Saturday, June 29, 2013

ከሰዓሊና ገጣሚ ገ/ክርስቶስ ደስታ የግጥም ስብስቦች


The painter-poet, was born in 1932 in the Eastern province of Harar, Ethiopia, to father Aleka Desta, a clergyman, and mother W/o Atsede Mariam Wondimagegnehu. Gebre Kristos completed his elementary education in his native town of Harar, and attended the Haile Sellassie 1st School and General Wingate High School. He later joined the Science Department at Haile Sellassie 1st University, presently Addis Ababa University. Gebre Kristos did not pursue a career in his field of study, scientific agriculture, but instead studied art and painted in his spare time. Initially, Gebre Kristos was a self-taught artist, but in his sophomore year, his predilection for art won out, and Gebre Kristos abandoned his studies in hope of becoming a full-time artist.

Sunday, June 23, 2013

በሰማንያ ወአሀዱ ሽፋን የተፈጸመው የጠላት ሴራ ሲገለጥ (ክፍል ሦስት )



ከባለፈው ክፍላችን የቀጠለውን በሰማንያ ወአሀዱ ሽፋን ጠላት አስርጎ ያስገባውን የስህተት መንፈሱን አሰራር በቀጣይነት እንመረምራለን። ጥንተ ጠላታችን በእግዚአብሔር ዋና ቃል ውስጥ ጥቂት የስህተት ቃላትን ሰንቅሮ ማስገባት መቻሉ ጠቅላላ የአምልኮ ሥርዓታችንን እንደፈለገ ለማናጋት በር ስለሚያገኝ በዚህ ዙሪያ አጥብቆ ይሰራል። ይህንን እስትንፋሰ እግዚአብሔር የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ከአበው ሲወርድ እዚህ ዘመን የደረሰውን ጠብቆና ጠንቅቆ በማቆየት፤ ስህተት ሲገኝ በማቃናት፤ የጎደለውን በማረም፤ የሁል ጊዜ አዲስነቱን እንደያዘ፤ ትውልዱን እያደሰ መቀጠል እንዲችል የማድረግ ኃላፊነቱ የቅዱስ ሲኖዶስና የሊቃውንት ጉባዔው ሥልጣን ቢሆንም ምሁራኑ በዐረፍተ ዘመን በሞት ጥላ ሥር አርፈው ቦታቸውን በመልቀቅ ለጊዜው ጥሬ ትርጉሙን እንኳን ለመረዳት አቅሙ በሌላቸውና «ከተንስኡ ለጸሎት» በዘለለ ቃለ እግዚአብሔርን ለመመርመር ድክመት ቤቱን የሰራባቸው ወንበሩ ላይ ያለአቅማቸው በመቀመጣቸው ቅዱሱ መጽሐፍ ሊበረዝ ችሏል። ሊቃውንቱ ወደዳር ተገፍተው በደጀ ጠኝነት ያንጋጥጣሉ።፤ ገሚሱም በጋዜጣ አዟሪነት ያለቦታቸው ተሰማርተዋል። እነ «በአፍ ጤፍ ይቆሉ»  በሊቃውንት ስም የቤተክህነትን ገበያ ያደራሉ። መጋቤ ብሉይ ሠይፈ ሥላሴን የመሳሰሉ ሊቃውንት የደረሱበትን እውቀትና እውነት እንዳይተነፍሱ በድንቁርና መዶሻ ተመትተው እስከወዲያኛው አሸለቡ። ድኩማነ አእምሮዎች ሲያዋክቧቸው የቆዩት ብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ እንኳን በዚህ በጎጋ ጉባዔያተኛ መካከል ባገኙት መንገድ ሁሉ ያካፈሉት ቃለ እውነት ብዙ ዘር ያፈራ ቢሆንም የተመኙትን ያህል ሳይሰሩ ያንን ሁሉ እውቀት ይዘውት የሄዱት ለቤተክርስቲያን ትልቅ ጉዳት መሆኑን እያየነው ነው። 
   እንደው ለመሆኑ ከእሳቸው ወዲያ በነገረ መጻሕፍትና ትርጉም አዋቂነት የሚጠራ ጳጳስ ማን ይሆን? ከተረትና ከእንቆቅልሽ በዘለለ ቃለ እግዚአብሔርን በምልዓትና በስፋት ማስተማር፤ ማረቅ፣ ማቃናት የሚችል አንድም ጳጳስ በዚህ ዘመን አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን የሚቆጨውም ሰው አለመገኘቱ በጣም አሳሳቢ ነው። ሊቃውንት ጉባዔ የተባለው የእነ ክንፈገብርኤል አልታዬና የሊቀ ሥዩማን  ራደ መሥሪያ ቤት ሊቅነቱን ሳናይለት ዘመኑን ፈጠመ።  የሚብሰው ደግሞ ትልቁንና ዋናውን ቃለ እግዚአብሔር/መጽሐፍ ቅዱስ/ ጥንታዊውን የአበው ትርጉምና ሕግጋት ጠብቆ እንደንጹህ የምንጭ ውሃ ኮለል ብሎ የምእመናን የልቡና ጥማት እንዲያረካ ማድረግ አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን የነበረውን መጽሐፍ አደፍርሰው፤ በጥብጠውና ከመርዝ ጋር ደበላልቀው በማቅረብ ሊቃውንት የሚባለውን ክብር ትቢያ ላይ ወድቆ እንዲቀር ማድረጋቸው ሌላው አሳዛኙ ገጽታቸው ነው። 
የሊቃውንት ጉባዔነትን ሥልጣን ተሸክመው የራሳቸውን ግዙፍ ድክመትና ስህተት በማየት ከማረም ይልቅ  የመንደር ላይ ጽሁፎችንና በራሪ ወረቀቶችን እየለቀሙ  አብረዋቸው የሌሉ ሰዎችን በማውገዝ መጠመዳቸው የሊቅነት ስያሜ  አቅጣጫው የጠፋ ይመስለናል። በየተአምሩ፤ በየድርሳኑ፤ በየገድላቱ፤ በየመጽሐፍ ቅዱሱ የተሰነቀረውንና ማን እንዳስገባው የማይታወቀውን ከእግዚአብሔር ቃል ሃሳብና ትርጉም የማይስማማውን እየመረመሩ ማስተካከል ሲገባ ሊቃውንት ጉባዔው የተኛበትን ሥራ በፈቃዳቸው ተረክበው «ይህ፤ ይህ ግድፈት ነው፤ ሊታረም ይገባል፤ የቀደምት አበው አስተምህሮ ሥፍራውን ይያዝ » በማለት በማስረጃ አስደግፈው የጠቆሙ ሰዎችን ጽሁፍ እየለቀሙ አውግዘናል ማለቱ ሊቃውንት ጉባዔው ኮምፓስ እንደሌለው መርከብ ውቅያኖስ ላይ መንሳፈፉን ራሱ አረጋግጧል። ሰዎቹ ይታረም ያሉት የተጻፈውን ስህተት አንስተው እንደ ወንጌል ቃልና እንደአበው አስተምህሮ ይታረም ማለታቸው ወንጀል ሆኖ ሊያስወግዝ ቀርቶ እኛ መሥራት ያቃተንን ስለሰራችሁልን እናመሰግናለን ሊባሉ ይገባ ነበር።
እኛም አቅማችንና ችሎቻን የፈቀደውን ያህል በመረጃና በማስረጃ አስደግፈን  ሁሉም እንዲያውቀው በሰማንያ ወአሀዱ ሽፋን ጠላት አስርጎ ያስገባውን የስህተት ቃል ለማሳየት እንሞክራለን። 

1/ የብቻችን መጽሐፍ እንዴት?

በባለፈው ክፍል ሁለት ጽሁፋችን ለመጠቆም እንደሞከርነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፊት እንደትርፍ የቀኖና መጻሕፍት ትቆጥራቸው የነበሩትና ከ2000 ዓ/ም መጽሐፍ ቅዱስ ህትመት በኋላ ግን እንደዋና  የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የደመረችው የመቃብያን መጻሕፍት ሦስት ክፍሎች ከአይሁዳውያን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ቁጥር ውስጥ የሌለ መሆኑን ለማሳየት ሞክረናል። በ3ኛውና በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበሩት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ትንቢተ ሚልክያስ ያሉትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በ39 ክፍል መድበው ትክክለኛ የእግዚአብሔር ቃል የሆኑ የአይሁዳውያን መጻሕፍትን ሙሉ በሙሉ መቀበላቸውም ታሪክ ያስተምረናል። ከዚህ ውጪ የአይሁዳውያን መጻሕፍት ያልነበሩትን የኦሪት መጻሕፍት እንደብሉይ ኪዳን ለመቀበል የሚያስችል ሌላ ምክንያት የለም። ለእስራኤል ዘሥጋ የተሰጡ የእግዚአብሔር ቃል መጻሕፍት ሙሉ በሙሉ በአዲስ ኪዳን ዘመን ተቀባይነት አግኝተዋል። እነዚህንም የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ብለን እንጠራቸዋለን። ነገር ግን ለሕዝበ እስራኤል ያልተሰጡና በብሉይ ኪዳን መጻሕፍትነት ያልተመዘገቡ መጻሕፍት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከየት አምጥታ እንደብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ቆጠረቻቸው? ምንጫቸው ከየት ነው?  እነዚህንም በትርፍነት የያዘቻቸው በእርግጥ ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሰጥ የለም። ስማቸውን ዘወትር የምታነሳቸው ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን/ እነአትናቴዎስ/ የማያውቋቸውና ዛሬም ድረስ እናቴ የምንላት የኮፕት ቤተ ክርስቲያን የማታውቃቸውን መቀበላችን ለምን? ብለን መጠየቅ አግባብነት አለው። ደግሞም በዓለማችን ላይ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት በአንዱም ውስጥ የሌለ መጽሐፈ መቃብያን ለኢትዮጵያ ብቻ የተሰጠው ከሰማይ ነው ወይስ ከምድር? መቼና እንዴት? ለሚሉት ጥያቄዎች በእርግጥ በቂ መልስ የሚሰጥ የለም።

2/ዲያብሎስ ከክብሩ የወደቀው ለአዳም ስገድ ተብሎ አልሰግድም በማለቱ ነው። 

መጽሐፈ መቃብያን ምንጩ ያለመታወቁ አንዱ ምክንያት የያዘው ሃሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አለመሆኑ ነው። ዲያብሎስ ከክብሩ የወረደው እግዚአብሔር ለአዳም ስገድ ባለው ጊዜ ለሚዋረድልኝ ለአዳምስ አልሰግድም ብሎ እምቢተኛ በመሆኑ ነው ይለናል። ዲያብሎስ ራሱ ይህንን ቃል ሲናገር ያዳመጠው ሰው ማን እንደሆነ ለጊዜው ባይገለጽም መቃብያን ግን የዲያብሎስን ንግግር የሰማ ያህል እንዲህ ሲል አስፍሮታል።
«የሚጠፉ በኔም የሚስቱ ሰዎች ፈጽመው ይበዙ ዘንድ የአዳምም ልጆች ይጠፉ ዘንድ ይህንን በተናገሩ ጊዜ እኔ ደስ ይለኛል። ለሚዋረድልኝ ለአዳም አልሰግድም በማለቴ እግዚአብሔር ስለአባታቸው ስለአዳም ከማዕረጌ አዋርዶኛልና« 3ኛ መቃ 1፤15

ዲያብሎስ ራሱን ከፍ ከፍ ስላደረገና አምላክነትን ስለፈለገ ከማዕረጉ እንደተዋረደ የምታስተምር ቤተ ክርስቲያን፤ የለም ዲያብሎስ የወደቀው ለአዳም ስገድ በተባለ ጊዜ አልሰግድም በማለቱ ነው የሚለውን የመቃብያን መጽሐፍ፤ እስትንፋሰ እግዚአብሔር ያለበት የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ነው በማለት ከ 81 ዱ ጋር አዳብላ ልትቆጥረው እንዴት ቻለች? ጥያቄአችን ነው። አይሁዶቹም እንደብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ያልቆጠሩት፤ ኮፕቶችና ሌሎቹም አብያተ ክርስቲያናት የማያውቁትን ይህንን መቃብያንን ከብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ጋር እንድንደምረው የሚያስገድደን መንፈሳዊ ይዘቱ ምንድነው? ስለ ሰማንያ ወአሀዱ መጽሐፍ ቅዱስ ስንናገር አሰሱንና ገሠሡን ሁሉ በመቆጠር ሊሆን አይገባውም። የአንድ መንፈሳዊ መጽሐፍ ልኬታ ምንጩ፤ መንፈሳዊነቱ፤ ተቀባይነቱና አገልግሎቱ ካልተመዘነ የጠላት አሰራር መግባቱ አይቀሬ ይሆናል። 

3/ ሳምራውያን ትንሣዔ ሙታን የለም ብለው ያምኑ ነበር ወይ?

ስለሰዱቃውያንና ስለፈሪሳውያን ትምህርተ ሃይማኖት የምናገኘው ማስረጃ ያለው በአዲስ ኪዳን ውስጥ ብቻ ነው። ሁለቱም የካህናተ ኦሪት ወገን ቢሆኑም  ሰዱቃውያን ከሞት በኋላ ስላለው ትንሣዔም ሆነ ዘላለማዊነት በፍጹም እምነት የላቸውም። ትንሣዔም፤ መላዕክትም የለም ባዮች ናቸው። ፈሪሳውያን ግን መላእክትም፤ ትንሣዔ ሙታንም መኖሩን  ቢያምኑም ይህ የሚሆነው ለአይሁዳውያን ብቻ ነው የሚል የትምክህት አስተምህሮ ስለነበራቸው ኢየሱስ ለክርስቲያኖች እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል።
«ኢየሱስም፦ ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ አላቸው። ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ እንድትጠበቁ ብዬ ስለ እንጀራ እንዳልተናገርኋችሁ እንዴት አታስተውሉምን? እነርሱም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዲጠበቁ እንዳላላቸው ያን ጊዜ አስተዋሉ» ማቴ 16፤6-12 የአዲስ ኪዳን የትንሣዔ አዋጅ ለተወሰነ ሕዝብ ስላይደለ የፈሪሳውያንን አስተምህሮ ክርስቲያኖች መቀበል ስለሌለባቸው ከዚህ ክፉ እርሾ እንዲጠበቁ አሳስቧል። እንደሰዱቃውያንም ትንሣዔ የለም ከሚል ትምህርትም ራሳቸውን እንዲጠብቁ ጳውሎስ  ሲያስረዳ የስንዴ ቅንጣት እንዴት ፈርሳና በስብሳ  ፍሬ እንደምታፈራ ትንሣዔውን በምሳሌ ሲያስተምር «አንተ ሞኝ፥ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም» 1ኛ ቆሮ 15፤36 ይለናል።
እዚህ ላይ ስለሰዱቃውያንና ስለፈሪሳውያን የትንሣዔ ሙታን እምነት ማንሳት ያስፈለገው ከላይ በቁጥር 3 ላይ ላመለከትነው የጥያቄ ኃይለ ቃል መንደርደሪያ እንዲሆነን ነው። ሰዱቃውያንና ፈሪሳውያን ስለትንሣዔ ሙታን ያላቸው እምነት ከላይ እንደገለጽነው የአዲስ ኪዳን አስረጂ ከሆነ ሳምራውያን የሚባሉት ሕዝቦች ትንሣዔ ሙታን የለም ያሉት መቼ ነው? ብለን እንጠይቃለን። ምክንያቱም መጽሐፈ መቃብያን ሳምራውያን ትንሣዔ ሙታን የለም ብለዋል ይለናልና። 

አጭር ታሪክ፤

ሴኬም የያዕቆብ ምንጭ ያለባት የዐሥሩ ነገድ ሰሜናዊው እስራኤል መቀመጫ ከተማ ነበረች። የሰሎሞን መንግሥት በልጁ በሮብዓም/ ሁለት ነገድ/ በኢየሩሳሌም እና በአገልጋዩ በናባጥ ልጅ በኢዮርብዓም /ዐሥር ነገድ/ በሴኬም ከተከፈለ ( 1ኛ ነገ 12፤20) በኋላ ቆይቶ የሰማርያ ታሪክ ይጀምራል። እሱም የአክአብ አባት ዘንበሪ ሳምር ከሚባለው ሰው ላይ ከሴኬም ከተማ በስተቀኝ ያለውን ተራራ በሁለት መክሊት ከገዛ በኋላ በባለቤቱ በሳምር ስም ተራራ ላይ ቤት ሰርቶ ቦታውን ሰማርያ ማሰኘቱን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። 1ኛ ነገ 16፤24 ከተማው እያደገ፤ ሀገሩም እየሰፋ ሰማርያ ስያሜውን ይዛ ዛሬም ድረስ አለች። ሰማርያ ገሪዛንና ጌባል የሚባሉ የአምልኮ ኮረብታዎቿን ይዛ በመገኘቷ ከሁለቱ ነገድ መዲና ከሆነችው ከኢየሩሳሌም ጋር ኅብረት ያልነበራቸው ከዚያን ጊዜ አንስቶ ነበር። ስለዚህም ጌታችን ከኢየሩሳሌም ወደሰሜናዊ የገሊላ አውራጃ ለመሄድ አማራጭ መንገዱ ሩቅ ስለሆነና የመጣበትም ዓላማ ስለነበረው በዚህች ከይሁዳውያን ጋር ኅብረት ባልነበራት በሰማርያ ማለፉን እናነባለን። (ዮሐ 4፤4)

ሰማርያውያን የእግዚአብሔር የክብሩ መገለጫ ስፍራ ገሪዛን ተራራ እንጂ ኢየሩሳሌም አይደለችም ከማለታቸው በስተቀር፤ የትንሣዔ ሙታንና የገነትንም መኖር ያምናሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፈ መቃብያን የተባለው የአዲስ ኪዳኑን ታሪክ እንደብሉይ ኪዳን ዘመን ትረካ ወደኋላ ጎትቶ የሌለውን ነገር ያስነብበናል።
«ሳምራውያን ግን ሥጋችን ትቢያ ይሆናል፣ አይነሳም ይላሉ» (2ኛ መቃ 14፤1-3) እዚህ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳው መቃብያን የተባለው መጽሐፍ በአዲስ ኪዳን የተጻፈውንና ጌታችን ያስተማረውን ታሪክ ስለሰዱቃውያንና ፈሪሳውያን ይዞ መገኘቱ አንዱ ነጥብ ሲሆን ትንሣዔ ሙታን የለም ያላሉትንና የማይሉትን ሳምራውያንን ከሰዱቃውያን ጋር አብሮ መጨፍለቁ ታሪኩን አስገራሚ ያደርገዋል። ምክንያቱም ሰዱቃውያንና ፈሪሳውያን ስለትንሣዔ በጠየቁት ጊዜ ሳምራውያን ያልነበሩ ሆነው ሳለ መቃብያን ግን ልክ እንዳሉ ቆጥሮ፤ ያልተናገሩትን ስለመናገራቸው መዘገቡ ምን ይባላል? ሳምራውያን የብሉይ ኪዳን እምነት ተከታዮች ስለትንሣዔ ሙታን ያላቸው እምነት ግልጥ ነው። መቃብያን ግን የትም ያልተጻፈውን አንስቶ ይለጥፍባቸዋል።
ዛሬ በቁጥር ከ 800 የማይበልጡ ሳምራውያን በትንሣዔ ሙታንም በመላእክትም መኖር የማመን ጥንታዊ እምነታቸውን ያልተዉ የ10ሩ ነገድ ዘሮች በሰማርያ ይኖራሉ። መቃብያን ግን ይዋሽባቸዋል። ለምን?
(ይቀጥላል)

Sunday, June 16, 2013

«መድኃኒት መልካም ነው፤ መድኃኒትን አላግባብ መጠቀም ግን አደጋ አለው»



(በ2002 ዓ/ም በሳይበር ኢትዮጵያ ድረ ገጽ አባ /ትንሣዔ ላደረጉት ሃይማኖታዊ ክርክር፤ ተሳታፊ ከሰጣቸው መልስ ተስተካክሎ የተወሰደ)
 «የሞኝ ለቅሶ መልሶ፤ መልሶ» እንዲሉ ስንት ያውቃሉ ተብሎ የሚነገርላቸው ትልቅ ሰው የባልቴት ወሬ ሲያንስነብቡን ይገርማል። በመሰረቱ ቅድስት ማርያም እሙ ለእግዚእነ፤ በኅቱም ድንግልና ወለደችው ብሎ ማመን ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኘ እንጂ ከመጽሀፈ ባልቴት የተወረሰ አይደለም። እናትህና «አባትህን አክብር»ያለው መጽሀፍ ቅዱስ የኢየሱስ ክርስቶስን እናት ክብር ዝቅ ማድረግ ጤናማነት አይደለም። ችግሩ ግን ያለው ማርያም ክርስቶስን በሥጋ ስለወለደችውና ይህንን የመመረጥ ጸጋ ለማጉላትና በጣም የሚወዷት አድርጎ ለመሳል የተሞከረበት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነና ይህንኑም «ትንሽ ዱቄት ይዘህ ወዳለው »ተጠጋ እንዲሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነውን እና እሱን የሚያፈርሰውን ሃይለ ቃል ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እየለቀሙ ይሄ ይደግፈናል፤ ይሄ ይረዳናል የሚል ለራስ ማሳመኛና ሌላውን በራስ ትርጉም መከራከሪያ አድርጎ ማቅረብ ምን ይሉታል? እስኪ አባ ከላይ የሰጡበትን የሞገት ሂደቶች እንቃኝ። ተዓምረ ማርያም አባ ገብርኤል አባ ሚካኤል በተባሉ የግብጽ ጳጳስት ዘመን፤ ቆስጠንጢኖስ ብሎ ራሱን በሰየመው ዘርዓ ያዕቆብ በነገሰ በ7ኛው ዐመት ከዓረብኛ ወደ ግዕዝ ተተረጎመ ይላል የተዓምር መቅድም። እውነቱ ይሄ ሆኖ ሳለ አባ ወ/ትንሳዔ ተዓምረ ማርያም ከዘርዓ ያዕቆብ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደነበረ አድርጎ ማቅረብን ምን ይሉታል? አባ በእርግጥ እውነቱን ያውቁታል፤ ችግሩ ግን በስብከተ ወንጌል የካቡት ስምና ክብር ተዓምር በሚሉት መጽሐፍ ልቡ የተሰረቀው ወገን ባንድ ሌሊት ዓይናቸውን ላፈር እንደሚላቸው ስለሚያውቁ ይህንኑ ጠብቆ ለመኖር ስሉ ብቻ ነው ብሎ መገመት ይቻላል። እናም አባ ተዓምር ተብዬው መጽሐፍ ኢትዮጵያ የገባው በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ንግስና መሆኑን ከተዓምር መቅድም አንብበው ይመኑ እንልዎታለን። የሚገርመው ግን ተዓምር ተብዬው መጽሀፍ ከግብጽ መጣሁ ብሎ መቅድሙ ላይ ይቀባጥር እንጂ ይህንን የተዓምር መጽሐፍ የግብጽ (ኮፕቲክ) ቤተክርስቲያን የማታውቀው መሆኑ ነው። ግብጽ የራስዋ የሆኑ  መጻሕፍቶችዋንም እንደዚህ እንደእኛ በማውገዝና በማስፈራራት በ «አሌ ለከ» በወየውልህ ማስፈራሪያ  የማያውቀውን ንባብ እንዲሰማ በማይፈታ ሥልጣን በጽኑ አወገዝን እያሉ የፍርሃት ቀንበር በግድ አይጭኑም። በየትኛውም የግብጽ ቤተክርስቲን ከሰሜን አሌክሳንድሪያ እስከ ደቡባዊ ለክሰር ከተሞች ብንሄድ የኢትዮጵያው ተአምር ተመሳሳዩ በግብጽ የለም። ካይሮ በሚገኘው የኮፕቲክ ቤተመጽሃፍት ውስጥ ከኢትዮጽያ የመጣ ተብሎ በግዕዝ እንደተጻፈ ተቀምጦ ይገኛል። በለንደን ብሪቲሽ ሙዚየም ከግዕዝ በስተቀር የሌላ የማንም ምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት አይገኝም። ታዲያ ዘርዓ ያዕቆብ ከየት አመጣው? ምንአልባት ለእግዚአብሔር እኛ ልዩ ህዝቦች ስለሆንን ከሰማይ ወርዶልን ይሆን? ምን አለበት የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት ለእኛ እንደሚስማማን አድርገን እየተረጎምን አዎ! ወርዶልናል ብንል!! አባ ሌላው መከራከሪያ ነጥባቸው «በክርስቶስ ያመኑቱ ኃይል ይከተላቸዋል» የሚለው የወንጌል ቃል ነው። ስለሆነም የተደረገውን ተዓምራት ሁሉ ልንቀበል እንዲገባን ይመክሩን ዘንድ መሻታቸው ነው። በእርግጥ በክርስቶስ ያሉ ቅዱሳን ድንቅ ተዓምርን ሰርተዋል፤ዛሬም ይሰራሉ። ሌላው ይቅርና አባ እርስዎም የእግዚአብሔር መንፈስ ካደረብዎ ብዙ ተአምራትን ሊሰሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ማንኛውም ተአምር በስመ ክርስቲያን ስለተሰራ እንዳለ ለመቀበል የማንችለው፤
1/በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሲመዘን የሚጋጭ ሆኖ መገኘት የለበትም።
2/በተደረገው ተዓምር ክብሩ ሁሉ ኃይልን ለሰጠ ለክርስቶስ መሆን አለበት። (የሐ/ሥራ14፤15)
3/ ተዓምር ሁሉ እውነት ስላይደለ የእምነትና የምግባር ሚዛኑ መለካት አለበት።(1ኛ ዮሐ4፤1)
ሀ/ ከዚህ አንጻር አጼ ዘርዓ ያዕቆብ የተዓምር መጽሐፍ ሲመዘን በቅድሚያ ጠላቶችችሁን ውደዱ፤ የሚሰድቧችሁን መርቁ የሚለውን የወንጌል ቃል ሽሮ አናምንም፤ አንቀበልም ያሉትን አባ እስጢፋኖስንና ደቀመዛሙርቱን አፍንጫቸውን ፎንነው(ቆርጠው) ጉድጓድ ቆፍረው እስከአንገታቸው በመቅበር ከብት እንደነዱባቸው፤ አስቃይተው ስለገደሏቸው ይህም ታላቅ የጽድቅ ስራ እንደሆነ ተቆጥሮ የዚህን በረከት አሳድርብን ብሎ ሰው ሁሉ እንዲቀበል በውግዘት ያስገድዳል። ይህ እንግዲህ የዘርዓ ያዕቆብን የመግደልና የማሰቃየት ተዓምር፤ ተዓምረ ማርያም በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ማርያም ደስ መሰኘቷን ተጽፎ ይገኛል።  በቅዱስ ወንጌላችን ውስጥ ክርስቲያኖች ስለእምነታቸው መገደላቸውን እንጂ ለማሳመን ሰው ገደሉ የሚል አንድም ቦታ ተጽፎ አናገኝም። ስለዚህ ተዓምረ ማርያም መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደለም ብሎ መደምደም ይቻላል። ሰውን መግደል ለእውነተኛ ክርስቲያኖች እንደክርስናትያናዊ ተአምር አይቆጠርም። ድንግል ማርያምም ሰው የገደለውን ሰው ቅዱስ ትለዋለች ብለን አናምንም። አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ግን ቅዱስ ተብሎ ቤተክርስቲያን ታንጾለት፤ ስም አጠራሩ ጳጉሜን 3 ቀን ይከበራል።
ለ/ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ ጅግራ ናት ብለው ይከራከራሉ እንዲሉ አምልኮ ስዕልን ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ የኦሪቱን የሚናተፍ አውራ ዶሮ አስመስሎ ሙሴ ሁለቱን ኪሩብ እንዲቀረጽ የተነገረውን ቃል ሁሉም ኦርቶዶክሳዊያን መምህራን ሳይጠቅሷት እንደማያልፏት ሁሉ አባም ያቺኑ ጭምብል ብቅ አድርገዋታል። ሙሴ አስመስለህ ቅረጽ የተባለው ለምንድነው? አስመስሎ መቅረጽን የታዘዘው ሙሴ ብቻ ነው ወይስ ሕዝቡ ሁሉ? አስመስሎ የተቀረጸው ምስል የሚቀመጠው በየሰዉ ቤት ወይስ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ብቻ? አስመስሎ የሚቀረጸው ምስል ዓይነት ኪሩብ ወይስ የሰው ምስል? በቁጥርስ ስንት? አጠቃላይ የብሉይ ኪዳን ሕግ ለም? እንዴት? ለማንና መቼ?  የሚለውን አመክንዮአዊ ሕግ ባለማየት የራስን የልብ መሻት ከልብ ለማድረስ መጠቃቀሱ ተገቢ አይደለም እንልዎታለን። በአዲስ ኪዳን ስለምስል የተነገረን ሳይኖር እናድርግ ብንል እንኳን የሙሴ የቅድስተቅዱሳን ኪሩብ ሳይሆን ልባችን ያፈለቀውንና በጭብጥ አልባ ምትሀት(illusion) የምንስላቸውና የምንቀርጻቸውን ሁሉ በህዝበ እስራኤል ዘንድ እንደተደረገ አድርጎ መቁጠር ዋሾ ቀጣፊ ያሰኛል።
     ሙሴ እንዳደረገው እናድርግ ብንል እንኳን  ሙሴ በሚናተፍ አውራ ዶሮ ዓይነት የቀረጸው ኪሩብ የተቀመጠው በመንበሩ ላይ በቅድስተ ቅዱሳን እንጂ በሕዝበ አስራኤል ድንኳን ሁሉ አይደለም። አንድም ቦታ ሕዝቡ የሙሴን ኪሩብ ምስል ሰርቶ በየቤቱ አስቀመጠ የሚል ጽህፉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም። ስለዚህ ሙሴን እንደምሳሌ ማቅረብዎ ከጠላት የተገኘ ምክር እንጂ የመንፈስ ቅዱስ አይደለም። ለሀገር ለመንደሩ፤ለደጅ ለሰፈሩ በመፍቀድ ምንጭና ባለቤት የሌላቸውን ሰዓሊ፤ ጠራቢ ያልሕግ የሰውን ልብ ሊያማልል፤ ዋጋ ገበያ እንዲያወጣለት የሚያጓጓ አድርጎ የሳለውን ሁሉ ሰው እየገዛ እንዲያመልክ እንዲሰግድ ማስተማር የጤንነት አይደለም። ሙሴም ይህንን አላደረገም፤ አላስተማረምም። የስዕልና የምስል አምልኮ መቼ እንደተጀመረ? ማን እንደጀመረ? ሊቃውንቱን ስንት እንዳከራከረ ተጽፎ ይገኛል። ወደኢትዮጵያም ቤተክርስቲያን መቼ እንደገባ ይታወቃል።
        ስዕል መሳልና ለስዕል መስገድ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ስለዚህ የዛሬዎቹ ሰዎች ስለምስል ሙሴን አግዘን ብለው ኪሩብን ከመጥቀሳቸው በፊት ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ውስጥ ምስልና ስዕል በስግደት የማይታወቅበት ጊዜ ነበር። በዚህ ጉዳይ ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ። የሚገርመው ደግሞ ስዕልና ምስል በሙሴ ተፈቅዷል ባዮች ህዝብ እንዲሳሳት ማድረጋቸውን አለማወቃቸው የሚያሳየው በዛሬዋ ቤተክርስቲያን መቅደስ ውስጥ የሚናተፉ አውራ ዶሮ የሚመስሉ ሁለቱ የሙሴ ኪሩብ አለመኖራቸው ነው። ምነው የሙሴን የኪሩብ ምስል ከቤተመቅደሱ አስወገዳችሁት? ሙሴን እንደአጋዥ ምክንያት ስታቀርቡ ሙሴ ያደረገውን መተዋችሁ ለምነው? ወይስ ሙሴ አሻሽሉት የሚል ሕግ ትቶላችሁ ነበር?
      ለህዝቡ በምክንያትነት ኪሩቦቹን ስትጠቅሱ እናንተ የሱን አርአያና ምሳሌ ተከትላችሁ ቤተመቅደሱ ውስጥ እንደሚናተፍ አውራ ዶሮ ግራና ቀኝ አለማስቀመጣችሁ የናንተ ሥራ ከሙሴ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ምስክር ነው። ስዕልም ይሁን ምስል ለታሪክ አስረጂ፤ ለመረጃ፤ ለትምህርት አስረጂና ጠቃሚ ሊሆን ከሚችል በላይ በየቤታችን ወይም በየመቅደሱ እጣን እንድናጥን፤ እንድንሰግድ፤ ከፊት ለፊታችን አስቀምጠን እንድንጸልይባቸው አንድም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት የለንም። እግዚአብሔር የሚገለጥበትን መንገድ ለሙሴ በብሉይ ኪዳን ተናግሯል። በአዲስ ኪዳንም በጾም፤ በጸሎት፤ በምጽዋትና በክርስቲያናዊ ምግባር ከተጋን የእግዚአብሔርን መልስ ለማግኘት፤ መልዕክት ለመቀበል፤ የሚገለጥበት መንገድ ያለራሱ ማንም አያውቀውም። እግዚአብሔርን ለመለመን በቅዱስ ሚካኤል ስም ካቶሊካዊው ጉይዶ ሬኒ በ1636 ዓ/ም በልቡ አቅንቶ፤ ችሎታውን ተጠቅሞ የሳለውን ስዕል ከገበያ ገዝቶ በመስገድ ወይም በእጣን ማጠን በዚያ በኩል እግዚአብሔርን መፈለግ እብደት ነው። ጉዶ ሬኒ ዛሬ ላይ ይህንን ቢያይ ኖሮ ምን ይል ይሆን?

                                 (www.artcyclopedia.com)
ሐ/ ሌላው ችግራችሁ የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት አለቦታው በመጠቀም የልባችሁን መሻት ሁሉ በእሱ ቻይነት ካባ ለመሸፈን መሞከር ነው። ተአምር ሁሉ እውነት አይደለም ያልኩበት 3ኛው ነጥቤ ወንጌል፤ አባት አባ ያለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማይ የሚገባ አይደለም እንዳለው ሁሉ ተዓምር ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው ብለን አንቀበልም። በዚህ ዓለም ብዙ መናፍስት ገብተዋልና። ሲሞን መሰርይ የሰማርያ ከተማ ድንቅ ተዓምር ሰሪ ነበር። ግን ተዓምሩ ከእግዚአብሔር መንፈስ አልነበረም። ታዲያ እነዚህ የኛ ሰዎች እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ስለሆነ በኛ ተጽፈው የተገኙትን ተአምራት ሁሉ ድንቅ ስራ እያላችሁ ተቀበሉ ይሉናል። እስኪ አንዱን እንመልከት፤ በገድለ ተ/ ሃይማኖት የተሰራ ተዓምር ነው። አባ ተ/ ሃይማኖት «ባህር አልቅም» የተባለ ሰይጣን በመስቀል ምልክት አማትበው ከያዙት በኋላ አሳምነው፤ አስተምረው፤ አጥምቀው፤ እግዚእ ኀረዮ ብለው ስመ ክርስትና ሰጥተው ካበቁ በኋላ አመነኮሱት የሚል አስነብበበውናል። በእነሱ እንዴት ብሎ መጠየቅ አይቻልም፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ነዋ!!! ጥሩ የበደል መሸፈኛ ምክንያት!!
እኛ የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት ብናምንም ከሃሌ ኵሉነቱን አለአግባብ ሲጠቀሙበት ማየት ስለማንፈልግ እንዲህ እንጠይቃቸዋለን።
1/ ሰይጣን ስጋና ደም አለው ወይ? ሲገርዝስ ደም ይፈሰዋል? ግርዛትስ ክርስቲያን ለመሆን መመዘኛ ነው? «በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና» ገላ 5፤6
2/ ሰይጣን ንስሃ ይገባል ወይ? በወንጌልስ ሊያምን ይችላል?
3/ የክርስቶስ ሞትና ትንሳዔ (ሎቱ ስብሐት) ሰይጣናትን ያካትታል ወይ? ሰይጣን ዘላለማዊ ህይወትን ወርሶ ገነት ገባ የሚሉ ሰዎችን አባ፤ ምን ይሏቸዋል?
መቼም በዚህ ላይም ጉድ እንዲያስነብቡን እንጠብቃለን። በበኩሌ የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት አለቦታው መጠቀም በእግዚአብሔር ላይ ከማሾፍ የተለየ አድርጌ አላየውም። መጠያየቅና እውነቱን ከመረዳዳት ባሽገር ጴንጤ፤ተሃድሶ፤ካቶሊክ፤መናፍቅ ወዘተ መባባል የትም አያደርስም። መድኃኒት መልካም ነው፤ መድኃኒትን አለቦታው መጠቀም ግን አደጋ አለው፤ የእግዚአብሔርን ሁሉን ቻይነት ለልባችን መሻት ሁሉ ማዋላችን ይብቃ። ከእውነቱ እንታረቅ። አስተዋይ ልቦና ይስጠን።

Wednesday, June 12, 2013

ጥያቄ፤ በክርስትና ሕይወቴ ኃጥአትን እንዴት ማሸነፍ እችላለሁ?






       ምንጭ፤    (michaelyemane.blogspot.com) 


ጥያቄ፤ በክርስትና ሕይወቴ ኃጥአትን እንዴት ማሸነፍ እችላለሁ?
መልስ፤ በጥረታችን ኃጥአትን ለማሸነፍ ይረዳን ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ የተለያዩ መንገዶችን ያቀርባል፡፡ በዚህ ዕድሜ በኃጥአት ላይ ፍጽሞ በሚገባ ባለድል አንሆንም (1ኛ ዮሐንስ 1፡8)፤ ነገር ግን ያ አሁንም የእኛ ግብ ሊሆን ይገባል፡፡ በእግዚአብሔር ዕርዳታ እና የቃሉን መርሆች በመከተል በሂደት ኃጥአትን ማሸነፍ እና በበለጠ ክርስቶስን መምሰል እንችላለን፡፡
በጥረታችን ኃጥአትን ለማሸነፍ መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቅሰው የመጀመሪያው መንገድ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ሰጥቶናል ስለዚህም በክርስትና ህይወታችን ባለድል መሆን እንችላለን፡፡ እግዚአብሔር ወደ ገላትያ ሰዎች 5፡16-25 ውስጥ የሥጋ ሥራዎችን ከመንፈስ ፍሬዎች ጋር ያነጻጽራል፡፡ በዚያ ምንባብ ውስጥ በመንፈስ እንድንሄድ ተጠርተናል፡፡ ሁሉም አማኞች አስቀድሞ መንፈስ ቅዱስ አላቸው፤ ነገር ግን ይህ ምንባብ ለእሱ ቁጥጥር እየተገዛን በመንፈስ መሄድ እንደሚገባን ይነግረናል፡፡ ይህ በቋሚነት መንፈስ ቅዱ በህይወታችን ውስጥ ሥጋን ከመከተል ይልቅ በተከታታይ የመንፈስ ቅዱስን ምሪት መከተል መምረጥ ማለት ነው፡፡
መንፈስ ቅዱስ ማድረግ የሚችለው ልዩነት፤ በመንፈስ ቅዱስ ከመሞላቱ በፊት ኢየሱስን ሦስት ጊዜ በካደው በጴጥሮስ ህይወት ታይቷል፤ እናም ከዚህ በኋላ ክርስቶስን እስከሞት ድረስ እንደሚከተለው ተናግሮ ነበር፡፡ በመንፈስ ከተሞላ በኋላ በጴንጤቆስጤ በዓል ላይ በአደባባይ በድፍረት ለአይሁዶች ነገራቸው፡፡
የመንፈስን ምሪት ላለማጥፋት ለመሞከር በመንፈስ እንሄዳለን (በ1ኛ ተሰሎንቄ 5፡19 እንደተነገረው) እና በምትኩ በመንፈስ መሞላትን እንፈልግ (ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5፡18-21)፡፡ አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ እንዴት ይሞላል? በብሉይ ኪዳን ውስጥ እንደነበረው ከሁሉ በፊት የእግዚአብሔር ምርጫ ነው፡፡ እሱ እንዲከወን የፈለገውን ሥራውን የሚያስፈፅሙ ግለሰቦችን መረጠ እና በመንፈሱም ሞላቸው (ኦሪት ዘፍጥረት 41፡38፤ ኦሪት ዘፀአት 31፡3፤ ኦሪት ዘዳግም 24፡2፤ 1ኛ ሳሙኤል 10፡10) በእግዚአብሔር ቃል ራሳቸውን እየሞሉ ያሉትን እነዚያን ሊሞላቸው እንደሚመርጥ ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5፡18-21 እና ወደ ቆላስያስ ሰዎች 3፡16 ውስጥ ማረጋገጫ አለ፡፡ ይሄ ወደ ሁለተኛው መንገድ ይመራናል፡፡
የእግዚአብሔር ቃል፤ መጽሐፍ ቅዱስ፤ እግዚአብሔር ለየትኛውም በጎ ሥራ ሁሉ እኛን ለማስታጠቅ ቃሉን ሰጥቶናል ይላል (2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16-17)፡፡ እንዴት መኖር እንዳለብን እና ምን ማመን እንዳለብን ያስተምረናል፣ የተሳሳቱ ጎዳናዎችን በመረጥን ጊዜ ይገልጥልናል፣ ወደ ትክክለኛውም ጎዳና እንድንመለስ እና በዚያ ጎዳና እንድንቆይም ይረዳናል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ሕያው እና የሚሰራ እንደሆነ፣ ሥር ለመስደድ ወደ ልቦቻችን ዘልቆ ለመግባት እና ጥልቅ የሆኑትን የልባችንን ኃጥአቶች እና አመለካከቶችን ማሸነፍ እንደሚችል ወደ ዕብራውያን ሰዎች 4፡12 ይነግረናል፡፡ ዘማሪው በመዝሙረ ዳዊት 119 ውስጥ ስለ እሱ የህይወት ቀያሪነቱ ኃይል በጥልቀት ይናገራል፡፡ ኢያሱ ጠላቶቹን የማሸነፍ ውጤታማነት ቁልፉ ይህንን መንገድ ያለመርሳት እንዳልሆነ ነገር ግን በምትኩ በቀን እና በማታ ማሰላሰል እና እሱን መታዘዝ እንደሆነ ተነግሮታል፡፡ እግዚአብሔር ባዘዘ ጊዜ እንኳ በውትድርናው ስሜት የማይሰጥ ነገር ባይሆንም ይህን አደረገ፤ እና ይሄ ለተስፋይቱ ምድር ላደረገው ጦርነት የድሉ ቁልፍ ነበር፡፡
እኛ ራሳችን ብዙውን ጊዜ በቀላሉ የምናየው መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱሶቻችንን በመሸከም ወይም የቀን ጥሞና ወይም በቀን አንድ ምዕራፍ እያነበብን ምልክታዊ አገልግሎት እንሰጣለን፣ነገር ግን እሱን ማሰቡን ፤ እሱን ማሰላሰሉን ወይም በኑሮዎቻችን ላይ ተግባራዊ ማድረጉን ትተናል፣ እሱ የሚገልጣቸውን ኃጥአቶቻችንን መናዘዝ ወይም ለእኛ ለሚገልጣቸውን ስጦታዎች እግዚአብሔርን ማመስገን ትተናል፡፡ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ በሚመጣበት ጊዜ እኛ ብዙውን ጊዜ ምግብ ያስጠላቸው ወይም አመጋገባቸው የተዛባብን ነን፡፡ ከቃሉ በመመገብ በመንፈሳዊው እንዲያው በህይወት እንዲያቆየን ያህል (ነገር ግን ጤናማ እና የሚፋፉ ክርስቲያኖች እንድንሆን ፈጽሞ የሚበቃንን ያህል አንበላም) ወይም ብዙ ጊዜ ልንመገብ እንመጣለን ነገር ግን መንፈሳዊ ምግብን ከእሱ ለማግኘት ለረጅም ጊዜ በፍጹም አናሰላስለውም፡፡
እሱ ጠቃሚ ነው፣የእግዚአብሔርን ቃል በየቀኑ የማጥናትና የማሰላሰል ልምድ ካላደረግህ ያን ማድረግ ትጀምራለህ፡፡ ጥቂቶች የሚረዳ ጅማሬ ሆኖ አግኝተውታል፡፡ ከእሱ ያገኘኸውን አንድ ነገር እስከምትጽፍ ድረስ ቃሉን ላለመተው ልምድ አድርገው፡፡ ጥቂቶች እነርሱን በተናገራቸው ዙሪያ ይለወጡ ዘንድ እንዲረዳቸው በመጠየቅ ወደ እግዚአብሔር የሚደረጉትን ፀሎቶች ይመዘግባሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ መንፈስ የሚጠቀምበት መሳሪያ (ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6፡17)፤ እግዚአብሔር መንፈሳዊ ውጊያዎቻችንን እንድንዋጋ የሰጠን ጠቃሚ እና ዋነኛ የጦር ዕቃ አካል (ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6፡12-18) ነው፡፡
በኃጥአት ላይ ለምናደርጋቸው ውጊያዎቻችን ሦስተኛው ዋነኛ መንገድ ፀሎት ነው፡፡ አሁንም ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖች የከንፈር አገልግሎት የሚሰጡበት መንገድ ነው ነገር ግን ጥቅሙን ደካማ ያደርጋል፡፡ የፀሎት ስብሰባዎች፣ የፀሎት ጊዜያቶች ወ.ዘ.ተ. አሉን ነገር ግን ጸሎትን የጥንቷ ቤተክርስቲያን በምትጠቀምበት መንገድ አልተጠቀምንበትም (የሐዋርያት ሥራ 3፡1፣4፡31፣6፡4፣13፡1-3)፡፡ ጳውሎስ ያገለግላቸው ለነበሩት እንዴት ይፀልይ እንደነበር በተደጋጋሚ ይጠቅሳል፡፡ እግዚአብሔር ጸሎትን በተመለከተ የሚያስደንቁ ተስፋዎችን ሰጥቶናል (የማቴዎስ ወንጌል 7፡7-11፣ የሉቃስ ወንጌል 18፡1-8፣ ዮሐንስ ወንጌል 6፡23-27፣ 1ኛ ዮሐንስ መልዕክት 5፡14-15)፣ እና ጳውሎስ ለመንፈሳዊ ውጊያ በመዘጋጀት ምንባቡ ውስጥ ፀሎትን ያካትታል (ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6፡18)፡፡
በኑሮዎቻችን ኃጥአትን በማሸነፉ ፀሎት እንዴት ጠቃሚ ነው? ልክ ከጴጥሮስ ክህደት በፊት በጌተሰማኔ የአትክልት ሥፍራ ለጴጥሮስ የክርስቶስ የሆኑ ቃላቶች አሉን፡፡ ኢየሱስ እየጸለየ ጴጥሮስ እየተኛ ነው፡፡ ኢየሱስ አነቃውና እናም አለው “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው።”(የማቴዎስ ወንጌል 26፡41) እኛ እንደ ጴጥሮስ ትክክል የሆነውን ማድረግ እንፈልጋለን ነገር ግን ጥንካሬውን እያገኘን አይደለም፡፡ መፈለጋችንን ፣ ማንኳኳታችንን፣ መጠየቃችንን ለመቀጠል የእግዚአብሔርን ተግሳጽ መከተል ያስፈልገናል እናም ያ የምንፈልገውን ጥንካሬ ይሰጠናል (የማቴዎስ ወንጌል 7፡7)፡፡ ጸሎት ምትሃታዊ ዘይቤ አይደለም፡፡ ጸሎት በቀላሉ የእኛን የራሳችንን ድክመትና የእግዚአብሔርን የማይወሰነውን ኃይል ማረጋገጥ እና እኛ ማድረግ የምንፈልገውን ሳይሆን እሱ እንድናደርገው የሚፈልገውን ለማድረግ ለዚያ ጥንካሬ ወደ እሱ መዞር ነው (1ኛ ዮሐንስ መልዕክት 5፡14-15)
ኃጥአትን ለመማረክ በምናደርገው ጦርነታችን ውስጥ አራተኛው መንገድ፤ የሌሎች አማኞች ህብረት፤ ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ኢየሱስ ደቀመዛሙርቱን በላከበት ጊዜ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው (የማቴዎስ ወንጌል 10፡1)፡፡ በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ያሉ ሚሲዮኖች በአንድ ጊዜ አንድ ሆነው አልወጡም ነበር ነገር ግን ሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆነ ማህበር ነበር፡፡ ኢየሱስ አንድ ላይ መሰብሰባችንን እንዳንተው ነገር ግን ያን ጊዜ በፍቅር እና በመልካም ሥራዎች እርስ በራሳችንን ለማበረታታት እንድንጠቀምበት አዞናል (ወደ ዕብራውያን ሰዎች 10፡24)፡፡ አንዳችን ለአንዳችን ስህተታችንን እንድንናዘዝ ይነግረናል (የያዕቆብ መልዕክት 5፡16) በብሉይ ኪዳን በጥበብ መጽሐፍ ውስጥ ብረት ብረትን እንደሚስል ተነግሮናል፥ ስለዚህ አንድ ሰው ሌላውን ይስላል (መጽሐፈ ምሳሌ 27፤17)። በቁጥሮች ውስጥ ጥንካሬ አለ (መጽሐፈ መክብብ 4፡11-12)፡፡
ብዙ ክርስቲያኖች የሚከብዱ ኃጥአቶችን በማሸነፉ ረገድ ኃላፊነትን የሚወስድ ወዳጅ መኖር በጣም ትልቅ ጥቅም መሆን እንደሚችል ያን አግኝተዋል፡፡ ከአንተ ጋር ሊያወራ፤ ሊፀልይ፣ ሊያበረታታህ፤ እና እንዲያውም የሚገጽህ የሚችል ሌላ ሰው ማግኘት ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ፈተና ለሁላችንም ያለ ነው (1ኛ ቆሮንቶስ 10፡13) ኃላፊነትን የሚወስድ ወዳጅ ወይም ኃላፊነትን የሚወስድ ማህበር መኖሩ እንዲያውም በጣም ከባድ የሆኑትን ኃጥአቶችን ለማሸነፍ የሚያስፈልገንን የመጨረሻውን የማበረታቻ እና የመነሳሳት መጠን ሊሰጠን ይችላል፡፡
አንዳንድ ጊዜ በኃጥአት ላይ ድል መንሳት በፍጥነት ይመጣል፡፡ ሌላ ጊዜ ድል በጣም በዝግታ ይመጣል፡፡ እግዚአብሔር የእሱን መንገዶች ስንጠቀም ለውጥን በህይወታችን በሂደት እንደሚያመጣ ቃል ገብቷል፡፡ ኃጥአትን ለማሸነፍ ጥረታችንን በቀጣይነት መቀጠል እንችላለን ምክንያቱም እሱ በቃሉ ታማኝ እንደሆነ እናውቃለን፡፡

Thursday, June 6, 2013

የፕሬዚዳንት ሞርሲና የፓርቲዎች ጉባዔ በዐባይ ጉዳይ


መምሪ በተባለው የግብጽ ቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት የተደረገ ውይይት) 

የነጻነትና ዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር እንዲህ አሉ፤ 

«ድምጼን አሰምቼ በግልጽ መናገር የምፈልገው ነገር ሁሉም አማራጮች ለእኛ አስፈላጊዎች መሆናቸውን ነው። እናም ሁሉንም አማራጮች እንደግፋለን፤ ነገር ግን ሂደቱ በየደረጃው መሆን ይገባዋል። የንግግር ግንኙነታችን ሂደቱን መቀየር ካልቻለ ወደዓለም ዐቀፉ የግልግል አካል እናቀርበዋለን። ይህም ካልተሳካ ማንም ሊገምተው እንደሚችለው የውሃ ዋስትናችንን ለመከላከል ወደሌላ አማራጭ እንገባለን። ምክንያቱም የውሃ ዋስትና  ለእኛ የሞት ወይም የሕይወት ጉዳይ ነውና።


የአልኑር ፓርቲ ፓርቲ ሊቀመንበር በተራቸው እንዲህ አሉ፤

አሁን እየተካሄደ ባለው የዐባይ ስምምነት ማዕቀፍ ላይ ግብጽ ከተስማማች አደገኛ ስትራቴጂካዊ ስህተት መፈጸሟ ነው። ምክንያቱም በዚህ ጉዳይ ላይ አሜሪካ፤ እስራኤልና ኢትዮጵያ ከጉዳዩ ጀርባ አሉና። ምክንያቱም በዚህ ስምምነት ግብጽን በመጉዳት ርካሽ የፖለቲካ ጫና ለማሳረፍ ሲሉ ነው። እኛም እንደእነሱ ለማድረግ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ 35%  ኦሮሞ ስለሆነና ኦሮሞም ለመገንጠል የሚዋጋለት ኦነግ የሚባል ድርጅት ስላለው ለእሱ ሁለመናዊ ድጋፍ ማቅረብ አለብን። በሀገር ቤት ያለው ፖለቲካዊ የተቃውሞ መድረክ ደካማና ልፍስፍስ ስለሆነ ለመገንጠል በሚዋጉት እንደኦጋዴን ነጻነት ግንባር ያሉትን መደገፍ ይገባናል። ይህም በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የተቀናጀ ጫና እንድናሳርፍ ያስችለናል። ይህ ሁሉ ተደርጎ  ውጤት ካላስገኘልን ሌላው አማራጭ ለግብጽ ኅልውና አደገኛ የሆነ ማንኛውንም ግድብ ለማውደም የምንችልበት ሁኔታ መፍጠር ነው። ለዚህም አስተማማኝ የደኅንነት መረጃ መኖር አለበት። ምክንያቱም አንዳንድ ጠበብቶች ግድቡን መጀመር በራሱ አደገኛና ጦርነት የማወጅ ያህል እንድንቆጥር በቂ ማስረጃ ነው እያሉን ነውና።

የአል አዝሃር ዩኒቨርሲቲ የሃይማኖት መምህር የሆኑት ደግሞ በተራቸው፤

አስታውሳለሁ፤ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግብጽ በመጣበት ወቅት በግብጽ ሕዝብ ላይ አላግጦ ነው የሄደው። ዐባይ ክንፍ የለውም፤ ወደእስራኤልም አይበርም አለ፤ ነገር ግን ማንኛውም ህዝብ እንደሚያውቀው የግብጽ ሕዝብም ያውቃል። የዓባይ ወንዝ በቀይባህር ስር የሚሄድበት የራሱ የቧንቧ መስመር ስውር ክንፍ አለው። ማንም ሀገር በቧንቧ መስመር ውሃ ወደሀገሩ እንደሚያስገባ ይታወቃል፤ ሲሉ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን በመቃወም ዐባይ ክንፍ አለው ብለዋል።  

የገድ አልተውራ ፓርቲ ሊቀመንበር ደግሞ ተራቸውን ጠብቀው እንዲህ አሉ፤

እንደዚህ ይባል ወይም አይባል እንደሆነ አላውቅም፤ ነገር ግን አንዱ ጓደኛዬ ቅድም እንዳለው ኢትዮጵያ ብዙ ተቃዋሚዎች እንዳሏት ይታወቃል፤ እዚያም የተለየ እንቅስቃሴ እያየን ነው። የግብጽ ኤምባሲ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሩ ምን ያደርግልናል? አስፈላጊ ነገር አሁን የፖለቲካና የመረጃ ክፍሎቻችን ብቻ ናቸው። በኢትዮጵያ ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ተመርኩዘን ሚና መጫወት አለብን። ይህንን ማስኬድ መቻል በትንሽ ወጪ ብዙ መስራት የሚያስችለን ሲሆን አጸፋዊ አደጋውም የቀነሰ ነው። በደንብ አድርገን በውስጥ ጉዳያቸው ብዙ መስራት ከቻልን ማዳከም ይቻለናል። አንድ የኢትዮጵያ ጋዜጣ እንዲህ አለ፤ ግብጽ የጦርነት ሃሳብ የላትም። ይህንን የማድረግ ብቃት የላትም፤ ሚሳይል የላትም፤ አውሮፕላን የላትም፤ ቢኖራትም ሱዳን በክልሏ ላይ ይህ እንዲደረግ አትፈቅድም ብሏል። በእርግጥም የሱዳኖች ሁኔታ ለእኛ በጣም የሚያሳምም ነው። ሁኔታዋ ማድረግ ከሚገባት አንጻር ሲታይ በጣም ደካማ ነው።  በእኛም በኩል መረጃ ፍሰት ችግር አለ።  ግብጽ የጦር አውሮፕላን ልትገዛ ነው፤ በአየር ላይ ነዳጅ መሙላት የሚችል አውሮፕላን አላት ወዘተ የሚሉት መረጃዎች መውጣት አለባቸው፤ በእርግጥ ባይሆንም እንኳን መረጃው በዲፕሎማሲያዊ ጥረታችን ላይ የራሱን ተጽዕኖ ያሳርፋል።

የሪፎርምና ደቨሎፕመንት ፓርቲ ሊቀመንበር ደግሞ ተራውን ተረክበው እንዲህ ዶለቱ፤

እኛ ባለን ግንዛቤ የብሔራዊ ቡድናችን ኢትዮጵያ ሄዶ ባደረገው ጫወታ ተጽእኖ በመፍጠር ማሸነፍ መቻሉን ነው። ብሔራዊ ቡድናችን የአፍሪካ ሻምፒዮን መሆኑና እጅግ በአመርቂ ውጤት ጫና መፍጠር መቻሉ በራሱ የሚያሳየው እውነትም ግብጻውያን ጫና የመፍጠር ጥበብ እንዳለን ነው። ትልቅም ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም አለን። የግብጽን ቤተክርስቲያንና የአልሃዛር ስኮላሮችን በዚህ ጉዳይ መጠቀም እንችላለን። አንዳንዶች የጦርነት አማራጮች ሊኖር እንደሚችል ያወራሉ። የሚወራውን ነገር ለመተግበር አስቸጋሪ ነው። እንደዚህ ዓይነቱን እሳቤ መነቀፍ ይገባዋል። ከዚህ ይልቅ የግንኙነት ምህዋራችንን ከኤርትራ፤ ከሶማሊያና ከጅቡቲ ጋር ብናደርግ ለደኅንነታችን ክፍሎች ትልቅ መስክ ነው።  ይህንን ማድረግ ጥሩ ከመሆኑም ባሻገር ግንኙነት የማድረግ መብታችንም እንደመጠቀም ስለሆነ ተገቢ ነው። ተስፋችን ሲጨልም ደግሞ ሃሳባችንን መፈጸም የምንችልባቸው በተዘዋዋሪ አንድ መቶ መንገዶች ስላሉን ሁሉንም እናደርጋለን።

የኢስላሚክ ሌበር ፓርቲ ሊቀመንበር ደግሞ ምኞታቸውን ከፍ አድርገው ተናገሩ፤

እኔ ከጠላቶቻችን ጋር ጦርነት የምናደርግበት ቀን ናፍቆኛል፤ በእርግጥም ከእስራኤልና ከአሜሪካ ጋር። ጦርነቱ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሎ ተገቢውን ፍትህና እርጋታ የሚያመጣ መሆን ከቻለ። ምንም እንኳን ይህ ውይይት ምስጢራዊ ውይይት እንደመሆኑ ሁሉንም ነገር በምስጢር መያዝ ይገባናል። ውይይታችን ወደሚዲያ ሾልኮ መውጣት የለበትም። በእህታችን በባኪናም በኩል በግልጽ ከሚወጣው በስተቀር። ሕዝባዊ የሀገራዊ ደኅንነት እቅድ በግልጽ እንዲኖር እንፈልጋለን። እኛ እንዲህ ቢሆንም እንኳን………. (አቋረጡ) ቀጠሉና እሺ…..መልካም………እኔ የማነሳቸው ነጥቦች አግባብ ከመሆናቸው ጀርባ በእርግጥም ምንም ምስጢርነት የላቸውም። ውጊያችን ከአሜሪካና ከእስራኤል ጋር እንጂ ከኢትዮጵያ ጋር አይደለም። ስለዚህ ውጊያችንን ለማስኬድ ፤ ይህ የኔ ሃሳብ ነው……….( ፕሬዚዳንት ሙርሲ ጣልቃ ገቡና፤ ይህ ውይይት እኮ በቀጥታ ስርጭት እየሄደ ነው ያለው! አሉ) የኢስላሚክ ፓርቲው ሊቀመንበርም፤ እኔም የምስጢር እቅድ ወይም ፕላን ማብራሪያ እየሰጠሁ አይደለም!  ሲሉ በጉባዔው ሳቅ ሆነ።  ቀጥለውም «እኔ ያልኩትን እኮ ማንም ሀገር የሚያደርገው ነው፤ በሌሎችም ሲባል የቆየ ነው» አሉ። (የጉባዔው ረጅም ሳቅ!!)
ማንም ሀገር ለከባቢያዊ ጥቅሙ የሚያደርገው ነው። እኔ ለግብጽ ሕዝብ የምለው ማንም ተነስቶ የውሃ አቅርቦትህን ሊዘጋ አይችልም ነው። የግብጽን ሕዝብ የዓለም አደገኛው የጽንፈኝነት መንገድ እንዲገባ ካልፈለጉ በስተቀር ይህን አያደርጉም። እስኪ አስቡት 80 ሚሊዮን ግብጻዊ ውሃ ሲዘጋበት በአሜሪካና በእስራኤል ላይ ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል?

ፕሬዚዳንት ሙርሲ፤ የልባቸውን በልባቸው ይዘው፤ በዲፕሎማሲያዊ  ቋንቋ ደስ የተሰኙበትን ገታራ ውይይት አለዝበው እንዲህ ሲሉ ደመደሙ።  

«እኛ ለሰሜንና ደቡብ ሱዳናውያን የከበረና የተትረፈረፈ አክብሮት አለን» አሉና የሱዳንን ዳተኝነት ሸነገሉ። «ውሳኔዎቻቸውን ሁሉ እናከብራለን» ሲሉ በማሞካሸት ጠላት ማፍራት እንደማይገባ በውሰጠ ታዋቂ ጠቆሙ። እንደዚሁም ሁሉ «ለኢትዮጵያ ሕዝብም ያለን አክብሮት ተመሳሳይ ነው!» አሉና ዙሪያ ገባህን እሳት እንለኩሳለን ሲል ለቆየው ጉባዔ ማለስለሻ ቫዝሊን ቀቡት። እኛ የትኛውንም ጀብደንነት ጀማሪዎችና በማንም ላይ አሳቢዎችም አይደለንም አሉ። ነገር ግን አሉ ፕሬዚዳንት ሞርሲ፤ ነገር ግን መታወቅ ያለበት  እያንዳንዷን የዐባይ ውሃ ጠብታ ለመከላከል እጅግ የጠነከረ እርምጃ የምንወስድ መሆናችን ነው። ለእያንዳንዷ ጠብታ ውሃ!
(ተፈጸመ)

Wednesday, June 5, 2013

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት እንዲሰነጣጠቅ ሲኖዶስ የወሰነው ለምንድነው?( ከዚህ በፊት የቀረበ ጽሁፍ)

            መንበረ ፓትርያርክ ቅ/ማርያም ቤ/ክ 1921 ዓ/ም (ፎቶ ምንጭ፤ ሰሎሞን ክብርዬ) 
          
ይህንን ጽሁፍ በጥቅምት/2004 ዓ/ም ሲኖዶስ ማብቂያ ላይ በዚሁ መካነ ጦማራችን አውጥተን ነበር። ዛሬ እንደገና መድገም ያስፈለገን በወቅቱ ቅዱስ ሲኖዶስ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን አራት ቦታ መከፋፈሉን በመቃወም ፤ ተገቢ እንዳልሆነና ጥናት ያልተደረገበት አሠራር ስለሆነ ውጤቱ ኪሳራ መሆኑን አመልክተን የነበረው በትክክል እንዳልነው ውጤቱ ኪሳራ ሆኖ በመገኘቱ ቅ/ሲኖዶስ በ2005 ዓ/ም ጉባዔው  ከግብታዊ ውሳኔው በመውጣት ሀገረ ስብከቱን ወደነበረበት ሲመልስ በማየታችን ነው። አሁንም ደግመን የምንለው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ወደነበረበት የቀድሞ ተቋማዊ መልኩ መመለስ ብቻ ሳይሆን የሥልጣን ክፍፍል እንዲኖረው ማስቻል ገና የሚቀረው ሂደት ነው እንላለን። ይኸውም የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በሠራተኛ ብዛት፤ በገቢ አቅም፤ በማዕከላዊ ተቋምነቱ ሠፊና ትልቅ ሀ/ስብከት ስለሆነ ሥልጣንን ሁሉ አንድ ቦታ ሰብስቦ እንዲይዝ የሚያደርገው ሁኔታ ስላለ ከሙስና፤ ከአድልዎ፤ ከፍትህና ውሳኔ አሰጣጥ መዛባት አንጻር ለቁጥጥር የማያመች፤ የአሰራር ዝርክርክነት የሚያስፋፋ ችግር እንደበፊቱ ተመልሶ ሊመጣ ስለሚችል ሥልጣን መከፋፈል አለበት እንላለን። ይህንንም የሥልጣን ክፍፍል በታወቀና በተወሰነ የአሠራር ደንብ ላይ ተመርኩዞ በወረዳዎች ደረጃ ወደታች መውረድ ይኖርበታል። ስለሆነም እንደእኛ እምነት ሀገረ ስብከቱን በአራት የወረዳ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በተሟላ አደረጃጀት አዋቅሮ ሥልጣን  መውረድ ካልቻለ ከችግሮች አዙሪት አለመውጣት ብቻ ሳይሆን ሀ/ስብከቱ የትናንሽ መንግሥታት ቢሮ ከመሆን አይዘልም። ሀገረ ስብከቱን ወደነበረበት ተቋማዊ አደረጃጀቱ መመለስ  ማለት የሥልጣን ጡንቻውን እንደገና አንድ ቦታ ማፈርጠም ማለት ሳይሆን ሥራን ከፋፍሎ ለመሥራት ያለመና የተሻለ ርእይ የያዘ መሆን ስለሚገባው አሁንም ይህ ይፈጸም ዘንድ ከችግሮች በፊት አበክረን እናሳስባለን።
በወቅቱ የሀ/ስብከቱን ክፍፍል በመቃወም ያወጣነውን ጽሁፍ ለማስታወስ ቀንጭበን ከታች አቅርበናል።

 ከዚህ ውስጥ ዋነኛውና አስደናቂው ውሳኔ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ሰነጣጥቆ የማጠናቀቁ ሂደት አንዱ ነበር።
የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ችግር ጠንቅቆ የሚያውቅ የሲኖዶስ አባል የለም። ጳጳሳቱ የተመደቡባቸውን ሀ/ስብከቶች ለሥራ አስኪያጆቻቸው አስረክበው ሁለትና ሦስት ወራት ከአዲስ አበባ ቤቶቻቸው መሽገው ወለተ ማርያምንና ገ/ማርያምን እያሳለሙ እንደሚቀመጡ ይታወቃል። ግድ እየሆነባቸው እንጂ ሐዋርያዊ ተልእኰ ለመፈጸም ዝግጁዎቹ ጥቂቶች ናቸው። ስለዚህ አብዛኛዎቹ ጳጳሳት በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ለመመደብ ያላቸው ፍላጎት ጫን ያለ ነው። ይህንኑ ጽኑ ምኞት ለመተግበር የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ከፓትርያርክ ጳውሎስ ልዩ ሀ/ስብከትነት  በማላቀቅ 4 ቦታ እንዲከፈልና 4 ሊቃነ ጳጳሳት ሊመደቡበት ይታገሉ እንደነበር ያለፉት ጉባዔያቶቻቸው ያስረዱናል። ተፈላጊው ነገር የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ችግሮች ምን እንደሆኑ በማወቅ መፍትሄ ለማምጣት ሳይሆን የአቡነ ጳውሎስን ስልጣን ከሀ/ስብከቱ ላይ በመቀማት 4 ጳጳሳት ተመድበውበት የሞቀ የደመቀውን በማግኘት ከክፍለ ሀገር ሀሩርና አቧራ ለመገላገል ብቻ ነበር። የሚገርመው ነገር ዛሬ አቡነ ጳውሎስ በሌሉበት ሁኔታ ውስጥ ፍላጎታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ መቻላቸው ሳይሆን ለምን? እንዲከፈል እንደተፈለገ አለማወቃቸው ነው። ምክንያቱም ሀ/ስብከቱን እንደዓይናቸው አምሮት ከመሰነጣጠቃቸው በቀር ለምን መሰነጣጠቅ እንዳስፈለገ የተናገሩት አሳማኝና ጥናታዊ መረጃ ያለውን ዝርዝር ነገር ሲነግሩን አለመደመጡ ነው። እንደ ደጀብርሃን ብሎግ እምነት የአዲስ አበባ ሀስብከት መሰንጠቅ የተፈለገው በሁለት ምክንያት እንደሆነ ከፍላጎቶቻቸውና ከዓላማዎቻቸው አንጻር እንረዳለን።
1/ ከሚመጣው ፓትርያርክ ልዩ ሀ/ስብከትነት ነጻ በማውጣት ለሚመደቡ ጳጳሳት ልዩ የደስታ ግዛት ለመፍጠር፤
2/ ለአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የአንድ ሰው ግዛት አድርጎ ከማቆየት ይልቅ ከፋፍሎ ለሌሎችም ቶሎ እንዲዳረስ ለማስቻል ነው ብለን እንገምታለን። ምክንያቱም መሰነጣጠቅ ያስፈለገው ምን ለማምጣት እንደሆነ አሳማኝ ነገር አለመቅረቡ ነው።
በኛ እምነት የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት መሰንጠቅ ትክክለኛ ያልሆነ ውሳኔና የሀ/ስብከቱን ችግር ያልተመለከተ ስሜታዊ ውሳኔ ነው እንላለን። ምክንያቶቻችንም ለሀ/ስብከቱ የተሻለ መንገድ መኖሩን በማመላከት ይሆናል።
1/ የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የሀገሪቱና የአፍሪቃ ዋና ከተማ ከመሆኑም ባሻገር የቤተክርስቲያኒቱ ማእከላዊ ሀ/ስብከት  በመሆኑ ሁኔታዎችን የገመገመና ወቅቱን ያገናዘበ  ልዩ መተዳደሪያ ደንብ ሊኖረው የተገባ ነው።
2/ የሀ/ስብከቱ ጽ/ቤት አወቃቀር የመንግሥትንና ዓለምአቀፍ ተቋማትን ደረጃ ያገናዘበ ዘመናዊ፤ ሙያዊና ችሎታን የተመረኮዘ የአስተዳደር መዋቅር  የያዘ መሆን ይገባው ነበር።
3/ አሁን ያሉትን ስድስት ሥራ ፈት የወረዳ ጽ/ቤቶችን ወደ አራት በማጠቃለል በአውራጃ ጽ/ቤት ደረጃ ሥልጣንና ኃላፊነት ከሀ/ስብከቱ  ከፍሎ በመስጠት እንደአዲስ ቢደራጅ ስልጣን የተሰበሰበበትን የሀ/ስብከቱን  ማእከል ጫናና ድርሻ ከመቀነሱም በላይ ተጠያቂነት ያለው አሠራርን ማስፈን ይቻል ነበር።
4/  የሀ/ስብከቱ አድባራትና ገዳማት የአስተዳደር መዋቅር በሀ/ስብከቱ መተዳደሪያ ደንብ በትክክል የተቀመጠውን የተከተለ መሆን የሚገባው ሲሆን ሙያን፤ ችሎታን፤ ብቃትን፤ ልምድንና መልካም ሥነ ምግባር የተከተለ የአስተዳደር መዋቅር ሊፈጠርበት ይገባዋል።
5/ በየአድባራት ያሉትን ከመጠን በላይ ያለውን የሠራተኞች ቁጥር  ወደሌላ የልማት ዘርፍ በመቀነስ እንደ አዲስ ማደራጀት የግድ መሆን አለበት።ይህ የልማት ዘርፍ ከደመወዝ ጠባቂነት ይልቅ አምራች ዜጋ እንዲኖርና የሚፈልሰውን ቅጥር ፈላጊ ለመከላከል የሚያስችል ነው።
6/ የሀ/ስብከቱ  ጽ/ቤት አድባራቱ በጋራ  ያላቸውን ካፒታል በማሰባሰብ በሚያቋቁሙት የልማት ተቋም የገቢ አቅም እንዲፈጥሩና ከልመና ገንዘብ እንዲላቀቁ ማድረግ ይጠበቅበታል። ለምሳሌ በጋራ ገንዘባቸው፤ ማተሚያ ቤት ወዘተ ማቋቋም ይቻላል።
7/ ቤተክርስቲያኒቱ ብዙ ባለሙያና አዋቂ ምእመናንና ምእመናት እያሏት ከዳር ሆነው ድክመቷን እየተመለከቱ፤ እሷም ልትጠቀምባቸው ሳትችል መቅረቷ ይታወቃል። በሀ/ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የሚደራጅ የምሁራን ልጆቿ የአማካሪ ቦርድ ቢኖረው ሀ/ስብከቱ ተጠቃሚ ይሆናል።
ሌሎች ተጨማሪና አስፈላጊ ነጥቦችን ለመፍትሄው በማስቀመጥ አሁን ያለውን የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ችግር ማቃለል እየተቻለ ሲኖዶስ ሀ/ስብከቱን መሰነጣጠቅ መፈለጉ ትክክል አይደለም። የትኞቹን ችግር በየትኞቹ መንገዶች ለማቃለል ተፈልጎ ነው ሀ/ስብከቱን በብዙ ሊቃነ ጳጳሳት ስር መሰንጠቁ ያስፈለገው? ለሚለው ጥያቄ  አሳማኝ መልስ የለም።
የአዲስ አበባ መስተዳደር እንኳን የሚተዳደረው በአንድ ከንቲባ ሥር ሆኖ ራሳቸውን ችለው በተወሰነ ሥልጣንና ኃላፊነት በተደራጁ ክ/ከተሞች እንጂ በልዩ ልዩ ከንቲባ ተሰነጣጥቆ አይታይም። የኛዎቹ በብዙ የሊቀ ጳጳስ ከንቲባ ሥር ሀ/ስብከቱን ከፋፍለው ሲያበቁ በሀ/ስብከቴ ጣልቃ አትግባ የሚል ድምጽ ለማስማትና አንድ ሠራተኛ  ከአንድ ክፍል ውስጥ ወደ ሌላኛው ክፍል እንዳይዘዋወር የሚያደርግ ስለሆነ ይህንን መፈለጋቸው አስገራሚም አሳዛኝም ነው። ውጤቱም አሳዛኝ ከመሆን አይዘልም።
ለወትሮውስ ቢሆን ርዕይና ግብ ከሌለው ጉባዔ ከዚህ የተሻለ ምን ሊጠበቅ ኖሯል? ሲኖዶሱ ራሱ ተሰነጣጥቆ አዲስ አበባንም በፈቃዱ ሰነጣጥቆ አረፈው። የ10 ቀናት ውጤት ይህ መሆን ነበረበት? ለአንባቢዎች የምናስገነዝበው ጽሁፋችን ለነቀፋ ሳይሆን በተገቢ ሂስ፤ አሳማኝ መልስ የሚሰጥ ካለ ያንን ለማግኘት ሲሆን መሠረቱም በሚታይ ገሃዳዊ እውነታ ላይ ተመስርተን ብቻ መሆኑን እንድታውቁልን ነው።

Tuesday, June 4, 2013

በሰማንያ ወአሀዱ ሽፋን የተፈጸመው የጠላት ሴራ ሲገለጥ ( ክፍል ፪ )


( ክፍል ፪ )
ከዚህ በፊት በክፍል ፩ ለመግለጽ እንደሞከርነው ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ ቅዱሳት መጻሕፍት ትርጉም ውስጥ እጁን በማስገባት የራሱን ዓላማ በእግዚአብሔር ቃል ሽፋን ሲፈጽም መቆየቱን ለማብራራት ሞክረናል። ክርስቲያኖች እውነቱን አውቀው እግዚአብሔርን ወደማምለክና በአንድያ ልጁ በኩል የተደረገውን የማዳን ሥራ በቂ እንዳልሆነና ልዩ ልዩ የድኅነት/ የመዳን/ መንገዶች መኖራቸውን በማሳየት መመለሻ ወደሌለው ጥፋት ለመውሰድ ሌሊትና ቀን የማይደክም ብርቱ ጠላት መሆኑ «የሚውጠውን የሚፈልግ አንበሳ» የተባለው ቃል ያረጋግጥልናል።

ብፁዕ አቡነ ሺኖዳ የቅብጥ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ከጻፏቸው በርካታ መጻሕፍት መካከል አንዱ የሆነውና «diabolic war» /ዲያብሎሳዊ ውጊያ/ በተሰኘ መጽሐፋቸው ውስጥ ዲያብሎስን ጠንካራ የሚያደርገው መልካም ነገር አለ ብሎ ባሰበበት ቦታ ሁሉ ከፍተኛ ውጊያ ቢገጥመው እንኳን ተስፋ ቆርጦ ስለማይሄድ ክፉ ጠላት በማለት ይገልጹታል። ሲሸነፍ አሜን ብሎ እጁን የሚሰጥ ሳይሆን ጊዜ እየጠበቀ እስከመጨረሻው ድረስ ያለመታከትና ያለመሰልቸት መዋጋት መቻሉ የክፋቱን ልክ ያሳያል ይላሉ። በእርግጥ ዲያብሎስ ከክብሩ የወደቀና የተሸነፈ መልአክ ነው። ቢሆንም ያለው ከሙሉ ኃይሉ ጋር ስለሆነ  ውጊያው ቀላል ስላይደለ እምነታችንን እንዳይጥልብን አጽንተን እንጠብቅ ዘንድ ይመክሩናል። 

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6፥12
«መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ»

ስለዚህ ጠላታችን ኃይለኛ ተዋጊ እንጂ የወደቀ ነው ተብሎ የሚናቅ ስላይደለ አብያተ ክርስቲያናትን አጥብቆ መዋጋቱን መዘንጋት ተገቢ አይደለም። ግለሰቦችን ተዋግቶ ከማሸነፍ ይልቅ ግለሰቦች የተሰባሰቡባትን ቤተክርስቲያን የምትመራበትን ቃል መጠምዘዝ መቻል ሁሉንም ከእውነተኛው መንገድ ላይ ማስወጣት መቻል መሆኑ አሳምሮ ስለሚያውቅ  ይህንኑ በትጋት ይፈጽማል።ከዚህም የመዋጊያ ስልቱ መካከል ቅዱሱን የእግዚአብሔር ቃል ባደረባቸው ሰዎች በኩል ማጣመም፤ መሸቃቀጥ፤ ብዙ የመዳን መንገዶች እንዳሉ ማሳየት፤ የኢየሱስ ክርስቶስን ብቸኛና ብቁ መድኃኒትነት በልዩ ልዩ መድኃኒቶች መተካት ዋናው ስራው ነው። ይህንንም በተግባር ሲሰራ ቆይቷል። ለዛሬም ጥቂቱን በማሳየት እንዴት እንደተዋጋን ለማሳየት እንሞክራለን።

1/ የመጽሐፍ ቅዱስን ቁጥር ማዛባት የጠላት ዋነኛ ሥራው ነው..

መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው የጻፉት መሆኑ አያጠያይቅም። ቀደምት አበውም የመጽሐፍ ቅዱስን ቅደም ተከተል፤ ምዕራፍና ቁጥር የተነተኑትም በመንፈስ ቅዱስ መርምረው መሆኑንም እናምናለን። ችግሩ የሚነሳው በዚህ ዘመን ላይ እንደመጽሐፍ ቅዱስ አካል የሚቆጠሩት የቀደምት መጻሕፍት አካል የሆኑት የትኞቹ ናቸው? የሚለው ጥያቄ ነው። ለማሳየነትም በቅብጥ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለ1600 ዓመት ስትመራ ቆይታለች እየተባለ የሚነገርላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ቁጥርና ዝርዝር በፍጹም አይመሳሰልም። ለምን? ሁለቱን አብያተ ክርስቲያናት የመጽሐፍ ቅዱስ ቁጥርና ዝርዝር አንድ ካላደረጋቸው አንድ ነበሩ ሲያሰኝ የቆየው ታዲያ ምን ነበር? እነአትናቴዎስን ከፍ ከፍ የምታደርገው በምን መለኪያ ነው? በዋናው የእግዚአብሔር ቃል ልዩነት ካላቸው በሃይማኖት አይመሳሰሉም ማለት ነው። የቅብጥ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በዕብራውያን እጅ ያሉትን 39 የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት እንደትክክለኛ የእግዚአብሔር እስትንፋስ መጻሕፍት አድርጋ ትቀበላለች። ካርቴጅ  በተደረገው ጉባዔ መጻሕፍት አምላካውያት ላይ ቀኖና ሲደነገግ እነቅዱስ አትናቴዎስ 39ኙን የዕብራውያን መጻሕፍት አጽድቀዋል። ኮፕትም ይህንኑ ተቀብላ እስከዛሬ አለች። እንደዕብራውያን መጻሕፍት የማይቆጠሩና በተጨማሪ ቀኖናተ መጻሕፍት የተያዙ /Deutrocanonical/ መጻሕፍትን ለብቻ መዝግባለች። 
እነዚህም 1/ እዝራ ሱቱኤል (አንድና ሁለትን) እንደአንድ መጽሐፍ 2/ ጦቢት 3/ ዮዲት 4/ ጥበበ ሰሎሞን 5/ ሲራክ 6/ ባሮክ 7/ መቃብያን (አንድና ሁለት) እንደአንድ መጽሐፍ መያዟ ይታወቃል። እነዚህም መጻሕፍት ቢሆኑ ድምራቸው ከዕብራውያን መጻሕፍት አይደሉም።  መጽሐፈ ሔኖክ፤ 3ኛ መቃብያን ፤ 4ኛ መቃብያን የሚባሉትን መጻሕፍት እንደትርፍ መጻሕፍት አድርጋ አትቀበልም።  መቃብያን አንድና ሁለት ራሱ ከኢትዮጵያው መቃቢያን ጋር ምንም የሃሳብና የመንፈስ ግንኙነት የሌለው በመሆኑበሁሉም  በመጽሐፈ መቃብያን በኩል ቅብጥና ኢትዮጵያ ልዩነታቸው የሰማይና የምድር ያህል ይርቃል። ለምን?

ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንደቅዱሳት መጻሕፍት አድርገው ያልቆጠሯቸውን መጻሕፍት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከማን አግኝታ ተቀበለቻቸው? ለመቀበል ያስቻላት መመዘኛ ምንድነው? እስክንድርያ እናቴ፤ ማርቆስ አባቴ ስትል የቆየችባቸው ዘመናት የክርስትና ሕይወትና ዓምድ በሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ አንድነት ከሌላት መነሻው ምንድነው? ኮፕት 66ቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እንደአበው ቅዱሳት መጻሕፍት ድንጋጌ ስትቀበል፤ በትርፍነት እንደሕጻናት የመንፈሳዊ ትምህርት ማጎልመሻ መጻሕፍትነት 7 በተጨማሪ ወይም በዲቃላ መልክ ይዛ ትገኛለች። 

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ግን ዲድስቅልያ፤ አብጥሊስ፤ትዕዛዝ፤ ሥርዐተ ጽዮን፤ ግጽው፤ ቀሌምንጦስ፤ ዮሴፍ ወልደኮርዮን ወዘተ ሳይቀሩ በ4ኛውና በ5ኛው ክ/ዘመን የተጻፉትን ሳይቀር የቅዱሳት መጻሕፍት አካል አድርጋ መቁጠሯ ለምን ይሆን?
ሰማንያ ወአሀዱ ተብለው በተለምዶ ቢጠሩም እነሱም እስከ 85 ይደርሳሉ። አንዳንዴ የግድ የተለመደው 81ን እንዳያልፍ ሲባል ሁለቱን በአንድ እስከመጨፍለቅ ይደረሳል። ቀሌምንጦስ የሐዋርያው ጴጥሮስ ደቀመዝሙር የእጣ ክፍሉ በነበረችው በኮፕት ቤተክርስቲያን ውስጥ መንፈሳዊ አገልግሎቱን ያበረከተ ብዙ መጻሕፍትን የጻፈ ቢሆንም ኮፕት የሱን መጻሕፍት እንደመጽሐፍ ቅዱስ አካል አድርጋ ያልተቀበለችው ሆኖ ሳለ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የኔ ሰማንያ አሀዱ በማለት በግድ የምትቆጥረው ምን ቁጣ ወርዶባት ይሆን? ከዘመነ ሐዋርያት በኋላ የተጻፉ መጻሕፍት ከመማሪያነትና በመንፈሳዊ እውቀት ከማነጽ ባሻገር እንደወንጌል ቃል ሊቆጠሩ ይችላሉ? የኛ ሰማንያ ወአሀዱ ይህንን ሁሉ ግሳንግስ ይዟል። ለምን? በምን መለኪያ? ቅዱሳት መጻሕፍትን በፈለጉበት ጊዜ እያነሱ መጨመር ይቻላል?

በዚህም ተባለ በዚያ አበው ሊቃውንት እስትንፋሰ እግዚአብሔር ያለባቸው ናቸው በማለት በቅደም ተከተል ያስቀመጧቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ብቻ ሳይሆን የማይታወቁ፤ ያልተመረመሩ፤ አበው በቀኖናቸው ያልያዟቸው፤ ብዙ ትርፍ መጻሕፍትን ይዛ መገኘቷ እንደቅርስ ካልሆነ በስተቀር እንደቅዱሳት መጻሕፍት ስብስብ ሊያስቆጥራቸው የሚችል አንዳችም አስረጂ አይቀርብባቸውም።
እስኪ ግብጽ/ቅብጥ/ እንደትርፍ መጻሕፍት የምትቆጥረውንና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ግን እንደዕብራውያን መጻሕፍት እስትንፋሰ እግዚአብሔር ያስጻፈው ነው ብላ የምታምንበትን 1ኛ መቃብያንን ምዕ 1፤1 በንጽጽር እንመልከት።

የቅብጥ ቤተክርስቲያን መቃብያን 1፤1

After Alexander son of Philip, the Macedonian, who came from the land of Kittim, had defeated Darius, king of the Persians and the Medes, he succeeded him as king. (He had previously become king of Greece.)

ተዛማጅ ትርጉም፤ «ከምድረ ኪቲም የመጣው መቄዶንያዊው የፊልጶስ ልጅ ፤ የፋርሱንና የሜዶኑን ንጉሥ ዳርዮስን አሸነፈ።ራሱንም ንጉሥ አድርጎ  ሾመ፤ ቀድሞም የግሪክ ንጉሥ ነበር»   (መቃብያን ቀዳማዊ 1፤1)

ይህ  ታሪክ ስለታላቁ እስክንድር የሚተርክ የታሪክ ክፍል ነው። ታላቁ እስክንድር ደግሞ የኖረበትን የታሪክ ዘመን ስንመረምር በ3ኛው መቶ አጋማሽ ዓመተ ዓለም የነበረ ጦረኛ ተዋጊ መሆኑን መረጃዎች ያሳዩናል። ከዚህ ተነስተን ስለ እስክንድር ታላቁ የሚተርከው ይህ የመቃብያን መጽሐፍ ታላቁ እስክንድር ካለፈ በኋላ እሱን በሚያውቁ ወይም ታሪኩን በሰሙ ሰዎች የተጻፈ ስለመሆኑ የጽሁፉ ይዘት ይጠቁመናል። ለጽሁፉም መነሻ ምክንያት የሆነው ኢየሩሳሌምን ጨምሮ ከፋርሶች እጅ ነጻ በማውጣቱ ምናልባትም የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊዎች የጻፉት ሊሆን እንደሚችል የነገረ መለኮት ታሪክ አዋቂዎች ይገምታሉ።  ግብጻውያንም እንደቅዱሳት መጻሕፍት ያልቆጠሩበት መነሻ ምክንያትም እስክንድር ቅድመ ክርስትና የነበረ ሰው ሲሆን በእምነትም አይሁዳዊ ባለመሆኑ የተነሳ ነው። በማታትያስና አምስት ልጆቹ ያለውን በሜዲተራንያን  አካባቢ በግሪኮች ላይ የተደረገውን የዐመጽ ትርክርት የሚናገር መጽሐፍ ነው። ዛሬም አይሁዳውያን እንደመንፈሳዊ መጽሐፍ ሳይሆን ከታሪክ መጽሐፍነት የበለጠ ስፍራ አልሰጡትም።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መቃብያን በተመሳሳይ(ምዕ 1፤1) ከኮፕቱ ጋር ሲተያይ፤

«ስሙ ጺሩጻይዳን የሚባል ኃጢአትንም የሚወዳት አንድ ሰው ነበር። በፈረሶቹም ብዛት፤ ከሥልጣኑ በታች፤ በጭፍራዎቹም ጽናት ይመካ ነበር» (መቃብያን ቀዳማዊ 1፤1)

የሃሳብ፤ የመልዕክት ግንኙነት ምንም የለውም። ይህ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን መቃብያን ስለማታትያስና አምስት ልጆቹ የዐመጽ ታሪክ ምን አይናገርም። ይልቁንም የሜዶን ንጉሥ ሳይሆን ግሪኮች መካከለኛው ምሥራቅን ሲገዙ የነበሩበትን ዘመን ትቶ ወደኋላ በመሄድ ስለሜዶኖች ይተርካል። እንግዲህ ይህንን ዓይነት የመጻሕፍት ልዩነት መኖሩ መነሻው ምንድነው? ብለን ብንጠይቅ ጠላት እያሰረገ በቅዱሳት መጻሕፍት ሽፋን ያስገባው እንጂ   በሁለት አፍ የሚናገር ቃለ እግዚአብሔር ለክርስቲያኖች የተሰጠ  ሆኖ አይደለም።

2/ መጽሐፈ መቃብያን ያላቸው ተቀባይነት ፣

፩ኛና ፪ኛ መቃብያን በካቶሊክ፤ በምሥራቅ ኦርቶዶክሶችና ኮፕት ኦርቶዶክስ ዘንድ እንደተጨማሪ መጻሕፍት ሲቆጠሩ በአይሁዶችና በፕሮቴስታንቶች ዘንድ እንደ እግዚአብሔር እስትንፋስ ስለማይቆጠር ተቀባይነት አላገኘም።  ፫ኛ መቃብያን በምሥራቅ ኦርቶዶክሶች ዘንድ ብቻ ተቀባይነት ሲያገኝ በካቶሊክ፤ በኮፕት፤ በአይሁዶችና በፕሮቴስታንቶች  ዘንድ እንደ እስትንፋሰ እግዚአብሔር ተደርጎ አይቆጠርም። ፬ኛ መቃብያን ደግሞ ከጆርጂያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ብቻ እንጂ በየትኞቹም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። 

በመቃብያን ስም የሚጠራ ነገር ግን ከላይ ከተዘረዘሩት አብያተ ክርስቲያናት መጽሐፈ መቃብያን ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ሦስት የመቃብያንን መጻሕፍት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስና የኤርትራ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የራሳቸው መቃብያን ይዘው ይገኛሉ። ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት የማይቀበሉት በተለይም ከአይሁድ የኦሪት መጻሕፍት ውስጥ እንደአንዱ የማይቀጠርና ወዳጅ ቤተክርስቲያን የተባለችው የኮፕት ቤተክርስቲያን ጭምር የማትቀበለውን ይህንን የመቃብያን መጻሕፍት መቀበላችን ምክንያቱ ምንድነው?

ለኢትዮጵያውያን ለብቻችን ከሰማይ የወረደ ልዩ መጽሐፍ ስለሆነ ይሆን? በበፊቶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ እንደመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ሳይቆጠር /Apocrypha/  ተብሎ ለብቻው የተቀመጠውን በ2000 ዓ/ም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግን እንደቅዱሳት መጻሕፍት ቆጥራው መዝግባው መገኘቷ አስገራሚ ሆኗል። እቀበለዋለሁ በምትላቸው የኒቂያ፤ የኤፌሶንና የቁስጥንጥንያ ጉባዔያት ውስጥ ከቅዱሳት መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ የሌሉትን በ2000 ዓ/ም እትም ውስጥ ማስገባትዋ የጤንነት ነው? በእርግጥም ጠላት ቤተክርስቲያኒቱን በእውነተኛው የእግዚአብሔር ቃል ውስጥ እንክርዳዱን በደንብ መዝራት መቻሉን ያረጋገጠ ሆኗል።

3/ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መቃብያን ግልጽ ስህተቶች፤ 

መቃብያን ምንጩ ከእግዚአብሔር ሳይሆን ከሰዎች ልብ መንጭቶ የተጻፈ ስለመሆኑ ብዙ ግድፈቶችን ማቅረብ ይቻላል። ለምሳሌ ያህል በ1ኛ መቃብያን 10፤ 1-2 ያለውን እስኪ እንመልከት። እንዲህ ይላል።
«ነገር ግን እንዲህ ካልሆነ የቀደሙት ሰዎች ከአዳም ጀምሮ ከሴትና ከአቤል፤ ከሴምና ከኖኅ ከይስሐቅና ከአብርሃም ከዮሴፍና ከያዕቆብ፤ ከአሮንና ከሙሴ ጀምሮ በአባቶቻቸው መቃብር ይቀበሩ ዘንድ ነው እንጂ በሌላ ቦታ ይቀበሩ ዘንድ ያልወደዱ ለምንድነው? በትንሣዔ ጊዜ በአንድነት ሊነሱ አይደለምን? አጥንታቸውስ ጣዖት ከሚያመልኩ ከክፉዎች ከአረማውያንም አጥንት ጋራ እንዳይቆጠር አይደለምን?» 

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረን አሮን የሞተው በሖር ተራራ ላይ ርስት ምድር ሳይገባ በሞዓባውያን ሀገር ነው። ዘኁል 20፤25-26 ሞዓብ ደግሞ ጣዖት አምላኪያውያን ናቸው እንጂ እስራኤላውያን አልነበሩም። መጽሐፈ መቃብያን ግን የሌለውን ታሪክ በመለፍለፍ አሮን  ከአባቶቻቸው መቃብር ከተቀበሩት አንዱ እንደሆነ ውሸት ይተርክልናል። የአብርሃምና ሚስቱ ሣራ እስከዛሬም  መቃብራቸው ያለው በኬብሮን ነው።  ዘፍ 23፤19-20  ኬብሮን ደግሞ ከደቡባዊ እስራኤል ከተማ አንዷ ናት። በአሮንና በአብርሃም መቃብር መካከል ያለው የቦታ ልዩነት ሩቅ ነው።  ሙሴ እስከዛሬ ድረስ መቃብሩ የት እንደሆነ እንደማይታወቅ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። የሞተው ግን በናባው ተራራ ላይ ነው። መቃብሩ በሞዓብ ሸለቆ ውስጥ ቢሆንም መቃብሩ አልተነገረም። ታዲያ የሙሴን መቃብር የት እንደሆነ አውቆ ነው መቃብያን ከአባቶቻቸው ጋር ለትንሣዔ ቀን እንዲያመች  አንድ ቦታ ተቀበሩ የሚለን? መቃብያን ስማቸውን በመጥራት ሁሉ አንድ ቦታ እንደተቀበሩና ይህም የሆነው መቃብራቸው ከጣዖት አምላኪዎች ጋር እንዳይቀላቀል፤ በትንሣዔ ቀንም አብረው እንዲነሱ ሲሉ ነው የሚለን ትንሣዔን የቦታ ርቀት ይከለክለዋል? 

በጣዖት አምላኪ መካከል መቀበር ሟችን የኃጢአት ተጋሪ እንዲሆን ያደርገዋል? መቃብያን አስገራሚ ትንተናና ልብወለዳዊ ትረካውን በመስጠት አንድ ላይ ያልተቀበሩትን መተረኩ ያስደንቃል። ስለዚህ መቃብያን የተጻፈው በእግዚአብሔር መንፈስ አይደለም። ቦታ አያውቅም፤ ታሪክ አያውቅም፤ የእግዚአብሔርንም የትንሣዔ አሠራር አያውቅም። ይህንን ዓይነት መዛነፍ በማስከተል በቀደምት አበው ተሸፍኖ መቃብያን ከቅዱሱ የእግዚአብሔር ቃል ጋር እንዲቆጠረው ያደረገው ጥንተ ጠላታችን መሆኑን ከመቀበል ውጪ ያፈጠጠውን እውነት መካድ የሚቻል አይደለም።
(ይቀጥላል)