆሙለት ታይተዋል፡፡ ይህ የሚያመለክተው አንዳንድ ፖለቲከኞች የዛሬ ጥቅማቸውን እንጂ የነገውን አደጋ ማየት አለመፈለጋቸውን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ሥልጣን ቢይዙ ችግሩን ከማባባስ ውጪ መፍትሄ መስጠት አይችሉም፡፡
የመገናኛ ብዙኃንን ስንመለከት እንኳንስ መፍትሄ ሊሰጡ ይቅርና ጥያቄውን እንኳ በትክክል የተረዱት አይመስልም፡፡ በትክክል ቢረዱትም እንኳን ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ስለሚጫናቸው የችግሩን ስረ መሰረት በመንካት መፍትሄ ማፈላለግ አይችሉም፡፡
ምሑራን ጥያቄውን የተወሰነ ያህል ይረዱታል ነገር ግን የችግሩን ስረ መሰረት በመጥቀስ የመፍትሄ ሐሳቦችን እንዳይሰነዝሩ በፍርሃትና በፖለቲካዊ ትክክለኝነት ተሸብበዋል፡፡
አንዳንድ ለዘብተኛ አመለካከት ያላቸው ምዕራባውያን የሚከተሉትን “መፍትሄዎች” ያስቀምጣሉ፡-
ለአክራሪ ሙስሊሞች ምንም ትኩረት አለመስጠትና ችላ ማለት፡፡ ነገር ግን ችላ የሚባሉት እምን ድረስ ነው? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ሰይፍ አንገታችን ላይ ተቀምጦ ትኩረት አንሰጠውም ማለት የሞኝ መፍትሄ ነው፡፡
ባሉበት እንዲሆኑ ማገድ (ወደ ክልላችን እንዳይገቡ ማድረግ፡፡) o አሁን ካለው የሕዝቦች እንቅስቃሴና የመረጃ ቴክኖሎጂ ደረጃ አኳያ አያስኬድም፡፡ የውጪዎቹ እንዳይገቡ ማገድ ይቻል ይሆናል፣ ውስጥ የሚገኙትንስ? መግደል? ማሰር? ከሃገር ማባረር? አያዋጣም፡፡
እስልምናን ከፖለቲካዊ ይዘቱ በማፋታት ምዕራባዊ መልክ ያለውን እስልምና መፍጠር [ለምሳሌ ኪልያም (Quilliam) ፕሮጀት]፡፡[3]

Saturday, August 27, 2016

ሴቶች ሁልጊዜ ልብ በሉ!



ሴቶች ከወንድ ጓደኛ ማንን ትወዱ? ማንንስ ትመርጡ? ከማንስ ጋር ጋብቻን ትፈፅሙ? እስኪ ራሳችሁን ጠይቁ።
በራስ መተማመን ያላት ሴት ለችግሮች ራሷን አሳልፋ አትሰጥም። በሁኔታዎች መለዋወጥ አትሸበርም። ራሷን ላጋጠማት ተግዳሮት ታዘጋጃለች እንጂ በሽንፈት ለቅሶን አታስተናግድም። ታዲያ ይህንን ኃይል ከየት ማግኘት ትችላለች?
               ✔ ✔✔
መልካም ክርስቲያናዊ ቤተሰብ ውስጥ ያደገች ሴት ስነምግባርን፣ እውቀትን፣ ችሎታና በራስ መተማመንን የምታዳብረው በቅርቧ ባለው ከቤተሰቧ ነው። በአስተዳደግና በልጅነት ሕይወት ጉድለት የደረሰባት፣ በብዙ ችግሮችና መከራ ውስጥ ያለፈች ሴት በስነልቦናዋ ላይ በሚደርሰው ጉዳት በራስ መተማመኗን በማጣት ችሎታዋን ለማውጣትና ችግሮችን ለመጋፈጥ ያላትን አቅም አውጥታ ለመጠቀም ሊያዳግታት ይችላል።

 በተለይም በአስገድዶ መደፈር፣ በእናት ወይም በአባት ብቻ ወይም ከሁለቱም አሳዳጊ ውጪ ያደገች፣ የኑሮ ጫናና ድህነት፣ አካባቢያዊና ሀገራዊ ችግሮች ( ጦርነት፣ ረሃብ፣ ስደት) በሴቷ ስነልቦና ላይ የሚያደርሱት ተጽእኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በቃላትም መግለፅ ከሚቻለው በላይ የስነልቡና ተጠቂ ልትሆን ትችላለች።
 በዚህም የተነሳ ሴቶች ለአካለ መጠን ከደረሱ በኋላ ቤተሰባዊ ሕይወትን ለመመስረት በሚያስችላቸው ሁኔታ ላይ ያሳለፉት ቁስል የሚያደርስባቸው የአእምሮ ፈተናና ትግል እጅግ ውስብስብ ነው።
የመጠራጠር፣ ያለማመን፣ አንዳንዴም በቀላሉ የመታለል ወይም የመሸወድ ክስተት ሲያጋጥማቸው ያታያል። ሴቶች በፈገግታና በሳቅ ሸፍነው በማህበራዊ ኑሮው ቶሎ የመቀላቀል ተፈጥሮአዊ ችሮታ አላቸው እንጂ በኋላቸው የተሸከሙት ህመም በጣም ብዙ ነው። ሲስቁና ሲጫወቱ ዘመናቸውን ሁሉ እድለኞች የነበሩ ሊመስለን ይችላል። እውነቱ ግን እሱ አይደሉም። ሴቶች መከራቸውን እንደወንድ እያመነዠኩ ስለማይኖሩ ከሰው ለመቀላቀል ብዙም አይቸገሩም። ያ ደግሞ ሴትን ልዩ ፍጥረትና የተወደደች ያደርጋታል። ሴት ለወንድ ሚስት ብቻ ሳትሆን የጉድለቱ ሙላት የመሆኗም ምስጢር ሁሉን መከራ መሸከም መቻሏ ነው። 6 ልጆቿን ያለአባት አሳድጋ ለቁምነገር ያበቃች እናት አውቃለሁ።
                ✔✔✔
ክርስቲያን ሴቶች ምንም እንኳን ያለፈ ሕይወታቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ባለ አዲስ የእምነት ልምምድ የተለወጠ ቢሆንም ያሳለፉት ስነልቦና በቀላሉ የሚፋቅ ባለመሆኑ አልፎ አልፎ መቸገራቸው አይቀርም። ከጋብቻ በፊት የመንፈሳዊ ጋብቻ ትምህርትና የምክር አገልግሎት ማግኘት የበለጠ ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው ስለሚችል በዚሁ መልኩ አስቀድመው ቢገለገሉ የተሻለ ግንዛቤ ይኖራቸዋል።
በኛ በኩል ያሉንን ምክሮች ጥቂት እንበል።
               ✔✔✔
ባለፈ ስህተትሽ አትቆጪ። የዛሬውን ሃሳብሽን እንዲቆጣጠረውም አትፍቀጂ። ያለፈው ላይመለስ አልፏል። ያለፈው ለዛሬው ያለው እድል አስተማሪ መሆኑ ብቻ ነው። ጎበዝ ሰው በሌላ ሰው ስህተት ይማራል፣ ሰነፍ ሰው ደግሞ ከራሱ ስህተት ይማራል። ያለፈው ስህተትሽ ለዛሬው ማንነትሽ ትምህርት ከሆነሽ፣ አንቺ የዛሬዋ ጎበዝ ነሽ። ካለፈችው ሰነፏ አንቺነትሽ በልጠሻል ማለት ነው። ስህተት አንዴ ከበዛ ደግሞ ሁለቴ ቢሆን ነው። ከደጋገመሽ ግን ስህተቱ ከጎዳሽ ነገር ሳይሆን ካንቺ አለመለወጥ የመጣ ነው።
ፈረንጆች እንዲህ የሚል አባባል አላቸው። "ስትሄድ የመታህ የድንጋይ እንቅፋት ስትመለስም ከደገመህ ስህተቱ የእንቅፋቱ ሳይሆን ድንጋዩ አንተው ነህ" ይላሉ።
ፍርሃትን በራስ መተማመን፣ ስህተትሽን በመታረም ማሸነፍ ትችያለሽ።
አብዛኛው ወንድ ሴትን የሚወደው በአይኑ ነው። የውስጧን ማንነት ሳያይ ውጫዊውን አይቶ ማድነቅም፣ መውደድም ይቻላል። ብቻውን ግን ለፍቅር ግንኙነት አያበቃም።
 የደም አይነት ልዩ ልዩ ነው። ሁሉም ደም ለሁሉም ሰው አይሆንም። በአይን የመጣ መውደድም በሁሉም ሴት ላይ ፍቅርን ሊመሰርት አይችልም። ለምርጫ የሚያበቃ ጥናት ያስፈልገዋል። የወደዱን ሁሉ ያፈቅሩናል ማለት አይደለም። ይህን ለማወቅ ጊዜ ወስዶ ማጥናት ተገቢ ነው። ለኛ የተሰጠ ሰው ከሆነ ለማጥናት በምንወስደው ጊዜ ያመልጠናል ብለን መስጋት አይገባም። እንዲያውም ሳናውቀው ዘው ከምንል ቢያመልጠን ይሻላል። ለኛ የተሰጠን እንዳይዘገይ ቶሎ መሄዱ ይሻላል። የከረመ ወይን ሲጠጡት ሆድ አይነፋም።

በአይን የወደደ የአይኑን አምሮት በአካል ባገኘው ጊዜ ቶሎ ይረካል። ከዚያም የማያርፈው አይኑ ወደሌላ ይሄዳል። ሴት ሆይ፣ የሚወድሽን ወንድ አይኑን ብቻ ሳይሆን ልቡን እዪው። ምን ይልሻል? ስሚው። አንቺን አይቶ ለልቡ አምሮት የሚቅበዘበዝ ከሆነ ችግር አለ። በአፉ እወድሻለሁ እያለ ፍቅሩን በተግባር የማያሳይ ከሆነ ችግር አለ። እንጋባ ሳይሆን እስክንጋባ አልጋ ላይ እንውጣ የሚልሽ ከሆነ ችግር አለ። የሚሰጥሽን ጊዜ ቀስ በቀስ የሚቀንስ ከሆነ ችግር አለ።
ታማኝ ወንዶችን ከአስመሳዮች ለመለየት ጊዜ ውሰጂ። አትቸኩዪ። በምላስ ብልጠት አትሸነፊ። ልቡን ለማወቅ አንቺ አምላክ አይደለሽም። ምላሱን በተግባሩ ፈትኚ። ከትዳር በፊት የተደጋገመ ውሸት በትዳር ውስጥም ይቀጥላልና ተጠንቀቂ።
በሰውኛ ሚዛን መልክና ውበት ጥሩ ነው። ነገር ግን ለእግዚአብሔር መንግስት በተመረጠ ትዳር ውስጥ ሁሉም ከንቱ ነው። ቅን እንጂ ቅንቅን አትሁኚ። ገንዘብ፣ ጌጥና ምቾት አያታልሽ። ዝሙት ኃጢአት ነው። ፍፃሜውም ሞት ነው። ስለዚህ በታማኝነት ለእግዚአብሔር መንግስት ራስሽን አስገዢ።

 ጠቢቡ በመጽሐፉ እንዳለው መክብብ 6፣12
"ሰው በከንቱ ወራቱ ቍጥርና እንደ ጥላ በሚያሳልፈው ዘመኑ በሕይወቱ ሳለ ለሰው የሚሻለውን የሚያውቅ ማነው? ወይስ ለሰው ከፀሐይ በታች ከእርሱ በኋላ የሚሆነውን ማን ይነግረዋል?" ነውና ለጊዜው ለእግዚአብሔር ክብር ለሚሆን ሕይወት እንጂ ይህ ቋሚ መኖሪያችን አይደለምና ራስን መግዛት አትርሺ።
             ✔✔✔
"ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ"
ፊልጵ 4:6