Saturday, September 17, 2016

ለምናምንቴ እረኛ ወየውለት!

ሕዝቅኤል 34
"የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ በእስራኤል እረኞች ላይ ትንቢት ተናገር፥ እረኞችንም እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ራሳቸውን ለሚያሰማሩ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች በጎችን ያሰማሩ ዘንድ አይገባቸውምን? ጮማውን ትበላላችሁ ጠጕሩንም ትለብሳላችሁ፥ የወፈሩትን ታርዳላችሁ፤ በጎቹን ግን አታሰማሩም። የደከመውን አላጸናችሁትም የታመመውንም አላከማችሁትም የተሰበረውንም አልጠገናችሁትም የባዘነውንም አልመለሳችሁትም የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም በኃይልና በጭቈናም ገዛችኋቸው።እረኛንም በማጣት ተበተኑ፥ ለምድርም አራዊት ሁሉ መብል ሆኑ፥ ተበተኑም። በጎቼ በተራሮች ሁሉና በረዘሙ ኮረብቶች ሁሉ ላይ ተቅበዝብዘዋል፥ በጎቼም በምድር ፊት ሁሉ ላይ ተበትነዋል፤ የሚሻም የሚፈልግም አልነበረም። ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና እረኛ ስለሌለ እረኞቼም በጎቼን ስላልፈለጉ እረኞችም ራሳቸውን እንጂ በጎቼን ስላላሰማሩ፥ በጎቼ ንጥቂያ ሆነዋልና፥ በጎቼም ለምድር አራዊት ሁሉ መብል ሆነዋልና"



Monday, September 12, 2016

ኦርቶዶክስ ሆይ ድምፅሽ ወዴት አለ?


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የወቅቱን የሀገሪቱን ቀውስ ከጸሎት ባሻገር በመምከርና በመገሰጽ ወደሰላማዊና የተረጋጋ ሁኔታ በመመለስ ረገድ ልትጫወተው የምትችለው ድርሻ ትልቅ እንደሆነ ይገመታል። ነገር ግን "መጽሐፉም ዝም፣ ቄሱም ዝም" እንዲሉ ሆነና እያየች እንዳላየች፣ እየሰማች እንዳልሰማች መሆንን የመረጠችው ለምን ይሆን?
ከሰማያዊው መንግሥት  ምድራዊውመንግሥት አስፈርቷት ነው? ወይስ ዝም እንድትል ከሰማያዊው መንግሥት መልእክት መጥቶላት ይሆን?
ቤተ ክርስቲያን ማእከላዊ ሆና ቤተ መንግሥቱንም፣ ሕዝቡንም ልትገስጽ፣ ልትመክር ካልቻለች ወደምድራዊ ውግንና ወይም ሥጋዊ ፍርሃት ገብታለች ማለት ነው። የተሰጣትን እውነት የመናገር ብርሃናዊውን መቅረጽ የምትቀማው መናገር ሲገባት ዝምታን ከመረጠችና ዝምታ በሚገባት ሰዓት መናገር ከፈለገች ብቻ ነው። እናም ዝምታዋ ዞሮ ዞሮ የተሰጣትን መንፈሳዊ ሃብት እንድትቀማ ያደርጋታል። ለሌላው አሳልፎ እንዲሰጥ ይሆናል። ለልክ እንደጥንታዊዋ የኤፌሶን ቤተክርስቲያን ማለት ነው። ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ሳይፈጸም አይቀርም። ደግሞም እያየን ያለንበት ወቅት ላይ ነን።
መንግሥት ሆይ፣ ሕዝብህን በሕግና በፍርሃት ግዛ። ሕዝብ ሆይ፣ ለመንግሥትህ በሕግና በፍርሃት ተገዛ ማለት የእርቅ አንደበት እንጂ ለማንም መወገን አይደለም። ምን ጊዜም ብጥብጥና ሁከት ለሕግና ለተአዝዞት ፈቃደኛ ካለመሆን የሚመጣ ስለሆነ የትኛውም አካል ለሕግ ተገዢ ይሁን ብሎ መናገር የሚያስፈራ ጉዳይ አልነበረም። ገዳይም፣ ሟችም፣ ሕግ አፍራሽም፣ ሕግ ደንጋጊም ሁሉንም እንደ ልጆቿ አድርጋ በማየት ለሕግ ተገዙ ልትል ሲገባት የኦርቶዶክስን አንደበት ሌሎች እየተናገሩበት ይገኛል። ልጆቿን ልጆቻቸው አድርገው አንደበቷን ወስደው እየተናገሩበት ይገኛሉ። ይሄ መነሳት የነበረበት ከእርሷ ቢሆንም የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጎዶሎ ወንጌል የሌላት ሆኖ ሳለ የወንጌል ሙሉ ነን የሚሉ ቀድመው የአስታራቂነት ሽምግልናውን ወስደዋል። ለመሆኑ የሀገር ቤቱ ሲኖዶስ በሕይወት አለህ?




Thursday, September 8, 2016

"ሳይቃጠል በቅጠል"




by ኢትዮ - አፖሎጂስት

አክራሪ እስልምና አፋጣኝ መፍትሄ ይሻል

ይህ ጊዜ ዓለማችን በከፍተኛ ሁኔታ እየተናጠችና እየታመሰች ያለችበት ጊዜ ነው፡፡ ሰላሟን እያናጉ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ቢኖሩም አብይ መንስኤው ግን ለሰው ልጆች ሰላምና ደህንነት እንደቆመ የሚሰብከው የእስልምና ሃይማኖት መሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡ በሦርያ፣ በኢራቅ፣ በየመን፣ በሊብያ፣ በናይጄሪያ፣ በሶማሊያ፣ በፓኪስታን፣ በአፍጋኒስታንና በሌሎችም ብዙ የዓለም ሃገራት የሚታዩት ሁኔታዎች ይህንኑ የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ እስልምና “የሰላም” ሃይማኖት መሆኑ በተደጋጋሚ ይነገረናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ስብከቶች ከሙስሊሞች ዘንድ ብቻ ሳይሆን ሙስሊም ካልሆኑት እና እንዲያውም የሽብር ተግባራቱ ሰለባዎች ከሆኑት ግለሰቦችና ሃገራት ዘንድ መሰማታቸው ጉዳዩን አደናጋሪ ያደርገዋል፡፡ እስልምና የሰላም ሃይማኖት ከሆነ እምነቱን አክርረው የያዙ ሙስሊሞች ስለምን እጅግ ሰላማውያን ከመሆን ይልቅ እጅግ ነውጠኞች ሆኑ? እንዲህ ዓይነት ተግባራትስ ስለምን የእምነቱ መታወቂያዎች ሆኑ? በማለት ተገቢ የሆነውን ጥያቄ የሚሰነዝሩ ወገኖች “እስላሞፎብያ” የሚል “የአዕምሮ ህመም” ስም ይለጠፍላቸዋል፡፡ እስልምና የሰላም ሃይማኖት እንዳልሆነ በድፍረት የሚናገሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ለአደጋ ያጋልጣሉ፡፡ ታዋቂ ግለሰቦች እስልምና የሰላም ሃይማኖት አለመሆኑን ሲናገሩ ከተደመጡ ፅንፈኛ ሙስሊሞች አደባባይ በመውጣት ንብረት ያወድማሉ፣ የንፁኀንን ደም ያፈስሳሉ፣ በእምነት ተቋማት ላይ ቦምብ ይጥላሉ፣ የሰላም ሃይማኖት መሆኑን ለማሳመን ሰላምን ያደፈርሳሉ፡፡ የሙስሊሞች ተግባርና ስለ እምነቱ የሚሰበከው ስብከት አራምባና ቆቦ ሆኖብን ግራ ተጋብተን ሳናበቃ እስልምና የሰላም ሃይማኖት አለመሆኑንና “ካፊሮችን” ማሸበር እስላማዊ መሆኑን የሚናገሩ ሙስሊም ሊቃውንት ይገጥሙናል፡፡ በአንድ ወቅት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊዩ ቡሽ “እስላም ሰላም ነው” በማለት መናገራቸውን ተከትሎ አቡ ቀታዳ የተሰኘ በጂሃድ የሚያምን ሙስሊም አስተማሪ የሚከተለውን ብሎ ነበር፡- “ፕሬዚዳንት ቡሽ በእስልምና ስም የሚደረገውን የጂሃድ ሽብር የሚደግፍ ምንም ዓይነት ነገር በቁርአን ውስጥ አለመኖሩን መናገሩ በእጅጉ አስገርሞኛል፡፡ ለመሆኑ እርሱ የሆነ ዓይነት የእስልምና ሊቅ ነውን? እንደው በእድሜ ዘመኑ ቁርአንን አንብቦ ያውቃልን?”[1]
ሙስሊሞች በሚበዙባቸው ሃገራት ውስጥ የሚገኙት ብዙ ሙስሊም ሊቃውንት እስልምና የሰላም ሃይማኖት አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ በምዕራብ ሃገራት እና ሃገራችንን በመሳሰሉ የሙስሊሞች ቁጥር ከአጠቃላዩ የሕዝብ ቁጥር በሚያንስባቸው ሃገራት ውስጥ የሚገኙት ደግሞ እስልምና የሰላም ሃይማኖት መሆኑን ይሰብካሉ፡፡ የፖለቲካ መሪዎቻችንና የሃይማኖት አባቶቻችንም ከእነርሱ ጋር ይስማማሉ፡፡ እውነቱ የቱ ነው? ማንን እንስማ? የቱን እንቀበል? ከዚህ ግራ መጋባት ለመውጣት እስላማዊ የሃይማኖት መጻሕፍትን ማጥናት አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡
ከፊት ለፊታችን ከባድ አደጋ የተጋረጠ ቢሆንም ብዙዎቻችን የአደጋውን ግዝፈት ማየት አለመቻላችን ወይም ለማየት አለመፈለጋችን የሚያሳዝን ነው፡፡ በአክራሪ ሙስሊሞች በዚህች ሃገር ውስጥ ለደረሱት ጉዳቶች የኛ ቸልተኝነትና ዝምታ አስተዋፅዖ ማበርከቱን መካድ አንችልም፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ነገሮች ከልክ አልፈው ሃገሪቱ ከገደሉ አፋፍ ደርሳ ከመውደቋ በፊት እግዚአብሔር መንግሥትን ባያነቃ ኖሮ መፃዒ እጣ ፋንታችን ምን ሊሆን እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን የማስታገሻ እርምጃ እንደተወሰደ እንጂ ትክክለኛ መፍትሄ እንደተሰጠ በልበ ሙሉነት መናገር አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የህመሙ ምልክት እንጂ መንስኤው አልታከመምና፤ መንስኤው እስካልታከመ ድረስ ደግሞ ጊዜ ጠብቆ መልሶ ማገርሸቱ የማይቀር ሃቅ ነው፡፡ የአክራሪነት ሥረ መሰረት በቁርአን፣ በሐዲሳትና በሌሎችም እስላማዊ ምንጮች ውስጥ ሰፍረው የሚገኙት ትምህርቶች መሆናቸውን መካድ አያዋጣንም፡፡ ሽብርተኝነት የዛፉ ፍሬ በመሆኑ ሥራ መሰራት ያለበት ከፍሬው ይልቅ በግንዱ ላይ ነው፡፡ ይህንን የተረዱት የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ ኧል-ሲሲ የዓለም ግምባር ቀደም እስላማዊ ዩኒቨርሲቲ እንደሆነ በሚነገርለት በአል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲ ሙስሊም ሊቃውንት ፊት ያደረጉት ዓለምን ያስደመመ ንግግር ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ያለ ምንም መሸፋፈን ችግሩ የሚገኘው እድሜ ጠገብ በሆኑት እስላማዊ ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ መሆኑን በማስገንዘብ በዓለም ላይ ለሚገኘው የሽብርተኝነት ችግር መፍትሄ እንዲመጣ ከተፈለገ እነዚህ ቅዱሳት መጻሕፍት መስተካከል እንዳለባቸው ጥብቅ ማሳሰብያ ሲሰጡ ተደምጠዋል፡፡ ሙስሊሞች በዓለም ላይ የሚገኙትን ሕዝቦች ሁሉ በማጥፋት እራሳቸው ብቻ ለመኖር መፈለጋቸው የሚያስከትለውን አደጋ በመጠቆም የማስጠንቀቂያ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ የሚከተለው ከንግግራቸው ተቀንጭቦ የተወሰደ ነው፡-
“… እዚህ ጋ እየተናገርኩ ያለሁት የእምነት አባቶችን ነው፡፡ እየተጋፈጥን ስላለነው ነገር በአንክሮ ማሰብ ያስፈልገናል – በእርግጥ ይህንን ጉዳይ ከዚህ ቀደም አንድ ሁለት ጊዜ አንስቻለሁ፡፡ በጣም ክቡርና ቅዱስ አድርገን የያዝነው አስተሳሰብ አጠቃላይ ኡማውን [እስላማዊውን ማሕበረሰብ] ለዓለም ማሕበረሰብ የጭንቀት፣ የአደጋ፣ የግድያ እና የጥፋት ምንጭ እንዲሆን ማድረጉ የማይታመን ነው፡፡ ይህ ሊሆን አይችልም!
ያ አስተሳሰብ – “ሃይማኖት” እያልኩ አይደለም ነገር ግን “አስተሳሰቡ” – ከእርሱ ማፈንገጥ የማይቻልበት ደረጃ ላይ እስክንደርስ ድረስ ለክፍለ ዘመናት አክብረን የያዝነው የመጻሕፍትና የአስተሳሰብ ስብስብ መላውን ዓለም እየተፃረረ ይገኛል፡፡ ዓለምን በሞላ እየተፃረረ ነው!
እነዚህን ቃላት እዚህ በአል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲ፣ በዚህ የሊቃውንትና የኡላማ ጉባኤ ፊት እየተናገርኩ ነው – አሁን እየተናገርኩ ያለሁትን ነገር በተመለከተ ሁሉን ቻይ የሆነው አላህ በፍርዱ ቀን ስለ እውነተኛነታችሁ ምስክር ይሁንባችሁ፡፡
እየነገርኳችሁ ያለሁትን ይህንን ሁሉ ነገር በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ ተጠምዳችሁ የምትኖሩ ከሆነ ልትረዱት አትችሉም፡፡ በትክክል መገምገም እንድትችሉና የበለጠ አብርሆት ካለው ፅንፍ ማየት ትችሉ ዘንድ ከራሳችሁ ሁኔታ መውጣት ያስፈልጋችኋል፡፡
ደግሜ ደጋግሜ እላለሁ ሃይማኖታዊ አብዮት ያስፈልገናል፡፡ እናንተ ኢማሞች በአላህ ፊት ተጠያቂዎች ናችሁ፡፡ መላው ዓለም፣ እደግመዋለሁ መላው ዓለም የእናንተን ቀጣይ እርምጃ እየተጠባበቀ ይገኛል… ምክንያቱም ይህ ኡማ እየፈረሰ ነው፣ እየወደመ ነው፣ እየጠፋ ነው – እየጠፋ ያለው ደግሞ በገዛ እጃችን ነው፡፡[2]
በዚህ ንግግር ውስጥ ፕሬዚዳንት ኧል-ሲሲ በእስላማዊ ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የተሰገሰገው የነውጠኝነት አስተሳሰብ የዓለም ስጋት ምንጭ መሆኑን በግልፅ አስረድተዋል፡፡ በዚህ ገፅ ላይ በተከታታይ ስናወጣ እንደቆየነው የሽብርተኝነት ሥረ መሰረት እስላማዊ መጻሕፍት እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ (አይ ኤስ የተሰኘው የሽብር ቡድን እየፈፀማቸው የሚገኙት የሽብር ተግባራት በእስላማዊ ምንጮች የተደገፉ መሆናቸውን ማስረጃዎችን በመጥቀስ ያሳየንበትን ጽሑፍ ለአብነት ያህል ማየት ይቻላል፡፡) ካለማወቅም ይሁን ከፖለቲካዊ ትክክለኝነት (Political Correctness) በመነጨ አስተሳሰብ እስላማዊ መጻሕፍት ሰላምን እደሚያስተምሩ በመስበክ ለእስልምና ጥብቅና ሲቆሙ የነበሩ ወገኖች ይህንን ማድረጋቸው ምንም አልፈየደም፡፡ አንድን ከሥነ ምግባር የወጣ ሰው ሥነ ምግባሩ ጥሩ እንደሆነ ደጋግሞ በመንገር ፀባዩን እንዲያርም ማድረግ እንደማይቻል ሁሉ ሽብርን የሚሰብክ ሃይማኖት ሰላምን እንደሚሰብክ በመናገር ሰላማዊ ማድረግ አይቻልም፡፡ ይልቁኑ ስህተቱን ነቅሶ በማውጣት እንዲያስተካከል መንገር እንጂ መፍረግረግና መለማመጥ አጥፊው የልብ ልብ እንዲሰማው ማድረግ ነው፡፡ እውነትን ሸሽጎ ውሸትን በመናገር ችግሩን ማፈርጠም መፍትሄ አይሆንም፡፡ የፖለቲካዊ ትክክለኝነት ንግግሮች ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጡ ይቅርና ጊዜያዊ መፍትሄ እንኳ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ የሃይማኖት አባቶችና የፖለቲካ መሪዎች የእስልምናን ሰላማዊነት አጥብቀው ቢሰብኩንም ነገር ግን ችግሮች እየተባባሱ ሄዱ እንጂ ሲቀንሱ አልታዩም፡፡ እውነትን በመናገር ሊፈጠር የሚችለውን ጊዜያዊ ችግር በመፍራት ዝንተ ዓለም በሽብር እየተናጡ ከመኖር እውነቱን አፍረጥርጦ በመናገር ዘላቂ መፍትሄ መፈለግ ይበጃል፡፡ “ጅቡ እግሬን እየበላው ነውና እንዳይሰማን ዝም በል” እንዳለው ሞኝ ሰው መሆን ይበቃናል፡፡
ማሕበረሰባችንን ከዚህ አስከፊ የጥፋት ማዕበል ለመታደግ የመጀመርያው እርምጃ መሆን የሚገባው የችግሩን ምንጭ ለመረዳት ጥረት ማድረግ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የምንጊዜም ምርጥ ሳይንቲስት የሆነው አንስታይን ዓለምን ከጥፋት ለመታደግ አንድ ሰዓት ብቻ ቢሰጠው የተሰጠውን ጊዜ እንዴት እንደሚጠቀም ተጠይቆ ሲመልስ 55 ደቂቃዎችን ችግሩን ለመረዳትና 5 ደቂቃዎችን ብቻ መፍትሄ ለማፈላለግ እንደሚጠቀም ተናግሮ እንደነበር ይነገራል፡፡ የብዙ ችግሮቻችን መፍትሄ ያለማግኘት ምክንያቱ ችግሮቹን ራሳቸውን በትክክል አለማወቃችን መሆኑ እሙን ነው፡፡ ሽብርተኝነት በህዝባችን ላይ አደጋን የደቀነ የዘመናችን ችግር መሆኑን እናውቃለን፡፡ ነገር ግን የሽብርተኝነት ምንጭ ምን እንደሆነ ስለማናውቅ የችግሩ አሳሳቢነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ሃገራችን በዙርያዋ ከሚገኙት ጎረቤቶችዋ ጋር ሊነፃፀር በማይችልበት ሁኔታ ከሽብር አደጋዎች ተጠብቃ ትገኛለች፡፡ ነገር ግን የሽብርተኝነት ምንጭ የሆነውን የእስልምናን ትምህርት በትክክል ተረድተን መፍትሄ ካላፈላለግን በስተቀር ይህ አንፃራዊ ሰላም በዚህ ሁኔታ ለመቀጠሉ ምንም ዋስትና አይኖረንም፡፡ ስለዚህ ዜጎችም ሆንን መሪዎች እስልምና ሽብርተኝነትን በተመለከተ ምን እንደሚያስተምር፣ ምን እንደሚያቅድ፣ የአፈፃፀም ስልቶቹ እንዴት እንደሆኑ፣ ወዘተ. ማጥናት ያስፈልገናል፡፡ እውቀቱ ካላቸው፣ በተለይም ደግሞ በእስልምና ትምህርቶች ከሰለጠኑና እስልምናን ለቀው ከወጡ ሰዎች መማር እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡
አክራሪ እስልምና ለዓለምም ሆነ ለሃገራችን አዲስ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በየዘመናቱ የአክራሪ እስልምናን ተግዳሮቶች ስትጋፈጥ ኖራለች፡፡ አንዳንዶች አክራሪ እስልምና ፖለቲካዊ ችግር በመሆኑ መፍትሄው ፖለቲካዊ ነው ስለዚህ ችግሩ ለመንግሥት ብቻ መተው አለበት ይላሉ፡፡ ነገር ግን፡-
መንግሥት ሥልጣንና ጉልበት ቢኖረውም የትምህርቱን ውጤት እንጂ ትምህርቱን መጋፈጥ አይቻለውም፡፡ የመንግሥት አካላት ብዙ ጊዜ በሃይማኖት ካባ ተሸፍኖ ለክፍለ ዘመናት የኖረውን አይ የእስልምናን ፖለቲካ ለመረዳት ሲቸገሩ ይስተዋላሉ፡፡ ስለዚህ ትክክለኛ መፍትሄ ለመስጠት ይቸገራሉ፡፡
የመንግሥት አካላት የነገሩን ውስጠ ሚስጥር ቢረዱትም እንኳን መንግሥት ሁሉን አቀፍ በመሆኑ ገለልተኛነትን ይመርጣሉ፡፡ ስለዚህ የችግሩ መንስኤ የሆነውን የእስልምናን መሰረት መንካት አይፈልጉም፡፡
አክራሪ እስልምና አይዲዎሎጂ በመሆኑ በጉልበት አይቀለበስም፡፡ ስለዚህ መንግሥት አክራሪ እስልምና የጦር መሳርያ ይዞ አደባባይ ሲወጣ በጦር መሳርያ ማስታገስ ቢችልም ነገር ግን ትምህርቱን የሚጋፈጥበት ሥነ መለኮታዊ መሳርያ የለውም፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት እንደታዘብነው አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይባስ ብለው ከአክራሪ እስልምና ጋር በመተባበር አጀንዳውን ሲያራግቡና ጥብቅና ሲቆሙለት ታይተዋል፡፡ ይህ የሚያመለክተው አንዳንድ ፖለቲከኞች የዛሬ ጥቅማቸውን እንጂ የነገውን አደጋ ማየት አለመፈለጋቸውን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ሥልጣን ቢይዙ ችግሩን ከማባባስ ውጪ መፍትሄ መስጠት አይችሉም፡፡
የመገናኛ ብዙኃንን ስንመለከት እንኳንስ መፍትሄ ሊሰጡ ይቅርና ጥያቄውን እንኳ በትክክል የተረዱት አይመስልም፡፡ በትክክል ቢረዱትም እንኳን ፖለቲካዊ ትክክለኝነት ስለሚጫናቸው የችግሩን ስረ መሰረት በመንካት መፍትሄ ማፈላለግ አይችሉም፡፡
ምሑራን ጥያቄውን የተወሰነ ያህል ይረዱታል ነገር ግን የችግሩን ስረ መሰረት በመጥቀስ የመፍትሄ ሐሳቦችን እንዳይሰነዝሩ በፍርሃትና በፖለቲካዊ ትክክለኝነት ተሸብበዋል፡፡
አንዳንድ ለዘብተኛ አመለካከት ያላቸው ምዕራባውያን የሚከተሉትን “መፍትሄዎች” ያስቀምጣሉ፡-
ለአክራሪ ሙስሊሞች ምንም ትኩረት አለመስጠትና ችላ ማለት፡፡ ነገር ግን ችላ የሚባሉት እምን ድረስ ነው? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ሰይፍ አንገታችን ላይ ተቀምጦ ትኩረት አንሰጠውም ማለት የሞኝ መፍትሄ ነው፡፡
ባሉበት እንዲሆኑ ማገድ (ወደ ክልላችን እንዳይገቡ ማድረግ፡፡) o አሁን ካለው የሕዝቦች እንቅስቃሴና የመረጃ ቴክኖሎጂ ደረጃ አኳያ አያስኬድም፡፡ የውጪዎቹ እንዳይገቡ ማገድ ይቻል ይሆናል፣ ውስጥ የሚገኙትንስ? መግደል? ማሰር? ከሃገር ማባረር? አያዋጣም፡፡
እስልምናን ከፖለቲካዊ ይዘቱ በማፋታት ምዕራባዊ መልክ ያለውን እስልምና መፍጠር [ለምሳሌ ኪልያም (Quilliam) ፕሮጀት]፡፡[3]

Saturday, August 27, 2016

ሴቶች ሁልጊዜ ልብ በሉ!



ሴቶች ከወንድ ጓደኛ ማንን ትወዱ? ማንንስ ትመርጡ? ከማንስ ጋር ጋብቻን ትፈፅሙ? እስኪ ራሳችሁን ጠይቁ።
በራስ መተማመን ያላት ሴት ለችግሮች ራሷን አሳልፋ አትሰጥም። በሁኔታዎች መለዋወጥ አትሸበርም። ራሷን ላጋጠማት ተግዳሮት ታዘጋጃለች እንጂ በሽንፈት ለቅሶን አታስተናግድም። ታዲያ ይህንን ኃይል ከየት ማግኘት ትችላለች?
               ✔ ✔✔
መልካም ክርስቲያናዊ ቤተሰብ ውስጥ ያደገች ሴት ስነምግባርን፣ እውቀትን፣ ችሎታና በራስ መተማመንን የምታዳብረው በቅርቧ ባለው ከቤተሰቧ ነው። በአስተዳደግና በልጅነት ሕይወት ጉድለት የደረሰባት፣ በብዙ ችግሮችና መከራ ውስጥ ያለፈች ሴት በስነልቦናዋ ላይ በሚደርሰው ጉዳት በራስ መተማመኗን በማጣት ችሎታዋን ለማውጣትና ችግሮችን ለመጋፈጥ ያላትን አቅም አውጥታ ለመጠቀም ሊያዳግታት ይችላል።

 በተለይም በአስገድዶ መደፈር፣ በእናት ወይም በአባት ብቻ ወይም ከሁለቱም አሳዳጊ ውጪ ያደገች፣ የኑሮ ጫናና ድህነት፣ አካባቢያዊና ሀገራዊ ችግሮች ( ጦርነት፣ ረሃብ፣ ስደት) በሴቷ ስነልቦና ላይ የሚያደርሱት ተጽእኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በቃላትም መግለፅ ከሚቻለው በላይ የስነልቡና ተጠቂ ልትሆን ትችላለች።
 በዚህም የተነሳ ሴቶች ለአካለ መጠን ከደረሱ በኋላ ቤተሰባዊ ሕይወትን ለመመስረት በሚያስችላቸው ሁኔታ ላይ ያሳለፉት ቁስል የሚያደርስባቸው የአእምሮ ፈተናና ትግል እጅግ ውስብስብ ነው።
የመጠራጠር፣ ያለማመን፣ አንዳንዴም በቀላሉ የመታለል ወይም የመሸወድ ክስተት ሲያጋጥማቸው ያታያል። ሴቶች በፈገግታና በሳቅ ሸፍነው በማህበራዊ ኑሮው ቶሎ የመቀላቀል ተፈጥሮአዊ ችሮታ አላቸው እንጂ በኋላቸው የተሸከሙት ህመም በጣም ብዙ ነው። ሲስቁና ሲጫወቱ ዘመናቸውን ሁሉ እድለኞች የነበሩ ሊመስለን ይችላል። እውነቱ ግን እሱ አይደሉም። ሴቶች መከራቸውን እንደወንድ እያመነዠኩ ስለማይኖሩ ከሰው ለመቀላቀል ብዙም አይቸገሩም። ያ ደግሞ ሴትን ልዩ ፍጥረትና የተወደደች ያደርጋታል። ሴት ለወንድ ሚስት ብቻ ሳትሆን የጉድለቱ ሙላት የመሆኗም ምስጢር ሁሉን መከራ መሸከም መቻሏ ነው። 6 ልጆቿን ያለአባት አሳድጋ ለቁምነገር ያበቃች እናት አውቃለሁ።
                ✔✔✔
ክርስቲያን ሴቶች ምንም እንኳን ያለፈ ሕይወታቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ባለ አዲስ የእምነት ልምምድ የተለወጠ ቢሆንም ያሳለፉት ስነልቦና በቀላሉ የሚፋቅ ባለመሆኑ አልፎ አልፎ መቸገራቸው አይቀርም። ከጋብቻ በፊት የመንፈሳዊ ጋብቻ ትምህርትና የምክር አገልግሎት ማግኘት የበለጠ ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው ስለሚችል በዚሁ መልኩ አስቀድመው ቢገለገሉ የተሻለ ግንዛቤ ይኖራቸዋል።
በኛ በኩል ያሉንን ምክሮች ጥቂት እንበል።
               ✔✔✔
ባለፈ ስህተትሽ አትቆጪ። የዛሬውን ሃሳብሽን እንዲቆጣጠረውም አትፍቀጂ። ያለፈው ላይመለስ አልፏል። ያለፈው ለዛሬው ያለው እድል አስተማሪ መሆኑ ብቻ ነው። ጎበዝ ሰው በሌላ ሰው ስህተት ይማራል፣ ሰነፍ ሰው ደግሞ ከራሱ ስህተት ይማራል። ያለፈው ስህተትሽ ለዛሬው ማንነትሽ ትምህርት ከሆነሽ፣ አንቺ የዛሬዋ ጎበዝ ነሽ። ካለፈችው ሰነፏ አንቺነትሽ በልጠሻል ማለት ነው። ስህተት አንዴ ከበዛ ደግሞ ሁለቴ ቢሆን ነው። ከደጋገመሽ ግን ስህተቱ ከጎዳሽ ነገር ሳይሆን ካንቺ አለመለወጥ የመጣ ነው።
ፈረንጆች እንዲህ የሚል አባባል አላቸው። "ስትሄድ የመታህ የድንጋይ እንቅፋት ስትመለስም ከደገመህ ስህተቱ የእንቅፋቱ ሳይሆን ድንጋዩ አንተው ነህ" ይላሉ።
ፍርሃትን በራስ መተማመን፣ ስህተትሽን በመታረም ማሸነፍ ትችያለሽ።
አብዛኛው ወንድ ሴትን የሚወደው በአይኑ ነው። የውስጧን ማንነት ሳያይ ውጫዊውን አይቶ ማድነቅም፣ መውደድም ይቻላል። ብቻውን ግን ለፍቅር ግንኙነት አያበቃም።
 የደም አይነት ልዩ ልዩ ነው። ሁሉም ደም ለሁሉም ሰው አይሆንም። በአይን የመጣ መውደድም በሁሉም ሴት ላይ ፍቅርን ሊመሰርት አይችልም። ለምርጫ የሚያበቃ ጥናት ያስፈልገዋል። የወደዱን ሁሉ ያፈቅሩናል ማለት አይደለም። ይህን ለማወቅ ጊዜ ወስዶ ማጥናት ተገቢ ነው። ለኛ የተሰጠ ሰው ከሆነ ለማጥናት በምንወስደው ጊዜ ያመልጠናል ብለን መስጋት አይገባም። እንዲያውም ሳናውቀው ዘው ከምንል ቢያመልጠን ይሻላል። ለኛ የተሰጠን እንዳይዘገይ ቶሎ መሄዱ ይሻላል። የከረመ ወይን ሲጠጡት ሆድ አይነፋም።

በአይን የወደደ የአይኑን አምሮት በአካል ባገኘው ጊዜ ቶሎ ይረካል። ከዚያም የማያርፈው አይኑ ወደሌላ ይሄዳል። ሴት ሆይ፣ የሚወድሽን ወንድ አይኑን ብቻ ሳይሆን ልቡን እዪው። ምን ይልሻል? ስሚው። አንቺን አይቶ ለልቡ አምሮት የሚቅበዘበዝ ከሆነ ችግር አለ። በአፉ እወድሻለሁ እያለ ፍቅሩን በተግባር የማያሳይ ከሆነ ችግር አለ። እንጋባ ሳይሆን እስክንጋባ አልጋ ላይ እንውጣ የሚልሽ ከሆነ ችግር አለ። የሚሰጥሽን ጊዜ ቀስ በቀስ የሚቀንስ ከሆነ ችግር አለ።
ታማኝ ወንዶችን ከአስመሳዮች ለመለየት ጊዜ ውሰጂ። አትቸኩዪ። በምላስ ብልጠት አትሸነፊ። ልቡን ለማወቅ አንቺ አምላክ አይደለሽም። ምላሱን በተግባሩ ፈትኚ። ከትዳር በፊት የተደጋገመ ውሸት በትዳር ውስጥም ይቀጥላልና ተጠንቀቂ።
በሰውኛ ሚዛን መልክና ውበት ጥሩ ነው። ነገር ግን ለእግዚአብሔር መንግስት በተመረጠ ትዳር ውስጥ ሁሉም ከንቱ ነው። ቅን እንጂ ቅንቅን አትሁኚ። ገንዘብ፣ ጌጥና ምቾት አያታልሽ። ዝሙት ኃጢአት ነው። ፍፃሜውም ሞት ነው። ስለዚህ በታማኝነት ለእግዚአብሔር መንግስት ራስሽን አስገዢ።

 ጠቢቡ በመጽሐፉ እንዳለው መክብብ 6፣12
"ሰው በከንቱ ወራቱ ቍጥርና እንደ ጥላ በሚያሳልፈው ዘመኑ በሕይወቱ ሳለ ለሰው የሚሻለውን የሚያውቅ ማነው? ወይስ ለሰው ከፀሐይ በታች ከእርሱ በኋላ የሚሆነውን ማን ይነግረዋል?" ነውና ለጊዜው ለእግዚአብሔር ክብር ለሚሆን ሕይወት እንጂ ይህ ቋሚ መኖሪያችን አይደለምና ራስን መግዛት አትርሺ።
             ✔✔✔
"ጌታ ቅርብ ነው። በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ"
ፊልጵ 4:6

Monday, August 22, 2016

ወሀቢዝም በኢትዮጵያ ውስጥ!


by ኢትዮ - አፖሎጂስት

ከ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት ነፃነት ከቀደሙት ዘመናት ጋር ሊነፃፀር በማይችልበት ሁኔታ መከበሩ የማይካድ ሃቅ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን ነፃነት የለአግባብ የተጠቀሙና የጥፋት መርዛቸውን በትውልዱ መካከል ለማሰራጨት የተጉ፣ ከዚህም የተነሳ ብዙ ጥፋቶችን ያስከተሉ ቡድኖች መኖራቸው አልቀረም፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ የወሃቢዝም (ሰለፊ) ፍልስፍናን የሚከተሉ ወገኖች ይጠቀሳሉ፡፡ ዛሬ በሃገሪቱ ውስጥ በብዛት ተሰራጭቶ በሕዝቦች መካከል ያለውን የመቻቻልና አብሮ የመኖር ባሕል እያደፈረሰ የሚገኘው ወሃቢዝም ይህንን ነፃነት ተጠቅሞ የተስፋፋ ይሁን እንጂ እግሩን  በሃገሪቱ ውስጥ ካሳረፈ ብዙ አስርተ አመታት አልፈዋል፡፡

ፋሺስት ኢጣልያ  በኢትዮጵያ ላይ የነበረውን እኩይ አጀንዳ ለማስፈፀም ሙስሊሞችን መንከባከብ የሚል መርሃ ግብር ስለነበረው ሙስሊሞች የሐጅ ጉዞ እንዲያደርጉ ያበረታታ ነበር፡፡ በገንዘብም በመደጎም ይልክ ነበር፡፡ በ1933 ለሐጅ ወደ መካ የተጓዙት ኢትዮጵያውያን ቁጥር 11 ብቻ ሲሆን ከ1934-1935 የሄዱት 29፣ ከ1935-1936 ደግሞ 7 ሰዎች ብቻ ነበሩ፡፡ ነገር ግን በ1937 ይህ ቁጥር ወደ 1,700 አድጓል፡፡ ሁሉም ደግሞ በኢጣሊያ መንግሥት ድጎማ የሄዱ ነበሩ፡፡[1] ሳዑዲ አረብያ ለሐጅ የሚሄዱትን ኢትዮጵያውያን በወሃቢዝም ፍልስፍና አጥምቃ ወደ ሃገር ውስጥ በማስገባት ፍልስፍናውን የማስፋፋት ሥራዋን የጀመረችው ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ከመውረሯ በፊት ነበር፡፡ በተለይም ደግሞ ሼኽ ዩሱፍ አብደል ረህማን እና ሐጂ ኢብራሂም ሀሰን የተሰኙ ሁለት ሰዎች ለዚህ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ሁለቱም ወደ ሳዑዲ የተጓዙት በ1930ዎቹ መጀመርያ አካባቢ ነበር፡፡ ሼኽ ዩሱፍ በ1939 ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በሐረር ከተማ የወሃቢዝም ትምህርታቸውን ማስተማር የጀመሩ ሲሆን የሐረርን ከተማ የቀድሞ ነፃነት ለመመለስ የከተማይቱን ሙስሊም ሊቃውንት አደራጅተው ፊርማ በማሰባሰብ በወቅቱ የብሪቲሽ የአካባቢው አማካሪ ለነበሩት ለኮሎኔል ዳላስ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ ነገር ግን ኮሎኔሉ ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርገዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር ሼኽ ዩሱፍ ለረጅም ጊዜ ትግል መሰረት ለመጣል የወሰኑት፡፡ ከዚያም ብሔራዊ እስላማዊ ማሕበር (አል-ጀማኢያ አል-ወኒያ አል-ኢስላሚያ) ወይም አል-ዋታኒ የተሰኘ ማሕበር በማቋቋም መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡ የማሕበሩ አባላት በሙሉ ሐረርን “ከኢትዮጵያ ቅኝ ነፃ በማውጣት” አሕመድ ግራኝባስቀመጠው ምሳሌነት መሰረት እስላማዊ መንግሥት እንደገና ለማቋቋም ቃል ኪዳን ገቡ፡፡ የሐረርን ሕዝብ በሚገባ ሳያስተምሩ መንግሥትን መጋፈጥ እንደማይቻል ስለተገነዘቡም ዋታኒ እስላማዊ ማሕበር ቀደም ሲል የተሰራውን ትምህርት ቤት በመጠቀም እስላማዊውን ትምህርት በማስተማር ላይ እንዲያተኩር ተወሰነ፡፡ ትምህርት ቤቱም ዘመናዊ መልክ ኖሮት አረብኛና በሐጂ ኢብራሂም ሀሰን አማካይነት ደግሞ የወሃቢዝም ትምህርት እንዲሰጥ ተባለ፡፡ ሐጂ ኢብራሂምም በከፍተኛ ትጋት በየምሽቱ በቤታቸውም ጭምር ይህንን ፍልስፍና ማስተማር ተያያዙ፡፡ የግራኝ ታሪክና ወታደራዊ አካሄድ እንደ አንድ ዋና ትምህርት ይሰጥ ነበር፡፡ ዋታኒ እስላማዊ ማሕበር በሚያዘጋጃቸው ክብረ በዓላት ላይ በአሕመድ ግራኝ ዙርያ የሚያጠነጥኑ ግጥሞችና የውዳሴ መዝሙሮችም ተዘጋጅተው በተማሪዎች ይዘመሩ ነበር፡፡ ሼኽ አብደል ረህማን ደግሞ በአዲስ አበባ ውስጥ በነበራቸው የመጻሕፍት መደብር አማካይነት በአረብኛ የተዘጋጁ የወሃቢያ መጻሕፍትን እያስመጡ ያከፋፍሉ ነበር፡፡ ነገር ግን ኋላ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር ሆነው የተሾሙት ከበደ ሚካኤል ትምህርት ቤቱን በጎበኙበት ወቅት ለግራኝ የሚዜሙትን መዝሙሮች ትርጉም ከሰሙ በኋላ እንዳይዘመሩ ያገዱ ሲሆን አማርኛም የመማርያ ቋንቋ እንዲሆን አዘዋል፡፡[2]

ነገር ግን ከመንግሥት ይልቅ የዋሃቢዝም ዋና ጠላት የነበሩት ሼኽ አብደላህ ኢብን ሙሐመድ ኢብን ዩሱፍ (አብደላህ አል-ሐረሪ) የተሰኙ ሙስሊም ሊቅ ነበሩ፡፡ እኚህ ሰው የሃገራችን አብዛኛው ሙስሊም የሚከተለው በአንፃራዊነት ሰላማዊ ሊባል የሚችለው የሱፊ እስልምና ተከታይ ሲሆኑ ከፀረ ሰላም ትምህርቱ በተጨማሪ አሁን በዝርዝር የማናያቸውን የወሃቢዝም አስተምህሮዎች ይቃወሙ ነበር፡፡ ሼክ አብደላህ ከሐረር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ውሏቸውን በመርካቶ አካባቢ በማድረግ ሙስሊሙን ህብረተሰብ በማስተማር ዝነኛ ሆነው ነበር፡፡ ኋላም ወደ ሊባኖስ በማቅናት በመካከለኛው ምስራቅ ትምህርታቸውን በማስፋፋት በዓለም ላይ ዋነኛ ፀረ ወሃቢዝም ለሆነው ዓለም አቀፍ እስላማዊ ማሕበር ሊቀ መንበር ሆነዋል፡፡[3] የኚህን

ኢትዮጵያዊ ትምህርት አረቦች “አሕባሽ” በማለት ይጠሩታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሐጂ አብደላህ ከሐበሻ ምድር የመጡ መሆናቸው ነው፡፡ ትምህርቱ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት የኖረውና አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝበ ሙስሊም የሚከተለው የሱፊ እስልምና እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ትምህርቱን የተቀበሉና ከኢትዮጵያዊው የተማሩ ሊቃውንት ስልጠናዎችን ለመስጠት ከሊባኖስ በመጡበት ወቅት ወሃቢዮች “መንግሥት አሕባሽ የሚባል አዲስ ሃይማኖት አመጣብን” በማለት ሁከት መፍጠር ጀመሩ፡፡ እነርሱ ባለ ሃገር ሆነው የሃገሪቱን የሱፊ ሊቃውንት ማሳደድና መግደል ተያያዙ፡፡ መንግሥትም የኢትዮጵያ ሕዝብ ቅሬታ እስኪገባው ድረስ ታገሳቸው፡፡ አሁንም አቅማቸው ቢሟስስም በየስርቻው መሽሎክሎካቸውንና “ድምፃችን ይሰማ” እያሉ በሰላላ ድምፆቻቸው መጮኻቸውን አልተውም፡፡

ሼኽ አብደላህ በአንድ ወቅት በሐረር ውስጥ በነበረው የወሃቢዮች ትምህርት ቤት ላይ ባስነሱት ተቃውሞ ምክንያት ለእስር ተዳርገው ነበር፡፡ አዲስ አበባ በነበሩበት ጊዜ ሐጂ ኢብራሂም ለአንድ የአረብኛ ጋዜጣ በፃፉት መጣጥፍ ክርስቲያናዊት ኢትዮጵያንና ንጉሡን ማጣጣላቸውን ለመንግሥት መረጃ እንደሰጡም ይነገራል፡፡ በዚህም ምክንያት ሐጂ ኢብራሂምና የትምህርት ቤቱ የወሃቢያ መምህራን ታስረው ለፍርድ የቀረቡ ሲሆን ሐጂ ኢብራሂም ከሐረር ከተማ ወደ ሌላ የኢትዮጵያ ክፍል ሄደው እንዲኖሩ ተፈርዶባቸዋል፡፡ እኚህ ሰው አሁን በሕይወት የሉም፡፡ ከዚያም ሼኽ አብደላህ የሐረር ከተማ ሙፍቲ ሆነው በመሾማቸው ምክንያት ወሃቢዮች ድምፃቸውን አጥፍተው ለመኖር የተገደዱበት ሁኔታ ነበር፡፡ የሐረር ወሃብዮች ኋላ ላይ በ1948 የሶማሌ ወጣቶች ክበብ ተብሎ በመንግሥት ፈቃድ በተቋቋመው ቡድን ውስጥ እጃቸውን አስገብተው የነበረ ሲሆን የአሕመድ ግራኝ መንፈስ እንደገና በመምጣት ከተማይቱ ላይ አንዣቦ ነበር፡፡ ነገር ግን ጥር 1948 ጉዳዩ ይፋ በመሆን 200 የሚሆኑ የክበቡ አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ ወጣቶቹ ይቅርታ በመጠየቅ የተፈቱ ሲሆን ሰማንያ አንድ የሚሆኑ የወሃቢያን እንቅስቃሴ የሚመሩ የዋታኒ ማሕበር አባላት ከተማይቱን በመልቀቅ እንዲበተኑ ተደርጓል፡፡ በዚሁ ዓመት ኢትዮጵያ የኦጋዴን ግዛቷን በማግኘቷ ምክንያት በሐረርጌ ላይ ያላት ሙሉ ቁጥጥር እውን ስለሆነ በ1936 በሐረር ከተማ የተጀመረውም በወሃቢዝም የተመራው የእስላማዊ ፖለቲካ መነቃቃት ሊከሽፍ ችሏል፡፡[4]ኢትዮጵያዊ ትምህርት አረቦች “አሕባሽ” በማለት ይጠሩታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሐጂ አብደላህ ከሐበሻ ምድር የመጡ መሆናቸው ነው፡፡ ትምህርቱ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት የኖረውና አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝበ ሙስሊም የሚከተለው የሱፊ እስልምና እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ትምህርቱን የተቀበሉና ከኢትዮጵያዊው የተማሩ ሊቃውንት ስልጠናዎችን ለመስጠት ከሊባኖስ በመጡበት ወቅት ወሃቢዮች “መንግሥት አሕባሽ የሚባል አዲስ ሃይማኖት አመጣብን” በማለት ሁከት መፍጠር ጀመሩ፡፡ እነርሱ ባለ ሃገር ሆነው የሃገሪቱን የሱፊ ሊቃውንት ማሳደድና መግደል ተያያዙ፡፡ መንግሥትም የኢትዮጵያ ሕዝብ ቅሬታ እስኪገባው ድረስ ታገሳቸው፡፡ አሁንም አቅማቸው ቢሟስስም በየስርቻው መሽሎክሎካቸውንና “ድምፃችን ይሰማ” እያሉ በሰላላ ድምፆቻቸው መጮኻቸውን አልተውም፡፡

የደርግ መንግሥት ባጠቃላይ ሃይማኖትን በተመለከተ ከሚከተለው ፖሊሲ የተነሳ ያን ያህል የጎላ የወሃቢዝም እንቅስቃሴ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ውስጥ ለውስጥ የተሰሩ ሥራዎች እንደነበሩ እሙን ነው፡፡ በ1958 ከየመን በመጣ ስደተኛ የተመሰረተው የአል-አወልያ ትምህርት ቤት በዘመነ ደርግ ጥብቅ በሆነ የመንግሥት ቁጥጥር ስር ነበር፡፡[5] ደርግ ወደ መውደቂያው አካባቢ “የሰርገኛ መጣ…” ዓይነት የፖሊሲ ለውጦችን በማድረጉ ምክንያት ለሳዑዲ እንቅስቃሴዎችም በር ከፍቶ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት የዓለም የሙስሊሞች ሊግ ከእርዳታ ማስተባበርያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን (እማማኮ) ጋር በመተባበር ትምህርት ቤቶችን፣ እጓለ ሙታንን እና ክሊኒኮችን ለማቋቋም ስምምነት አደረገ፡፡ መንግሥትና ሊጉ ያላቸው ግንኙነት መጥበቁን ከሚያመለክቱ ተግባራት መካከል አንዱ ሊጉ የሃይማኖትና የአረብኛ ቋንቋ ሥልጠናዎችን እንዲሰጥ መፈቀዱ ነበር፡፡ በ1991 ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት የመጣው የሊጉ ልዑካን ቡድን በወሎ፣ በሐረር፣ በአዲስ አበባና በደብረ ዘይት ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ሥራ ላይ መሆኑን መግለፁ ኢትዮጵያን የማስለም እንቅስቃሴው በአዲስ መልክ መጀመሩን አመላካች ነበር፡፡[6]

ከ1991 ወዲህ የተደረገውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ በሃገራችን ውስጥ የተገኘውን የእምነት ነፃነት ሽፋን በማድረግ ብዙ ጥፋቶች ተፈፅመዋል፡፡ በተለይ የወሃቢዝም ፍልስፍና ተከታዮች ነፃነቱ የሰጣቸውን ክፍተት በመጠቀም አክራሪ የሆኑ ትምህርቶችን በማስተማር  ግርምቢጠኛ ባህርያቸውም ከልክ አልፎ በሚያሰራጯቸው ጽሑፎችና የድምፅ እንዲሁም የምስል መልዕክቶች ሌሎች ሃይማኖቶችን በነገር በመጎሽመጥ ሃገሪቱን ሲያምሱ ቆይተዋል፡፡ የተሰጣቸውንም የመንግሥት ሥልጣን ለእምነታቸው ማስፋፍያ በመጠቀም ብዙ በደሎችን ፈፅመዋል፡፡ በአንድ ወቅት ከውጪ ሃገራት በገፍ በመግባት ሃገሪቱን ያጥለቀለቁት የጂሃድ ፊልሞችና አክራሪነትን የሚሰብኩ የህትመት ሥራዎች ያስከተሉትን ውጤት ሁላችንም በግልፅ ያየነው ነው፡፡ በተለይ ከሳዑዲ አረብያ በሚመጣው ፔትሮ ዶላር የተገነቡት መስጊዶችና እስላማዊ ማዕከላት  ሃገሪቱን እንደሙጃ ውጠዋታል፡፡ በበጎ አድራጎት ሥም ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ በርካታ እስላማዊ ድርጅቶችም ውስጥ ለውስጥ ጂሃዳውያንን እያሰለጠኑና የገንዘብ ድጋፍ እያደረጉ ሃገሪቱን ቁልቁል ወደ ጥፋት አዘቅት ነድተዋታል፡፡ እቅዳቸው ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ ሊከተል የሚችለውን አደጋ ማሰብ በእጅጉ ይከብዳል፡፡ አደጋውን ከማስቀረት አንፃር መንግስት ይበል የሚያሰኙ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡ በተለይም የወሃቢዝም ዋነኛ የርቢ ማዕከል የሆነው አል-አወልያ እስላማዊ ትምህርት ቤት ከወሃቢዮች እጅ ወጥቶ ለተገቢው አካል መሰጠቱ ትክክለኛ እርምጃ ነበር፡፡ ይህ ከአንደኛ ደረጃ ተነስቶ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በምስራቅ አፍሪቃም ጭምር ግምባር ቀደም እስላማዊ ትምህርት ቤት ለመሆን የበቃው የፅንፈኞች ማዕከል በሃገሪቱ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ቀላል አልነበረም፡፡ የተወሰደው እርምጃ ከረፈደ በኋላ ቢሆንም ነገር ግን ከመሸ በኋላ አለመሆኑ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን በመርዛማ ትምህርቱ ተበክለው የወጡ ወጣቶች ክትትል ሊደረግላቸውና በፅንፈኝነት ቅልበሳ መርሃ ግብር (De-radicalisation Program) ሊታቀፉ ይገባል፡፡

በኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ላይ የደረሱ እስላማዊ ጥቃቶች የቅርብ ዘመን ትዝታዎች

ቀን ቦታ የሞተ የቆሰለ የክስተቱ ዝርዝር
6/2/97 አርሲ – ቆሬ 10 3 2237 ክርስቲያኖች ተፈናቀሉ፡፡ 1 ቤተ ክርስቲያንና 194 የክርስቲያን ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተቃጠሉ፡፡ 24 የክርስቲያን ቤቶች በከፊል ተቃጠሉ፡፡ 304 ከብቶች ተዘረፉ፡፡
16/1/99 ጀምሮ ጂማ – በሻሻ 18 38 488 በግድ ሰልመዋል፡፡ ከ2000 በላይ ተፈናቅለዋል፡፡ ከ850 በላይ የክርስቲያን ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ 3 አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፡፡ 4 ተዘርፈዋል፡፡
ከላይ የተቀመጡት መረጃዎች የተወሰዱት “በኢትዮጵያ የሃይማኖት መቻቻል አለን” በሚል ርዕስ በአባ ሳሙኤል ከተዘጋጀው መጽሐፍ ገፅ 28-31 እና “አክራሪ እስልምና በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በኤፍሬም እሸቴ ከተዘጋጀው መጽሐፍ ገፅ 172-175 ነው፡፡ ዓመታቱ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ናቸው፡፡

ቀን ቦታ የሞተ የቆሰለ የክስተቱ ዝርዝር
3/8/11 ጅማ – አሰንዳቦ 2 – በቁጣ የተሞሉ ሙስሊሞች አብያተ ክርስቲያናትን የማቃጠል ዘመቻ አድርገዋል፡፡
3/1/11 ባሌ – ሆማ ቀበሌ – 17 ወንጌልን ለማስተማር በወጡ የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ክርስቲያን ተማሪዎች ላይ ድብደባ ተፈፅሟል፡፡
9/13/10 አፋር – ዱፍቲ – 1 ከእስልምና የወጣን አንድ ክርስቲያን ወጣት ሙስሊሞች በስለት ወግተዋል፡፡
8/21/10 አዲስ አበባ – 1 ታዋቂ ክርስቲያን መሪ በበትር ተደብድቧል፡፡
7/16/2010 አዲስ አበባ – 1 ከእስልምና የመጣ ክርስቲያን በቁጣ በተሞሉ ሙስሊሞች ተደብድቧል፡፡
9/11/09 ሸዋ – ሰንበቴ – 3 የሙስሊሞች ቡድን ወደ ቤተ ክርስቲያን ግር ብሎ በመግባት በፀሎት ላይ የነበሩትን ክርስቲያኖች ክፉኛ አቁስለዋል፡፡
7/3/09 ደሴ 2 – በቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ በሥራ ላይ የነበሩ 2 ክርስቲያኖች ተኩስ ተከፍቶባቸው ተገድለዋል፡፡
9/20/08 አዲስ አበባ – 1 አንድ ዕድሜው 35 ዓመት የሚሆን ክርስቲያን መሪ ለሞት እስኪቀርብ ድረስ በሙስሊሞች ተደብድቧል፡፡
7/19/08 ጂጂጋ – 2 ሁለት ከእስልምና የመጡ ክርስቲያኖች በድንጋይ ተደብድበዋል፡፡
4/30/07 ጂጂጋ 2 3 ሙስሊሞች በድንኳን ውስጥ በተሰበሰቡ ክርስቲያኖች ላይ ቦምብ በመጣል 2 ክርስቲያኖችን ሲገድሉ 3 አቁስለዋል፡፡
1/5/07 ኮፈሌ 1 – ሙስሊሞች አንድ ክርስቲያን በብረት ቀጥቅጠው ገድለዋል፡፡
10/1/06 ጂማ 10 12 ሁለት አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፡፡
4/16/06 ጂጂጋ 3 23 በሁለት ምግብ ቤቶችና በአንድ ቤተ ክርስቲያን ላይ በሙስሊሞች በተፈፀመ የቦምብ ጥቃት የደረሰ አደጋ
3/22/06 አርሲ ነጌሌ 1 – ሙስሊሞች በአንድ የፕሮቴስታን ቤተ ክርስቲያን በር ፊትለፊት ከእስልምና የመጣን አንድ ክርስቲያን በጥይት ገድለዋል፡፡ ሟች የ 7 ልጆች አባት ነበሩ፡፡
7/19/05 ጂጂጋ 1 – የታጠቁ ሙስሊሞች አውቶብስ በማስቆም በውስጥ የነበሩትን ክርስቲያኖች ሸሃዳ አስብለዋል፤ ወደ መካም በመዞር እንዲሰግዱ አስገድደዋል፡፡ ይህንን ለማድረግ ፍቃደኛ ያልሆነ አንድ ወጣት ተገድሏል፡፡
መረጃዎቹ የተወሰዱት በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሱትን እስላማዊ ጥቃቶች በመዘገብ ከሚታወቅ ክርስቲያናዊ ድህረ ገፅ ላይ ነው፡፡ ዓመታቱ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ናቸው፡፡

http://www.thereligionofpeace.com/pages/christianattacks.htm

ከላይ የተጠቀሱት ጥቃቶች ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ሲሆኑ ፍትህን በማዛባት፣ አድማ በማድረግ፣ የክርስቲያን ልጆችን አፍኖ በመውሰድ፣ አስገድዶ በመድፈር፣ አስፈራርቶ አካባቢን በማስለቀቅ፣ የክርስቲያን ይዞታዎችን በልዩ ልዩ ዘዴዎች በመንጠቅ፣ ወዘተ. የተፈፀሙ የግፍ ሥራዎችን ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም፡፡

[1] Haggai Erlich, Saudi Arabia & Ethiopia, 2007, p. 73

[2] Ibd, 80-83

[3] Ibd, 84

[4] Ibd, 85-92

[5] Ibd, 189-190

[6] ኤፍሬም እሸቴ፣ አክራሪ እስልምና በኢትዮጵያ፣ 2000፣ ገፅ 142-143


Thursday, August 18, 2016

ከመንጋ አድር ባይ ጳጳስ፣ ፓስተር፣ ቄስና ሼክ ተብዬ አንድ ሳበኬ ወንጌል ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ያቀረበው ማሳሰቢያ ይሻላል!


ለኢትዮጲያ የኢፌድሪ መንግስት ጠቅላይ ሚንስተር ለአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ እና አመራሩ።

ከፀጋአብ በቀለ(የወንጌል ሰባኪ)

          የየትኛውም የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አራማጅ አይደለሁም፡፡ ጥሪዬ ስላልሆነ፡፡ ለፖለቲከኞች ግን አክብሮቴ ትልቅ ነው፡፡ በግሌ በዚህ መንግሥት ከቀበሌ እስከ ፌደራል ስላሉት መሪዎች እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡ ቃሉ፡-"ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ። ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው"(ሮሜ.13፡1) የሚለውን ቃል ስለማምን፡፡ እንዲሁም በእግዚአብሔር መንፈስ የተመራው ሐዋርያ "ልመናና ጸሎት ምልጃም ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ"(1ጢሞ.2፡1) ስለሚል ሁለም እግዚአብሔር ማስተዋልና ጥበቡን እንድሰጣችሁ እፀልያለሁ፡፡ እግዚአብሔር መንግሥትን ያፈልሳል ደግሞም ሌላ ያስነሣል፡፡ እግዚአብሔር፡- "ጊዜያትንና ዘመናትን ይለውጣል ነገሥታትን ያፈልሳል፣ ነገሥታትንም ያስነሣል ጥበብን ለጠቢባን እውቀትንም ለአስተዋዮች ይሰጣል"(ዳን.2፡21)፡፡
ለመንግሥት ያለኝ አድናቆት

      በዚህ ሥርዓት እውነተኛና ሚዛናዊ ሕሊና ያለው ዜጋ ቀርቶ ዓለም ሁሉ ያደነቀው በትምህርት፣ በጤና፣ በኢኮኖሚ፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የብሔርሰቦች እኩልነት፣ በኢንቪስትመንት፣ በሃይማኖት ነፃነት፣ ...ረገድ የተገኘው ድል ትልቅ በመሆኑ ለዚህ ሁሉ አቅምና ኃይል የሆነን እግዚአብሔርን በማመስገን ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ያለኝ ግላዊ አድናቆቴን ከልቤ መግለጥ እፈልጋለሁ፡፡ እግዚአብሔር የአገሬን ሕዝብና መንግሥት ይባርክ!

ለመንግሥታችን በትህትና የቀረበ ግልጽ መልዕክት                                                                                                                      
    በተቃራኒው ኃላፊነትና ሸክም እንደምሰማው እንደ አንድ የዚህች አገር ዜጋና የወንጌል አገልጋይ ስለዚህች አገር መጻኢ ሕይወት ሳስብና ስጸልይ ብሩህ ገጽታና ያን ለማጥፋት የሚታገል አሉታዊ ሁለት ገጽታዎች ይታዩኛል፡፡ በዚህም ይች አገር በመስቀለኛ መንገድ ላይ መሆኗ ተገነዘብኩ፡፡ እነዚህ ተግዳሮቶች በትክክል ከተጠቀምንባቸው የሚበልጥ ዕድገትና ለውጥ ይዞ የመጣ ሲሆን ካልተጠንቀቅን በዚህች አገር ትልቅ ጥፋትም ሊያመጣ የሚችል አቅም እንዳለሁ ስገነዘብ ባልተለመደ መንገድ ያልተለመደ ድምፅ ግልጽ አሰተያየት በትልቅ ትህትናና አክብሮት በማኅበራዊ ሚዲያ ለማቅረብ ወሰንኩ፡፡

1. የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት በሕግ መደንገጉ፤ ራስን በራስ ማስተዳደሩ፣ የራስን ቋንቋ፣ ባሕልና እሴቶች ማሳደጉ መልካም ሆኖ ሳለ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ስለ ልዩነታችን፣ ስለመንደራችን፣ ስለብሔራችን፣ ስለጎጣችን እንድናስብ የተደረገውን ያህል ስለ አንድነታችንና ስለአገራችን እንድናስብና እንድንነጋገር አልተደረግንም የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡
 ዓመታዊ የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን ለአንድ ሳምንት ከማክበር ያለፈ፡፡ ዛሬ ከደቡብ ወደ ሰሜን፣ ከሰሜን ወደ ምዕራብ፣ ከምዕራብ ወደ ምስራቅ ሄዶ በነፃነት ከመሥራት ኢትዮጵያውያን ወደ ተለያዩ አገራት መሰደድን ይመርጣሉ፡፡ ለመገናኛ ብዙሀን ዜና ግብአት አንድነታችንን የሚያሳዩ ሰሞነኛ ዜናዎችና ትእይንቶች እንጂ ለእርስ በርሳችን ያለን እይታና ልብ እጅግ መጥበቡ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
 ለምሳሌ፡- በቅርቡ በተነሳው ግጭት አንዳንድ አካባቢዎች ሌላውን ብሔር ለይቶ የማጥቃትና ከአካባቢያችን ውጡ የሚሉ ግልጽ መልዕክቶች ሲተላለፉ አይተናል፡፡ ሌላው ከኦሮምያ ዩንቨርሲቲ የጨረሱ ወጣት ተማሪዎች ወደ ሌሎች ክልሎች ሄደው ሥራ መሥራት እየቻሉ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የአገሪቷን ብሔራዊ ቋንቋ አማርኛን ስለማይችሉ፡፡ በአብዛኛው የተማረ ኃይል ተምሮ እየተመለሰ ያለው ወደ መንደሩ ሲሆን ወደ ሌላ ስፍራ ሲሄዱ ተቀባይነት የላቸውም፡፡ ከዚህም የተነሣ በብዙ ወረዳዎች ዩንቪርሲቲ የጨረሱ ወጣቶች ሥራ ፈተው ይቀመጣሉ፡፡ ሥራ የፈታ አዕምሮ ደግሞ አደገኛነቱ የታወቀ ነው፡፡
 ያ ሚዛናዊ ሥራ እንደሚገባው ባለ መሠራቱ አሁን የገባንበት አንዳንድ ተግዳሮቶች ተጨባጭ ማስረጃዎችና ገሃዳዊና ጊዜ የማይሰጣቸው የለውጥ ጥሪ ናቸው፡፡ ለዚህ ትክክለኛ ጥሪ መንግሥት የተቃዋሚዎች ድምፅ አድርጎ ከመደምደም ይልቅ ትክከለኛ ምላሽ ቢሰጥ የሚል የብዙዎች ጩኼት ነው፡፡
 መንግሥታችን ያለፈውን ድልና ስኬት ብቻ ሳይሆን በብዙዎች ልብ በቅሎ ምድሪቷ ወዳልተፈለገው አቅጣጫ ሊወስዳት እየታገለ ያለውን በብሔርና በቋንቋ ላይ ያውጠነጠነ አደገኛ ጽንፈኝነት ላይ በጥንቃቄ መሥራት አለበት፡፡ ተሐድሶ የግድ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ጠባብነት ታላቅቷን ሶቪየት ኅብረት፣ ዩጎዝላቪያ ...የሕዝብን ጭፍጨፋ፣ መፈናቅሎችና የአገር መፋራረስና የሩዋንዳውያን መተላለቅ ምክንያት መሆኑን ምሁራን ይጠቅሳሉ፡፡ በብዙ አስቸጋሪ መንገድ ውስጥ ሄዶ ለዚህ የበቃውና ሕዳሴን መለያው ያደረገ መንግሥት ይህን ማድረግ ቀላል ባይሆንም አይችልም የሚል ልብ ግን የለኝም፡፡ ይህን እውን ለማድረግ መንግሥት ብቻውን አይደለም፡፡ ዜጎች ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን መሥራት አለብን፡፡ መንግሥት በዚህ ላይ ለመሥራት ካልፈቀደ ግን መጪው መልካም እንዳልሆነ የማገለግለው የሕያው አምላክ መንፈስ አመልክቶኛል፡፡

ቤንጃሚን ፍራንከሊን የተባሉ ሊቅ ሲናገሩ፡- "የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ እንደ ሞት ሽረት የሚቆጥሩ መንግሥታት በተፈጠሩበት ቆዳ ተጠቅልለው የሚሞቱ ናቸው፡፡ አንድ አገር ወይም ሕዝብ የሚመራበት ፖሊሲ፣ ስትራቴጂዎችና ርዕዮተ ዓለማዊ ፍልስፍናዎች እንደ ተጨባጭ ዓለማዊ ሁኔታ ወይም ሕዝቡ ከደረሰበት የግንዛቤና የውጤት ደረጃ አንፃር መቃኘት አለባቸው፡፡ ይህን ማድረግ አለመቻል ነው ጉዞን የሚያደናቅፈው፡፡"

2. መንግሥት የደጋፊዎችን ድምፅ ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚዎችንም ድምፅ ከዚህ በበለጠ ቢሰማ መልካም ነው፡፡ (በስሜት የሚደገፍ የደጋፊዎች ድምፅ አንዳንዴም መንግስት እውነቱን ሊጋርደው ይችላል) የሚሰራው ፖለቲካ እንጂ የሃይማኖት ህግ አይደለም። ዴዝመንድ ቱቱ እንዳሉት፡" ሰላም ከፈለክ ከወዳጅ ጋር ሳይሆን ከጠላት ጋር መንጋገር ጀምር" እንዳሉት የተለያየ ርዕዮተ ዓለም መከተል ጠላትነት ባይሆንም እኛ ከሚንለው የተለየ ፍልስፍና ላላቸው ሰዎች ትክክለኛ ቦታ ልኖረን ይገባል፡፡ ሁለታችንም ለአንድ አገር ጥቅም እስከቆምን ድረስ፡፡ ይህን የሚንለው ብዙውን ጊዜ የፖለቲካው ምህዳር ከቀን ወደ ቀን እየጠበበ እንደመጣና አሳታፍ አይደለም በማለት አንዳንዶች በተስፋ ቁረጥ ስናገሩ ይሰማልና፡፡ ይህ ደግሞ ለዲሞክራሲያዊ ግንባታ አይበጅም፡፡

3. መንግሥት ቀርቶ መላዕክትም ይሳሳታሉ፤ ስለዚህ መንግሥት አንዳንዴ ገሃዳዊ ስህተት ሲፈጽም ይቅርታን ይጠይቅ፡፡  (እንደሚሳሳት አምኖ ለፈፀመው ስህተት ይቅርታ አለመጠየቅ ግብዝነት ነው)

መደምደሚያ
    መንግሥት ጠባብነት፣ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳሉ አምኖ ደጋግሞ በመገናኛ ብዙሃን ስናገር ይሰማል፡፡ ይህም ትልቅ ነገር ነው፡፡ ብርቱ አቋም፣ ጠንካራ እርምጃ ከእያንዳንዱ ዜጋ ይጠበቃል፡፡ ከላይ የተዘረዘሩ ሀሳቦች አዲስ ባይሆኑም አዲስ ትኩረት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ይፈልጋሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ የትላንቱ ታሪክ ታሪክ ነው፡፡ መጥፎም ይሁን ጥሩ፡፡ የእኛ ታሪክ ነው፡፡ ያለፈው ታሪክ አይለወጥም፤ አይከሰስም፡፡ ዛሬ የተሻለ ነገር ከሠራን ግን መልካም ታሪክ ሆኖ ነገ ይጻፋል፡፡ መልካም ታሪክ በሠራን መጠን የትላንቱ አሉታዊና የማንፈልገው ታሪካዊ ገጽታዎች እየተዋጡ ይመጣሉ፡፡ የትላንቱን አሉታዊ የታሪክ ክስተት ለበቀልና ለህቡዕ የጥፋት አጀንዳ እየመዘዝን ከተጠቀምንበት ግን የጥፋት ሠራተኞች እንሆናለን፤ ምድራችንን የደም መሬት እናደረጋታለን፡፡ ከመጥፎ ታሪክ ጋር ሁልጊዜ ስማችን እየተጠራ ይኖራል፡፡ ስለዚህ መልካም ታሪክ ለመሥራት መልካም አመለካከት ይኑረን፡፡

 ትልቁ ችግራችን ችግሮቻችንን ያየንበት ዓይን እንጂ ያለፉም ሆኑ አሁን ያለንበት ችግሮቻችን በራሳቸው ከአሉታዊ አመለካከቶቻችን በላይ አደገኞች አይደሉም፡፡ ችግሮቻችን ከእኛ በላይ ትልቅ አይደሉም፡፡ ችግሮቻችን አደገኛ መሆን የሚጀምሩት እኛ ፈጥረናቸው መፍትሔ በመስጠት ማስወገድ ሲገባን እኛን መፍጠር ወይም መምራት ሲጀምሩ ብቻ ነው፡፡

 
ሰላም፣ ብልጽግና፣ ዕድገት፣ ለውጥ፣ አንድነት፣ ፍቅር በአገራችን ለሚገኙት ብሔር ብሔረሰቦችና መንግሥት ይሁን፡፡


እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
ፀጋአብ በቀለ/ሐዋሳ/ ነሐሴ 4/12/2008 ዓ.ም

ይህን ፅሁፍ ከጠቅላይ ሚንስተሩ እጅ ይደርስ ዘንድ ሼር በማድረግ የበኩሎን ይወጡ።

Tuesday, August 9, 2016

ተገቢ ትኩረት የሚያሻው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ካህናት አቤቱታ!



በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ውስጥ ያሉ አጠቃላይ ማኅበረ ካህናቱ በአቤቱታ ድምጻቸው  ወቅታዊ፤ ትክክለኛና አፋጣኝ ምላሽ የሚያስፈልገው አቤቱታ አቅርበዋል የሚል እምነት አለን። ይህንን አቤቱታ ዝም ብሎ ማለፍ በቤተክርስቲያኒቱ አጠቃላይ ውድቀት ላይ ከኤጲስቆጶሳት አስመራጭ ኮሚቴ ስህተቶች ጋር ተባባሪ መሆን ብለን እናምናለን።
ዘረኝነት፤ ጉቦና የኃጢአት ገመና እንዲህ እንደዘንድሮው ታይቶም፤ ተሰምቶም አይታወቅም። ማኅበረ ቅዱሳን በትክክል ቤተ ክርስቲያኒቱን መቆጣጠሩን ያስመሰከረበት ጊዜ ቢኖር በዚህ የኮሚቴ ምርጫ የታየው የኩነኔና የፍርድ መዝገብ በአደባባይ መነገሩ ነው። ዘረኝነት ቦታውን ተረክቧል። ሙስናው በግልጽ ይታያል። ድሮም ቢሆን በእነጉድ ሙዳይ የሚመራ ኮሚቴ ከዚህ ዓይነቱ ቆሻሻ ተግባር የራቀ ሊሆን እንደማይችል የነበረን ግምት ትክክለኛ ነበር።
የኛም ግምት ስህተት እንዳልነበር የሚያሳየው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ካህናት ድርጊቱን በመመልከት ቀጥተኛ አቤቱታ ማቅረባቸው ሲሆን ለካህናት ጩኸት ጆሮ ሊሰጠው ይገባል እንላለን። ፓትርያርክ ማትያስም ለራሳቸው ክብርና ስም፤ ታላቂቱ ቤተክርስቲያኒም ከተደቀነባት ውርደት ማዳን ካለባቸው ጊዜው አሁን ነው። የካህናቱን አቤቱታ እዚህ ያንበቡ!