Friday, October 17, 2014

ካሕናቱና ማኅበሩ…እንዴት ተጃመሩ(ተጀማመሩ)???…

 ( በአማን ነጸረ )

 - ልክ የዛሬ አመት በተካሄደው አመታዊው የሰበካ ጠቅላላ ጉባኤ የምዕራብ ሸዋዎቹ አቡነ ሳዊሮስና ስ/አስኪያጆቻቸው “ማኅበሩ በሀገረ ስብከታችን ጣልቃ እየገባ አላሰራን አለ” የሚል ሪፖርት አቀረቡ፡፡ጉባኤው ለሪፖርቱ ያለውን ድጋፍ በእጁ ብቻ ሳይሆን በእግሩ ጭምር መሬት እየደበደበ በድምድምታ ታግዞ ገለጸ፡፡የዚህ ትርጉም ‘መናገር ፈርተን እንጅ በሁላችንም ሀገረ ስብከት ጣልቃ እየገባ ነው’ የሚል ነበር፡፡መፍትሄውም የራሱን የማኅበሩን አካሄድ መፈተሽ ነበር፡፡ማኅበሩ ያደረገው ግን በኅቡዕ ሚዲያዎቹ ጳጳሱንና ስ/አስኪያጆቹን ማብጠልጠል ሆነ፡፡የእነሱ ኃጢኣት የማኅበሩን ጥፋት ይሸፍነው ይመስል ጳጳሱን ‘ሺበሺ’፣መነኩሴውን ‘ዘማዊ’፣ካሕኑን ‘ካንድ በላይ ያገባ’ እያለ በኅቡዕ መዝለፉን ቀጠለ፡፡

2 - በሂሳብ ሙያ 25 አመታት ልምድ አለን ያሉ የጠቅላይ ቤተክሕነቱ ሰዎች ማኅበሩ በቤተክሕነት ስር እስከሆነና ተጠሪነቱም ለኛ እስከሆነ ድረስ በራሳችን ሰዎች ኦዲት ይደረግ፣የራሳችንን ደረሰኝ ይጠቀም የሚል ጥያቄ አቀረቡ፡፡ጉባኤው አሁንም ድጋፉን ገለጸ፡፡የማኅበሩ ተወካዮች ግን ጉባኤውን ረግጠው ወጡና በተለመዱት ኅቡዕ ሚዲያዎቻቸው የቤተክሕነቱን የአቅም ውሱንነትና የደረሰኞቹን ለሂሳብ አያያዝ ምቹ አለመሆን በመግለጽ ጥያቄውንና ጠያቂዎቹን ለማንኳሰስ ተሽቀዳደሙ፡፡ ‘እንዲህ አይነቱን አሰራር እኮ ማስተካከል የሚቻለው ከአስተዳደሩ በመራቅና እሱን በማራከስ ሳይሆን ውስጥ ገብቶ ራሱን ተቋሙንም አግዞ ከችግሩ ለመውጣት ያብሮነት ተጋድሎ በማድረግ ነው’ ብሎ ለመናገር ይቅርና ይሄን ሀሳብ ማሰብም ኑፋቄ ነው ተባለ፡፡

3 - ቀጠሉና ቤ/ክ ትዘምናለች፤አስተዳደሯ ይስተካከላል የሚል መፈክር አነሱ፡፡መፈክሩ ሁላችንንም አማለለን፡፡በገዳማውያን ጸሎት በመታገዝ 3 ሚሊዮን የፈጀ ጥናት አቅርበናል ‘ወንዶች በጭብጨባ ሴቶች በእልልታ’ ተባልን፡፡ከማኅበራዊ ሚዲያ እስከ ዐለማዊ ጋዜጦችና የዲያስፖራው ሚዲያ ተቀባበለው፡፡ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን ጥናቱ ለሚመለከተው አካል ደርሶ ገና አልጸደቀም፤ካሕናቱም አልመከሩበትም፡፡ቀጠለ፡፡ካሕናቱና ምዕመናኑ ስለ ጥናቱ ስልጠና ተብሎ አራት ኪሎ ላይ ከተሙ፡፡ጉዳዩ ግን ስልጠና ሳይሆን ራስን መስበኪያና ጥያቄዎችን ማፈኛ ወደ መሆን አዘነበለ፡፡

4 - ከአጥኚው ክፍል ውስጥ ከ12ቱ 8ቱ የማኅበሩ አባላት ሲሆኑ በቋሚ ትክለኛ አገልጋይ ደረጃ ደግሞ አንድ ጸሐፊ መሀላቸው ጣል ተደርጓል፡፡ካሕናቱ እዚህ ላይ ጥያቄ አነሱ “በጥናቱ ውስጥ እኛን የሚወክል ሰው የታለ?” አሉ፡፡ “ጉዳያችሁ ከጥናቱ ጠቀሜታ ነው ወይስ ከአጥኚው?” እየተባለ ትርፍ ንግግርና አፈና ተጀመረ፡፡ነገርየው “እኛ ስለናንተ ጥቅም ስለምናውቅ ባትሳተፉ ምን ቸገራችሁ--እናውቅላችኋለን” በሚል እንደሚተረጎም ማን አስቦት!!እነሱ እንደሆነ ቀናኢነታቸው ከማንም በላይ ነው!!ጥያቄው ቀጥሏል!! “ያጠናችሁት ጥናት የቤ/ክ የበላይ ሕግ በሆነው ቃለዐዋዲ የታቀፉ ነባር የስራ መደቦች ላይ ሽግሽግ የሚያደርግና የተወሰኑ ኃላፊነቶችን ጨምሮ እንደ አዲስ የሚደለድል ስለሆነ ቃለዐዋዲውን ቀድሞ መመሪያው መምጣቱ ከፈረሱ ጋሪው (በሐጋጊዎች አነጋገር against hierarchy of law) ሆነሳ?” ቢባል!! እረ ወዲያ!!ማን ሰምቶ!! አማሳኝ፣ ዘረኛ፣ ተሐድሶ፣ ካድሬ፣ ወያኔ፣ ሌባ፣ ሙሰኛ፣ምንደኛ፣ተላላኪ፣ደደብ፣ምቀኛ፣ሸረኛ…..የስድብ ሜኑ ተደረደረ!!

5 - አሁን ፅዋው ሞላ!!የአድባራትና ገዳማት አለቆችና ፀሐፊዎች መጋረጃውን ገልጠው ወጡ!!በይፋ ተሰባስበው በቤ/ክሕነቱ አዳራሽ አጀንዳቸውን ቀርጸው ፊርማ ማሰባሰብ ጀመሩ፡፡ገና በጠዋቱ መንገዳቸው ላይ ያለውን ፈተና ተገንዝበውት ነበር፡፡የማኅበሩ ኅቡዕ ሚዲያ የ30 እና 40 አመት አገልግሎታቸውን አፈር አስግጦ ዛሬ እሱ ላይ ጥያቄ ስላነሱ ብቻ ስማቸውን ጭቃ ከመቀባትም አልፎ በራሳቸውና በሚቀርቧቸው ሰዎች ጭምር እንደሚመጣባቸው እንደሚጠብቁ በአደባባይ ተናገሩ፡፡እነ ፋክት መጽሔት፣እነ ‘ቀናኢ ነን’ ብሎጎች የአደባባዩን አቋም “ጥብቅ ምስጢር” እያሉ ቲፎዞ ማንቀሳቀሳቸውን ቀጠሉ፡፡አልገረመንም!!ብሎግን ከግል ኅትመት ሚዲያ አቀናጅቶ በማኅበሩ አካሄድ ጥያቄ ባነሱ ሁሉ መዝመት ከሚሊኒየሙ ማግሥት ጀምሮ እንደ መልካም ትውፊት ስለተያዘ!!

6 - የካሕናቱ በአለቆችና በፀሐፊዎች መያዝ ባሰጋው ማኅበር ቀስቃሽነት ጉዳዩን የምዕመናንን መብት የማስከበር አስመስሎ ከ40 አመት በፊት በሰበካ ጉባኤና በልማት ኮሚቴ እየተመረጠ ከካሕናቱ ጎን ለጎን በቤ/ክ ጉዳይ ውሳኔ ሰጭ የሆነውን ምዕመን ሆድ ለማስባስ ተሞከረ፡፡ “መሬት አንቀጥቅጥ ሰልፍ እንጠራለን፣የአማሳኞችን ገመና እናወጣለን” ተባለ!!ተፎከረ!! ‘እረ ቀስ’ የሚል አልነበረም!! ‘ገመና-ገመና የሚባለው አካሄድ የሚሰራው ሰዎቹ ያጠፉ እለት እለቱን እንዲታረሙና ማስረጃውም ገና ትኩስ እያለ ቢሆን እንጅ ማኅበሩን ሲያነሱ ብቻ ከሆነማ ማኅበሩን ሳያነሱ ስለሚያጠፉት ሰዎች ደንታ የላችሁም፤ስለዚህ እናንተ ቤ/ክ ተጎዳች ምትሉት ማኅበሩ ላይ ጥያቄ ከተነሳ ብቻ ነው’ ያሰኝብናል የሚል ይሉኝታ እንኳ የለም!!ወደ ፊት ብቻ!!በዚህ መሀል ካሕናቱ በጥናቱ ይዘት፣በአጥኚው ስብጥር፣በጥናቱ የስልጠና ሂደት ያላቸውን ቅሬታ በመጠኑ ፈንገጥ ካለና ስሜታዊነት በታከለበት አኳኋን የማኅበረቅዱሳንን ሥም እየጠሩ አስረዱ--ለቅ/ፓትርያርኩ፡፡

7 - ‘የለውጥ አራማጅ ነኝ፣ተነቃናቂ ኃይል አለኝ፣ተወደደም ተጠላም ጥናቱ ሳይሸራረፍ ይተገበራል’ የሚለው ቡድንም በጋዜጣና በብሎግ ተጠራርቶ ፓትርያርኩ ላይ ገብቶ አጀንዳውን አስረዳ፡፡ፓትርያርኩም “ጥናቱ በሊቃውንት ክለሳ ተካሂዶበት ለቤ/ክ በሚበጅ መልኩ ይተገበራል፤ቀደም ሲል የመጡት ካሕናትም ጉዳያቸውን ማስረዳት መብታቸው ቢሆንም ዳኅፀ - ቃል (የምላስ ወለምታ) አድርገዋል” ብለው በአባታዊ መንገድ አስተናገዱ፡፡እዚህ ላይ ጨዋታው ፈረሰ!! ‘ጥናቱ አሁኑኑ’ የሚለው ኃይል የጭቃ ጅራፉን ያጮኸው ጀመር!!ጮኸ-ጮኸ-ጮኸ!!ይሄን ጩኸት ከኋላ ሆኖ ይዘውረው የነበረው ማኅበርም በጩኸቱ ተበረታቶ ነው መሰለኝ መጋረጃውን ገልጦ ወጣና ልሳኔ-የግሌ በሚል ስሜት ሐመር መጽሄቱን መዶሻ፣አቤቱታ አቅራቢዎቹን ካሕናት ደረቅ የማገዶ ግንድ አድርጎ አማሳኝ፣ተሐድሶ…እያለ ፈለጣውን ቀጠለ!!

8 - ካሕናቱ ግን ወይ ፍንክች!!ከነብር ተፋዞ (ተፋጦ) ማን እንቅልፍ ያበዛል!!እስከ በታች ሰራተኛ ወርደው 5ሺህ የሚገመት ፊርማ አሰባሰቡ፣ኮሚቴ አዋቀሩ፣መንግሥት እንዳይገላምጣቸው አሳወቁ (በመንግሥትም ተሰግስግንበታል እየተባለ ማስፈራሪያ ሆኗላ)፣ዐላማቸው ማኅበሩ ቤ/ክ ባሰመረችለት ልክ ከመጓዝ አልፎ ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆም እንጅ ማኅበሩን ለማፍረስ አንዳች ፍላጎት እንደሌላቸው ተናገሩ፣የተላተምነው አድማሳትን የሚያቋርጥ የሚዲያ መረብ ከዘረጋ አካል ነውና በአስተዳደር ላይ ያላችሁ ራሳችሁን ካላስፈላጊ ምግባርና ከተበላሸ አስተዳደር ጠብቁ፣በተቻለ መጠን አባቶችን ሰድቦ ለሰዳቢ ከሚሰጠው የተሐድሶዎች እንቅስቃሴ አጀንዳችንን እንጠብቅ…የሚሉ መርሆዎች ተቀመጡ፡፡

9 - እንቅስቃሴው ከላይኛው የቤተክሕነት አካልም ቀላል የማይባል ድጋፍ አገኘ፡፡በፓ/ኩ ዕለተ - ሲመት የካቲት 24 በተደረጉ ቅኔያት ይሄው ሀሳብ…ወቤቴል አሀቲ ኢትኩን ዝርውተ፣አኃዝ ማኅበራተ፣መዋግደ ብዙኅ ፀጋከ ወአስተናድፍ ሥርዓተ…በሚሉ የሊቃውንት ቅኔያት ተንፀባረቀ፡፡ማኅበሩ ግን ይሄንን ከቅርቡ ያሉ ሊቃውንት ውትወታ ከመስማት ይልቅ ለሚመለከተው መምሪያና ላሉበት ሀገረ ስብከት ሳያሳውቅ የጠረፎቹን እየጠራ “ለማናውቀው ስብሰባ ኃላፊነት አንወስድም” ሲባል….የኛ ቤት እንደምታውቁት…እያለ የአዞ እንባውን መርጨት ጀመረ፡፡ታዲያ ሚዲያው አልሰነፈም!!ጉዳዩን ሲፈልግ ከወያኔ አነሳስ፣ሌላ ጊዜ ደግሞ ከተሐድሶ እንቅስሴ ጋር እያገናኘ ማኅበሩ ራሱን የሚያይበትን ውስጣዊ ዐይን ዐውሮ በትምክሕቱ እንዲጀቦን የውዳሴ ከንቱ ቡልኮ አጎናጸፈው፡፡ “አንድ ለእናቱ” እያሉ የቤተክርስቲያኒቱን የ2ሺህ አመት ታሪክ ለ20 አመቱ ማኅበር አሸክመው አንገዳገዱት፡፡ውስጡን እንዳይመለከት ጋረዱት!!

10 - እናም ይሄው አባላቱ ማኅበሩን የበጎነት እና የክፋት፣የጽድቅና የኩነኔ መለኪያ አድርገው ኮሽ ባለ ቁጥር ፡- ራሳቸውን መድኅን ቅሬታ አቅራቢዎችን ሰቃልያነ - እግዚእ፣ራሳቸውን ድመት ሌላውን አይጥ፣እነሱ ርቱዕ ኦርቶዶክሳዊ ሌላው መናፍቅ፣እነሱ ለነፍስ ያደሩ ሌላው ለሆዱ….እያሉ እያስመሰሉ የልዩነት መስመር ሲያሰምሩ ይውላሉ፡፡የሚበዙት አባላቱም ማኅበራቸውን ከመፈተሸ ይልቅ ዕቡያን ክሶቹን ተቀብው አሜን-አሜን ይላሉ!!ይህ የማኅበሩ ከመዋቅር እና ከማዕከላዊ አስተዳደር የማፈንገጥ ዝንባሌ፣ስሙን ባነሱ የቤ/ክ ልጆች ላይ ሁሉ ከቅ/ሲኖዶስና ከፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት የሚያደርገው “የተሐድሶ እና አማሳኝ” የውንጀላ ዘመቻ ለቀሳጥያን ተሐድሶዎችና የእነሱ ልሳናት ለሆኑ ብሎጎች ምን ያህል መንገዱን ጨርቅ እንዳደረገላቸው አልተረዱም!!እነዚህ በቁም ያሉትን፣እነዛ ደግሞ በቅድስና ያረፉትን ክብር በማጉደፍ ምዕመኑ ላይ የእጓለማውታነት ስሜት ለመፍጠር ይታትራሉ!!ከንቱ መታተር!!ፍኖተ ሐኬት--የክፋት መንገድ!!

Wednesday, October 15, 2014

«እርስዎም በአማካሪዎችዎ የተነሳ ዕድሜዎ እንዳያጥር ያስቡበት!» ያሉት አባ ማቴዎስ ጠንቅ ዋይ ወይስ የሞት መንፈስ?



ዋና ሥራ አስኪያጁ ‹‹ውድቀት እንዳይደረስብዎ አማካሪዎችዎ ሊያዝንልዎ ይገባል፤›› ማለታቸውን የገለጹት የስብሰባው ተሳታፊዎች አያይዘውም ‹‹ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በአማካሪዎቻቸው ክፋት ከዕድሜያቸው ዐሥር ዓመት አሳጥረዋል፤ እርስዎም በአማካሪዎችዎ የተነሣ ዕድሜዎ እንዳያጥር ያስቡበት፤›› ሲሉ መምከራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ( ሐራ)

«እርስዎም በአማካሪዎችዎ የተነሳ ዕድሜዎ እንዳያጥር ያስቡበት!» ያሉት አባ ማቴዎስ ጠንቅ ዋይ ወይስ የሞት መንፈስ ናቸው?

የሁላችንም ዕድሜ ያለው በእግዚአብሔር እጅ ነው። ማንም የማንንም ዕድሜ አያውቅም። ነገር ግን የሰውን ዕድሜ እናውቃለን የሚሉ ጠንቅ ዋዮችና መናፍስት ጠሪዎች ቢኖሩም አታላዮችና አጭበርባሪዎች ናቸው። ታዲያ አባ ማቴዎስ የፓትርያርክ አቡነ ማትያስን እድሜ በዐሥር ዓመት ማሳጠር የሚችሉት በምን ጥበባቸው ነው? ደግሞስ ነፍስ ኄር አቡነ ጳውሎስ ሊቆዩ ከሚችሉበት ዕድሜ በዐሥር ዓመት ያሳጠሩትስ በምን ኃይል ነው? አባ ማቴዎስ ስለሟቹ ፓትርያርክ አሟሟት የሚያውቁትን ምሥጢር በፓትርያርክ ማትያስ ላይ ለመድገም እንደሚችሉ «እርስዎም ዕድሜዎ በዐሥር ዓመት እንዳያጥር ያስቡበት!» ሲሉ ማስጠንቀቃቸው የሚነግረን አንድ ምሥጢር አለ። እግዚአብሔር ማኅበረ ቅዱሳንን የማይወደውን ሁሉ ይገድላል እያሉን ነው ወይም ማኅበረ ቅዱሳንን የማይወደውን ሁሉ እኛ እንገድላለን ማለታቸው ነው። እንደዚያ ካልሆነ ማኅበረ ቅዱሳንን ባለመውደድና በሞት መካከል ምን ግንኙነት አለ?

    አባ ማቴዎስ በግልጽ ቋንቋ የተናገሩት ዐረፍተ ነገር እንደሚያስረዳው ስለፓትርያርክ ጳውሎስ አሟሟት በትክክል እንደሚያውቁ ነው። ይህንኑ ዕውቀት በፓትርያርክ ማትያስ ላይ እንደሚደግሙት ማስጠንቀቂያቸው ያስረዳናል።
«የአቦን ግብር የበላ ይለፈልፋል» እንዲሉ በማኅበሩ ላይ የደረሰው የማኅበረ ካህናቱና የፓትርያርኩ ግልጽ አቋም ያበሳጫቸው ሸዌው እጩ ፓትርያርክ አባ ማቴዎስ በንዴት ሳያውቁት ድብቁን አደባባይ ላይ አዋሉት። «አቡነ ጳውሎስን የገደልናቸው እኛ ነን» ሲሉ ራሳቸው መሠከሩ። እኛም በመጠየቅ ጨምረን እንዲነግሩን የምንፈልገው እንዴት አድረገው እድሜአቸውን ማሳጠር እንደቻሉ ምስጢሩን ከቻሉ በጀመሩበት መንገድ በፈቃዳቸው እንዲነግሩን፤ እምቢ ካሉ ደግሞ በሕግ ፊት እንዲዘከዝኩልን ለሚመለከታቸው ክፍሎች እናሳስባለን። 

በአንድ ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያኒቱ አመራር ላይ «ዕድሜህን በዐሥር ዓመት እናሳጥራለን!» የሚለው ዛቻ «ልብስ አጥበን እንተኩሳለን» እንደሚባለው የሠፈር ማስታወቂያ ተነቦ በቀላሉ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም። በተዘዋዋሪ «እንገድልሃለን» ማለት ነው። የግድያ ዛቻ ደግሞ በምድራዊው ሕግ ወንጀል ነው።  በሰማያዊውም ቃል ዐመጻና ክፋት ነው።

«አስበው ክፉ ነገርን ተናገሩ። ከፍ ከፍ ብለውም በዓመፃ ተናገሩ» መዝ 73፤8 

አስበው የተናገሩት ቃል ከፍ ያለ የግድያ ዐመጻ ነው። አባ ማቴዎስ ቀድመው እንደማይሞቱ ያረጋገጡ ይመስል የአቡነ ማትያስን በፍጥነት በሞት መወገድ በአደባባይ እንደማወጅ ነውረኛና የከፋ አነጋገር ይኖር ይሆን? እግዚአብሔር አምላክነቱ ለአባ ማቴዎስና ለማኅበረ ቅዱሳን ብቻ የሆነ ያህል አቡነ ማትያስን ቶሎ እንደሚገድል መናገር አሳፋሪ ነው። እንግዲህ እነዚህ ናቸው፤ ቤተ ክርስቲያንን የሚመሩት!

በማኅበረ ካህናቱ ስብሰባ ላይ የነበሩ አንድ ካህን ከተናገሩት አንድ ቃል እዚህ ላይ ልዋስ። « እነዚህ እኮ መንግሥትን ከአንድ ክ/ሀገር ወደሌላ ክ/ሀገር ያመጡ ሰዎች ናቸው እኮ፤ በዚያን ዘመን እንዲህ ማድረግ የቻሉ ዛሬ «አቢሲዲ ቆጥረውማ ማን ይችላቸዋል?» ማለታቸው አንድ ነገር ያሳስበናል። ለሥልጣን ሲሉ ሰው እስከመግደል ሊደርሱ መቻላቸውን ይገልጻል። እንደዚያ ካልሆነ አባ ማቴዎስ እስከዕድሜ ማሳጠር እብደት ቀመስ ንግግር ባልደረሱም ነበር። ምንም እንኳን የሰው ልጅ ዕድሜ በእግዚአብሔር እጅ ያለ ስለሆነ ሁሉም ሰው መሞቱ ባይቀርም አሟሟቱ ግን ልዩ ልዩ ነው።

 በጎርፍ፤ በመሬት መንቀጥቀጥ፤ በመኪና አደጋ፤ ገደል በመውደቅ፤ ውሃ ውስጥ በመስመጥ፤ በሕመም፤ በሰው እጅ በመገደል ወዘተ መንገድ ሕይወቱ ሊያልፍ ይችላል። የአቡነ ማትያስ አሟሟት በእነ አባ ማቴዎስ እጅ ይፈጸም ዘንድ ከፈጣሪ የታዘዘ ካልሆነ በስተቀር ካልጠፋ ወቀሳና ሌላ የማሳሰቢያ ንግግር «እንደአቡነ ጳውሎስ ዕድሜዎት በዐሥር ዓመት ያጥራል» ባለሉም ነበር። እግዚአብሔር የነፍሳት ሁሉ ጌታ ስለሆነ  አሟሟታቸውን ልዩ ልዩ አድርጓል።  በእርግጥም የሰውን ነፍስና ሥጋ ይለዩ ዘንድ ምክንያት ከሚሆኑት መካከል ክፉ መናፍስቶች አንዱ ናቸው። አባ ማቴዎስን ከክፉው መንፈስ እንደአንዱ እንቁጠራቸው? ሞትን ያህል ዜና በአደባባይ ያወሩት የክፉው መንፈስ መልዕክት ቢደርሳቸው ይሆናል። እውነታው ግን እግዚአብሔር ለአባ ማቴዎስና ለማኅበራቸው ብቻ የቆመ አምላክ አይደለም። ኃጢአተኞችን ሁሉ በመታገስ ዕለትን በዕድሜአቸው ላይ የሚሰጥ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው።
ነገር ግን አባ ማቴዎስ እንደጻድቅ ራሳቸውን ቆጥረው በሌላው ሰው ላይ ሲፈርዱ ለዚህ ክፉ አሳባቸው የሞት መልአክ ቀድሞ ወደእርሳቸው ቢመጣስ?

«ክፉ ሰው ዓመፃን ብቻ ይሻል ስለዚህ ጨካኝ መልአክ ይላክበታል» መዝ 17፤11 ይላልና መጽሐፉ።

አቡነ ማትያስም ከክፉ ሰዎች እጅ እንዲድኑ አብዝተው መጸለይ የሚገባቸው ይመስለናል። ዳዊት በዝማሬው እንዳለው

 « አቤቱ፥ ከክፉ ሰው አድነኝ፥ በልባቸውም ክፉ ካሰቡ ከዓመፀኞች ሰዎች ጠብቀኝ ቀኑን ሁሉ ለሰልፍ ይከማቻሉ» መዝ 140፤1

የዕድሜ ወሰን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።

«የሰው ዕድሜ የተወሰነ ነው፥ የወሩም ቍጥር በአንተ ዘንድ ነው፥ እርሱም ሊተላለፈው የማይችለውን ዳርቻ አደረግህለት» ኢዮ 14፤5
አባ ማቴዎስ ማኅበረ ቅዱሳንን የሚነካ ሁሉ ይሞታል እያሉ ይናገራሉ።  ታዲያ አባ ማቴዎስ ጠንቅ ዋይ ናቸው ወይስ የሞት መንፈስ???? የምታውቁ ንገሩን!!

Saturday, October 11, 2014

ፓትርያርኩም፤ ካህናቱም ስለማኅበረ ቅዱሳን በአንድ ድምጽ ተናገሩ!

ቤተ ክርስቲያን ግልጽ የሆነ መዋቅር ያላት ቢሆንም በቤተ ክርስቲያን ስም የሚደራጁ ማኅበራት፣ ከመዋቅራዊ ቁጥጥር ውጭ በመንቀሳቀስ ሀብትና ንብረት ያከማቹና እያከማቹ በመሆናቸው፣ ሕግና ሥርዓት የማይቆጣጠራቸው ከሆነ አሸባሪ የመሆን ዕድላቸው የሰፋ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አስታወቁ፡፡

 

Wednesday, October 8, 2014

«የማዕተብ ጉዳይ ሰሞነኛ ወሬ»


 
ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ «የኦርቶዶክሱን ክር እናስበጥሳለን» ብለዋል በማለት ማስጮሁን የጀመረው አሉላ ጥላሁን የሚባለውና የማኅበረ ቅዱሳኑ አባል የሚነዳው «ሐራ ተዋሕዶ» መካነ ጦማር ነው።  ድርጅት እንጂ እምነት የሌለው ሁሉ ያንን ተቀብሎ አስተጋባ። በእርግጥ ዶ/ር ሽፈራው ብለውታል? ወይስ አላሉትም? የሚለው ጉዳይ ማረጋገጫ የሚያስፈልገው  ቢሆንም «ራስ ሲመለጥና አፍ ሲያመልጥ አይታወቅም» እንዲሉ ዶ/ሩ ብለው ሊሆን ይችላል ብለን ብንገምት እንኳን ይሄንን ያህል ማስጮህና ማጦዝ ያስፈለገው ለምንድነው? ብለን መጠየቅ ተገቢ ይመስለናል።

1/ ምክንያታዊነቱ፤

    አዲስ ይወጣል በተባለው የሴኩላሪዝም ደንብ በመንግሥት የሥራ ቦታዎች ውስጥ ሃይማኖታዊ የሆኑ ምልክቶች ማለትም ስዕል ማድረግ፤ በጠረጴዛም ይሁን በግድግዳ መስቀል ማንጠልጠል፤ የኮምፒውተር ስክሪን ሴቨር ማድረግ፤ መንፈሳዊ ጥቅሶችን፤ ሂጃብ፤ ኒቃብ፤ ቡርቃና ሌላ ተመሳሳይ ሃይማኖታዊ ምልክቶች እንዳይኖሩ የመከልከል ደንብ እየወጣ መሆኑ ሲነገር ቆይቷል።

  እነዚህ ሃይማኖታዊ ምልክቶችን እንደፈለጉ መጠቀም ከዚህ ቀደም ባለፉ ሥርዓታት ዘመን ያልነበሩና አዲስ የፈጠራ ልምዶች እርግጥ ነው። ዲሞክራሲ ያሰፈናቸው ወይም ዘመን የፈጠራቸው ናቸው ወይ? ብለን አንከራከርም።  ነገር ግን ሁሉም ሃይማኖት ከማን አንሼ ሰበብ አጋጣሚውን ተጠቅሞ የሚያደርግ ከሆነ ወይም «እኔን ደስ የማይለኝ ነገር በሥራ ቦታዬ ላይ ተቀምጧል፤ ስለዚህ እንዲወገድ ይደረግልኝ» በማለት ቢቃወም ሰላማዊ የሥራ ሁኔታውን ወደሃይማኖታዊ ንትርክና ጭቅጭቅ ሊቀይር መቻሉ ሳይታለም የተፈታ ነው። ከዚህ በፊትም ይህ ክሰተት ተፈጽሞ «መብቴ ነው!»  «መብትህ አይደለም!»  ወደሚል አተካራ ማስገባቱን ያጋጣመቸው ሰዎች ሲናገሩ ተደምጧል። 

  ለመሆኑ ደመወዝ ሊከፈለው ውል ፈጽሞ በገባበት የሥራ ቦታ ሃይማኖታዊ ምልክቶችን ማስቀመጥ ለምን አስፈለገ? ነገሩን ስንመለከተው ብዙ ጊዜ ሃይማኖታዊ ምልክቶችን ባልተፈቀደ ቦታም ይሁን ተገቢ ባልሆነ ሥፍራ ለማሳየት የሚፈልጉ ሰዎች «እኔ እበልጣለሁ» ወይም «ሃይማኖቴን በጣም እወዳለሁ» በሚል ስሜት ሌላውን ለማሳነስና እነሱ በእምነታቸው የተሻሉ መሆናቸውን ለማሳየት የሚፈልጉ ሰዎች ይመስሉናል።  የዚህ ተቃራኒ ደግሞ «እኔም አላንስም» በማለት ሌላውን ለመቃወም የራሱን ምልክት በተደራቢነት ለመጠቀም የመፈለጉ አዝማሚያ ወይም «ይነሳልኝ» ሲል ክስ የማቅረቡ ሁኔታ ያለውን የእኔነት ውጥረት ለማርገብና አደብ ለማስያዝ መንግሥት መፈለጉ ከተገቢነቱ አኳያ አያጠያይቅም። በየቦታው እየሄዱ በስመ ስብከት ሰበብ «ኢየሱስ ጌታ ነው» እያሉ የግል ነጻነትን ሳያስፈቅዱ እንሰብካለን ሲሉ ከግለሰብ ጋር የሚጋጩትን ጨምሮ በሃይማኖት ሽፋን የሌላውን መብትና ነጻነት መጋፋት ተገቢ አለመሆኑም ትክክል ነው።

  «እኔ የተሻልኩ ነኝ» በሚል ራስን የማግዘፍና በፈጣሪ ፊት ያለውን ተመራጭነት ለማሳየት ካልሆነ በስተቀር ምልክትን መደርደር፤ አብዝቶ መናገር ወይም ራስን ለማሳየት መሞከርና የየትኛው ሃይማኖት ተከታይ እንደሆንክ ማስተዋወቅ በእግዚአብሔር ፊት የበለጠ ተወዳጅ መሆንን ሊያሳይ አይችልም። ስለዚህ የትኞቹም ምልክቶች የፊት ማሳያ እንጂ የልባችን ተግባር መግለጫዎች ስላይደሉ አስፈላጊነታቸው ምክንያታዊ አይደሉም። የክርስትና ወይም የእስልምና ምልክት አድርጎ የሚሰርቅ ወይም የሚያመነዝር ትውልድ ምልክት ስላደረገ እንደ እውነተኛ ሰው ሊቆጠር አይችልም። 

«ራሳችሁን በሰው ፊት የምታጸድቁ እናንተ ናችሁ፥ ነገር ግን እግዚአብሔር ልባችሁን ያውቃል፤ በሰው ዘንድ የከበረ በእግዚአብሔር ፊት ርኵሰት ነውና» ሉቃ 16፤15

የሃይማኖታዊ ምልክት ፉክክር የጥፋት መጀመሪያ ነው። አንድ ሰሞን «አንድ እምነት፤ አንዲት ጥምቀት፤ አንድ ጌታ» የሚለውን ጥቅስ በልብስ ላይ አትመው የለበሱ ሰዎችን ለመገዳደር በሚመስል መልኩ «ኢየሱስ፤ መሐመድና ሙሴ የአላህ ነብያት» የሚል ጥቅስ ለብሰው የሚዞሩ ወጣቶችን ማየቴን አልረሳውም። ሃይማኖቱን በተፈቀደለት ቦታና በሥፍራ እንደመጠቀም ከሌላው የተሻለ እውነተኛነት እንዳለው ለማሳወቅ በሚደረግ ሩጫ ጥፋት ለማስከተል መሞከር የነበረውን ሰላም ከማደፍረስ በስተቀር በዚህ አድራጎት የሚታነጽ ማንም የለም።

«እንዲሁ ደግሞ እናንተ መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ የምትፈልጉ ከሆናችሁ ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ እንዲበዛላችሁ ፈልጉ» 1ኛ ቆሮ 14፤12

2/ የክር እናስበጥሳለን ፉከራና የተቃውሞ ዘመቻ፤

ከላይ በመግቢያችን ላይ እንደጠቆምነው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ስልጠና ላይ «ሂጃብ እንዳስወለቅን ክርም እናስበጥሳለን» ብለዋል የተባለው ጉዳይ እውነት ነው ወይ?   
«ሃይማኖታዊ ምልክቶችን ከመንግሥት የሥራ ቦታዎች ውስጥ እናስቆማለን፤ ሴኩላር የሆነ የሥራ ቦታ እንፈጥራለን» በሚለው እሳቤ ዙሪያ ከአንገት ላይ ክርም እናስበጥሳለን» የሚለውን ፉከራ በምን መስፈርት እንደተመለከቱት ግልጽ አይደለም። እንደእውነቱ ከሆነ ክር አንገት ላይ ማሰር ሌላውን አማኝ አያውክም። ለጌጥ ብሎ ሀብል ከሚያስር ሰው የተለየ ነገር የለውም። መንግሥት እስከዚህ ድረስ የወረደ ተግባር ይፈጽማል ተብሎ አይታሰብም። ተብሎ ከሆነ መስተካከል ያለበት ጉዳይ ነው እንላለን።
 ዶ/ር ሽፈራው ብለዋል ከተባለ በኋላ የገቡበትን አጣብቂኝ ለመከላከል እንደሆነ ለጊዜው ባይገባንም የጉዳዩን ጡዘት በማርገብ ደረጃ  በመንግሥታዊው ሚዲያ «ፋና ብሮድ ካስቲንግ» ቀርበው አላልኩም በማለት አስተባብለዋል። «ቤን» የተባለው አፍቃሬ መንግሥት ድረ ገጽ አዘጋጅም ጥያቄ አቅርቦላቸው አለመናገራቸውን ገልጸዋል። «እንደዚህ አላልንም» ካሉት በላይ የምንጠብቀው ምላሽ አይኖርም።
 ነገር ግን በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ሃይማኖታዊ የሆኑ ምልክቶች ሁሉ እንዳይኖሩ እናደርጋለን ተብሎ ከተዘጋጀው ደንብ ውስጥ ከተዘረዙት ሁሉ በአራጋቢዎቹ ዘንድ የዚህ የክር ጉዳይ ብቻዋን ለምን ተነጥላ ወጣች? ነው ጥያቄያችን። ይህንን ጉዳይ አስቀድሞ ያስጮኸው የማኅበረ ቅዱሳኑ «ሐራ ተዋሕዶ» መካነ ጦማር ነው። ሐራ ደግሞ ጅራፏን የምታስጮኸው በማኅበረ ቅዱሳኑ አሉላ ጥላሁን በኩል ነው።

 ብዙ ጊዜ በአፍቃሬ ማኅበሩ ብሎጎች ስማቸው በክፉ የሚወሳው ዓባይ ፀሐዬ፤ ስብሐት ነጋና ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም ናቸው።  እነዚህን የፖለቲካ ሹማምንት ማኅበሩና ደጋፊዎቹ የሚቃወሟቸው ማኅበሩ የፖለቲካ ድርጅት ስለሆነ ሳይሆን የማኅበሩን አካሄድ በግልጽ ስለሚቃወሙ ብቻ ነው።  እዚህ ላይ በአንድ ወቅት አቶ ስብሐት ነጋ «ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያን ሸክም» ማለታቸው ሳይዘነጋ ነው። 
በሌላ በኩል ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ማኅበር መሆኑም መታለፍ የለበትም። ማኅበሩ  በፓትርያርኩ ላይ ጫና በማሳደር በወዳጆቹ ሊቃነ ጳጳሳት በኩል ማስፈጸም ያቃተውን ቤተ ክርስቲያንን የመረከብ ዓላማ ለጊዜውም ቢሆን የተገታው በሃይማኖት ሽፋን ሀገሪቱን ወደቀውስ መውሰድ ከሚፈልጉ ተቋማት አንዱ ማኅበረ ቅዱሳን ነው ስለተባለና ስሙ ብዙ ጊዜ ብዙ ጊዜ መነሳቱም አንዱ ምክንያት ነው። በዚህ በኩል ዶ/ር ሽፈራው ብዙ ተጉዘዋል። 

  ማኅበሩ ከአባ እስጢፋኖስ ጀርባ ሆኖ ያረቀቀውና የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን የመረከብ ሕግ  ውድቅ ከሆነበት በኋላ የተወረወረበትን ቅዝምዝም ለማሳለፍ ባለፉት ወራቶች አንገቱን ዝቅ አድርጎ ጠብቋል። መጪው ወር የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ይካሄዳል።  በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ውስጥ ያጣውንና ለአባ እስጢፋኖስ መነሳት ምክንያት የሆነው የሕግ ማርቀቅን ጉዳይ ተከትሎ ማኅበሩን አደብ ለማስያዝ በፓትርያርኩ በኩል የቀረቡ ነጥቦች ነበሩ። 

ይህንን ተከትሎ በማኅበሩ ላይ ይጸና ዘንድ ከሚታሰበው ደንብ በፊት ጥቂት ነገር መጫር ሳያስፈልግ አልቀረም። በማኅበሩ ላይ በሴኩላሪዝም ደንብ ስዕልና ጥቅስ በመሥሪያ ቤቶች እንዳይገኙ ከሚከለክለው ጉዳይ ውስጥ ከኦርቶዶክሳውያን አንገት ላይ የሚታሰረውን ክር ነጥሎ በማውጣት ማስጮህ የፈለገው በአማኙ ስስ ስሜት ተጠግቶ ብዙ ተቃዋሚ በማስነሳት አቅጣጫ የማስቀየር ስልት መሆኑ ነው። በዚህም የማኅበሩ አመራር የሆነው አሉላ በተወሰነ መልኩ ተሳክቶለታል። በዶ/ሩ ላይ ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ድረ ገጾችና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ሳይቀሩ ተቀባብለው ዘምተውባቸዋል። በዚህም ጫና ይመስላል፤ ዶ/ሩ ሳይወዱ ምላሽ ወደመስጠት የተገደዱት። ብለውም ከሆነ «ካፈርኩ አይመልሰኝ» መሆኑ ነው። ያላሉም ከሆነ አጋጣሚውን ጠብቆ ዱላውን ያሳረፋባቸው ማኅበር ምላሽ በመስጠት የማስገደድ አቅሙን እንዲያዩ አድርጓቸዋል። ወደፊት በማኅበሩ ላይ ተጽዕኖ የማሳደር እስትንፋሳቸውን የመከልከል ዘዴ መሆኑ ነው።  በእርግጥ እንዲያ ከሆነ አያዋጣም።

የሚገርመው ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ «ኦርቶዶክሶች ክር የማይበጥሱ ከሆነ እኛም እስላሞቹ ሂጃብ አናወልቅም፤ ቆባችንንም አንጥልም» የሚል ዘመቻ መጀመሩ ነው። ነገሩ አብረን እንጥፋ ነው። «ከኔ ኪስ መታወቂያ ከጠፋ፤ ያንተም መታወቂያ መጥፋት አለበት» ማለት ቅናት እንጂ ጤናማ ክርክር አይደለም። ቡርቃና ኒቃብ ከክር ጋር የሚነጻጸሩት በምን ስሌት እንደሆነ አይገባንም። ትክክልም አይመስለንም። ባለክሮች ስለክር ማሰር ሲጮሁ ባለኒቃቦች ባለክሮችን ተጠግተው ጩኸት አስነሱ። ስለክርም፤ ስለቆብም፤ ስለኒቃብም ማንሳት የማይፈልግ ነጻው ሰው በመንግሥት መሥሪያ ቤት ነጻ ሆኖ እንዴት ይስራ? መልሱ አጭር ነው። ሃይማኖተኞች ሃይማኖታችሁን በተፈቀደላችሁ ቦታ ብቻ ፈጽሙ ነው። ሴኩላሪዝም ማለት ይህ ነው። መንግሥታዊ ሃይማኖት የለም፤ ሃይማኖታዊ መንግሥትም የለም።

 ነገር ግን ባልተጋነነ መልኩ ሥርዓት ማስያዝ የመንግሥት ድርሻ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሃይማኖታዊ ነገሮችን በጥንቃቄ በመያዝና ከባለጉዳዮቹ ጋር በመነጋገር ማስተካከል እንደሚቻል ጽኑ እምነት አለን። ለምሳሌ ፈረንሳይ ኒቃብና ቡርቃን በሕግ አግዳለች። «ኒቃብ» ዓይን ብቻ የሚታይበት ሲሆን «ቡርቃ» ደግሞ ሙሉ በሙሉ የተሸፋፈነች ሴት አለባበስ ነው። ሳርኮዚ «ለእነዚህ ሰዎች መታወቂያ መስጠት ምን ይጠቅማል?» ሲሉ ጠይቀዋል።
መታወቂያ ማን መሆኑን መለያ ነውና አባባላቸው እውነት ነው። ስለዚህ ክርን ከቡርቃ ጋር ለማስተያየት የምትሞክሩ ጥቂት ተረጋጉ። ከጸጥታ ስጋት አንጻርም ቢያስፈራ አያስገርምም። በ2007 ዓ/ም ያሲን ዑመር የተባለ እንግሊዛዊ አሸባሪ ፈንጂ ታጥቆ እንደሴት ቡርቃ ለብሶ እንደነበር የቢርምንግሃም ፖሊስ ሲያከሽፍበት አይተናል።

  በሌላ በኩል ደግሞ ክር ማሰር የተጀመረው መቼ ነው? ብለን ወደዝርዝር አንገባም። ታሪኩ ረጅም ነው። ነገር ግን «ማዕተብ» ማለት ምልክት ማለት እንደሆነ እንናገራለን። ከክርስቲያንም ኦርቶዶክስ የመሆን ምልክት!
 ክር ማሰር ምልክት እንጂ ሌላ ምንም አይደለም። በአዲስ ኪዳን ስለክር ማሰር የተነገረን ነገር የለም። ማኅበሩ እንደቀድሞ ዋሾዎች የሌለውን ጥቅስ እያቀረበ የወንጌል አስተምህሮ እንደሆነ አድርጎ ለማሳመን ቢሞክርም ከውሸትነቱ ፈቀቅ ብሎ እውነት ሊሆን አይችልም። ክርስትና እምነት እንጂ ምልክት አይደለም። በክርስቶስ አምላክነትና አዳኝነት በማመን የሚኖሩበት ሕይወት ነው። የሚገርመው ደግሞ ሚሊዮኖች ክርና መስቀል አንገታቸው ላይ እያለ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት ይዘርፋሉ፤ ያመነዝራሉ፤ ይሰክራሉ፤ ይሰርቃሉ፤ ይዋሻሉ። የአንገት ላይ ምልክት እንጂ የልብ ላይ ክርስትና የላቸውምና ከዚህ ድርጊታቸው ክር ማሰራቸው በጭራሽ ሊያድናቸው አይችልም።
 እንዲያውም ሥነ ምግባር የሌላቸውን ብዙ ጫት በሊታዎች፤ ሴትኛ አዳሪዎች፤ አመንዝራዎች፤ ሰካራሞች፤ ተሳዳቢዎች፤ ዘፋኞች ሰዎች ልብ ብላችሁ ብታዩ አንገታቸው ላይ ክር ወይም መስቀል ታገኛላችሁ። አንገታቸውን ላይ ምንም ምልክት የሌላቸው ሰዎች በተመሳሳይ ጥፋት ብናገኛቸው ያላዳናቸው አለማሰራቸው ነው ብንል ምልክቱን አስረው ያጠፉትንስ ለምን አልታደጋቸውም? ብለን መጠየቁ ተገቢ ነው።


  ስለዚህ ከክር ማሰር ጀርባ የራሳቸውን ዓላማ ለማራገብ የሚፈልጉ ቡድኖች ክር ስላሰራችሁ ጻድቅ አትሆኑም፤ ስላላሰራችሁም አትኮነኑም እንላቸዋለን። ክርስትና በክርስቶስ በማመንና የሥጋ ሥራዎችን በመተው የሚጓዙበት ሕይወት እንጂ ክር በማሰር ክርስቲያን መሆንህን ለሰዎች የምታሳይበት የጎዳና ላይ ማስታወቂያ አይደለም። ባለክሮችም እንደባለቡርቃዎቹ ተረጋጉ።
ጥል፤ ክርክር፤ አድመኝነት፤ በወንጌል ቃል ያልሆነ የቃላት ስንጠቃ፤ እውነትን የተቀሙ ሰዎች ተግባር ነው። አንዲቱ ቤተ ክርስቲያን የተከፋፈለችውም በእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ስለተሞላች ነው። የሐራ ተዋሕዶው አሉላ ያልኖረበትን ክርስትና በክር ስር ቢፈልገው አያገኘውም። እንዲያውም ጥፋት በደጁ ታደባለች።
 ክርስትና ስለስዕል ስለመስቀል፤ አንገት ላይ ክር ስለማሰር አይደለም። ክርስቶስን ስለመምሰል እንጂ።
 
«እነዚህን አስተምርና ምከር። ማንም ልዩ ትምህርት የሚያስተምር ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ጤናማ ቃልና እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚስማማ ትምህርት የማይጠጋ ቢሆን፥ በትዕቢት ተነፍቶአል አንዳችም አያውቅም፥ ነገር ግን ምርመራን በቃልም መዋጋትን እንደ በሽተኛ ይናፍቃል፤ ከእነዚህም ቅንዓትና ክርክር ስድብም ክፉ አሳብም እርስ በርስ መናደድም ይወጣሉ፥ አእምሮአቸውም በጠፋባቸው እውነትንም በተቀሙ፥ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እንደነዚህ ካሉት ራቅ» 1ኛ ጢሞ 6፤3-5

Wednesday, October 1, 2014

በምድራችን ላይ በክፉ መንፈስ ተነድተው ሕዝብን ያሳሳቱ ሀሰተኛ ክርስቶሶችና ነብያት!



 ( ክፍል 3 ) 

ጂም ጆንስ (1931-1978)
በአሜሪካዋ ኢንዲያና ስቴት ህዳር 18, 1931 ተወለደ። እድሜው ለአቅመ ህውከት ሲደርስ በኢንዲያናፖሊስ ከተማ የኮሙኒስት ፓርቲ አባል በመሆን በህውከት ስራ ላይ መሰማራትን «ሀ» ብሎ ጀመረ። የኮሙኒስት ርእዮት አራማጅ የሆነው ጆንስ በሜቶዲስት፤ በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ውስጥ ብቅ ጥልቅ እያለ ከቆየ በኋላ ዓለም በኒውክለር ትጠፋለች ስለዚህ ሐዋርያዊ ሶሻሊዝም በዓለም ላይ መምጣት አስፈላጊነት ይሰብክ ነበር። ጆንስታውን ወደተባለች የጉያና ከተማ በማቅናት «የህዝቦች ቤተ መቅደስ» የተሰኘ ቤተክርስቲያን ከመሠረተና ከተደላደለ በኋላ የእርሻ ተቋም ከፈተ።  በዚህ የእርሻ ተቋም ውስጥ ሶሻሊስታዊ እኩልነት የሰፈነበት ማኅበረሰብ እመሰርታለሁ በማለት የራሱን «የቀይጦር ሠራዊት» አደራጀ። ይህ የቀይ ጦር ሠራዊት ዋና ዓላማው የእርሻውን ሜካናይዜሽንና የቤተ ክርስቲያኑን ህልውና የመጠበቅ ዓላማ ይዞ የተነሳ ቢመስልም በተግባር ግን የጂም ጆንስን አንባገነንነት መንከባከብ ነበር። ወደተቋሙ የገባ ማንም አባል መውጣት አይችልም በማለት ማገድ ጀመረ። በዚህም ሳቢያ በዚያ ማኅበረሰብ ውስጥ የፈለገውን ማድረግ የሚችል አንባ ገነን መሆን ቻለ። ከዚህ ተቋም ሸሽተውና አምልጠው ወደአሜሪካ የገቡ ሰዎች ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተርና ለምክርቤቱ አቤቱታቸውን ማቅረብ ቻሉ። በሰብአዊ መብት ጥሰት የተከሰሰው  የጆንስን ጉዳይ የሚያጣሩ በኮንገረስ ማን ሊዮ ሪያን የሚመራ ብዙ የሚዲያ ሰዎችን የያዘ ቡድን ወደጉያና አመራ። ቡድኑ ከቦታው እንደደረሰ ከጆንስ ቀይጦር አባላት የጠበቀው የሞቀ ሰላምታ ሳይሆን የደመቀ የጥይት ተኩስ ነበር። ኮንግረስ ማን ሪያንና ሌሎች ብዙዎቹ በተኩሱ ተገደሉ።  ከፊሎቹም ቆሰሉ። ህዳር 18, 1978 ዓ/ም ጥዋት ላይ ይህ ግድያ ከተፈጸመ በኋላ ጆንስ ወደተከታዮቹ በመመለስ ከሚመጣባችሁ ቁጣ ለመዳን ራሳችሁን አጥፉ፤ ልጆቻችሁንም ጭምር ለመፍጀት ለሚመጡ ጠላቶች አሳልፋችሁ አትስጡ፤ ስለዚህ አብራችሁ ሙቱ በማለት ትእዛዝ ሰጠ።
ሳይናድ መርዝ እየጠጡና እያጠጡ 300 ህጻናት ያሉበት 900 ሰዎች በጥቂት ሰዓት ውስጥ አለቁ።
እኔ ቡድሃን፤ ሌኒንን፤ኢየሱስን እና ሌሎችን ሆኜ ተገልጫለሁ እያለ ያታልል የነበረው ጂም ጆንስ በአውቶማቲክ ጥይት ግንባሩን ብትንትንን አድርጎ ራሱን በራሱ ገደለ።




ማርሻል አፕልዋይት  (1931-1997)
ስፐር ፤ቴክሳስ ተወለደ። እድሜው ለአቅመ ማሳሳት ከመድረሱ በፊት የአሜሪካ ወታደር በመሆን አገልግሏል። በሂውስተንና ኮሎራዶ ትምህርቱን የተከታተለው አፕል ዋይት በአላባማ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሲሰራ በግብረ ሰዶም ተጠርጥሮ ከስራው ተባሯል። ይህንን ተግባሩን የመሰከረበት ደግሞ በስብከቱ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን አስፈላጊነት መናገሩ ነበር። አፕል ዋይት የሙዚቃ ባለሙያ ስለነበር በዚህ ሙያ ያገኘውን ችሎታ ተጠቅሞ «Heaven’s Gate» /የመንግሥተ ሰማይ በር/ የተሰኘ ሃይማኖታዊ ድርጅት መሠረተ።  አፕልዋይት በዩፎዎች መኖር የሚያምንና በነሱ ላይ ጥገኛ የሆነ ስብከት ያስተምር ነበር።
 በ1974  ዓ/ም የተከራያትን መኪና ባለመመለስ ወንጀል ተከሶ ስድስት ወር ተፈርዶበት ከርቸሌ ወረደ። ከዚያም እንደወጣ ጣዖታዊ ስብከቱን ቀጥሏል። መስከረም 25, 1995 ዓ/ም «እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ነኝ» በማለት ለተከታዮቹ አሳወቀ።
በመጋቢት 29/ 1997 ዓ/ም ዩፎዎች መጥተው ወደገነት ስለሚወስዱን ራሳችንን እናጥፋ ብለው በጅምላ ራሳቸውን ገደሉ። ከተከታዮቹ መካከል ማርሻል አፕል ዋይትን ጨምሮ 30 አባላቱ ሞተው ተገኙ። ነገር ግን ሁኔታው እንደተሰማ ከቦታው የተገኘ አንድም ዩፎ አልነበረም። ይልቁንም ፖሊስ ከቦታው ተገኝቶ እነአፕልዋይት ራሳቸውን በራሳቸው ማጥፋታቸውን አረጋግጦ የህዝብ መቃብር ውስጥ እንዲወርዱ አድርጓል።




ያህዌህ ቤን ያህዌህ (1935-2007) 

 ጥንተ ስሙ ኸሎን ሜሼል ጁንየር ይባል ነበር። ይህ ጥቁር አሜሪካዊ እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ለማለት ፈልጎ ስሙን  በ1979 ዓ/ም «ያህዌህ ቤን ያህዌህ» በማለት ቀየረ። ብዙዎቹም ተከታዮቹ ከክርስትናውና ከአይሁድነት ያፈነገጡ ሰዎች ነበሩ። በተለይም ጥቁር አሜሪካውያን ብዙ ቁጥር ያላቸው ሲሆን ትክክለኛው እስራኤላውያን እኛ ነን፤ ይሉ የነበረ ሲሆን በአሜሪካና በዓለም ላይ በ1300 ከተሞች ውስጥ አባላቱን ማደራጀት ችሏል። እግዚአብሔር ጥቁር ነው። እስራኤልውያንም ጥቁሮች ነበሩ። ነጮቹ ታሪካችንን ቀምተው ነው። ሰይጣን ማለት ነጮች ናቸው ይል ነበር። በዚህም ምክንያት ዓርብ ህዳር 13 ቀን አንገታቸው የተቀላ የነጮች ሬሳ በአቅራቢያው ዳዋ ውስጥ ተጥሎ በመገኘቱ ጥቁሩ መሲህ ቤንያህዌህ በ1992 ዓ/ም ሰው በመግደል ወንጀል ተጠርጥሮ ተያዘ። በፍርድ ቤትም በምስክሮች ስለተረጋገጠበት የ18 ዓመታት እስር ተበይኖበት ከርቸሌ ወረደ።  
በእስራቱም ነብይ በሀገሩ አይከበርም ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው ሲሉ ተከታዮቹ ለፈፉ። ከ8 ዓመት እስራቱም በኋላ በ2001 ዓ/ም በምህረት ተለቀቀ። በ2007 ዓ/ም በፕሮስቴት ካንሰር ሞተ። ከሱ ሞት በኋላ ተከታዮቹ በሥጋ የተገለጠው እግዚአብሔር ማለታቸውን አልተዉም። ልቡ የደነደነ ዓለም ዓይኑ ታውሮ ሰው ያመልካል። ለጣዖትና ስዕል ይሰግዳል።

(ይቀጥላል % )

Wednesday, September 24, 2014

ስለመላእክት ያለው አስተምህሮ ምን ይመስላል?


( ክፍል ሁለት )
 


3/የቅዱሳን መላእክት አገልግሎት


በክፍል አንድ ጽሁፋችን ስለመላእክት ስያሜ ትርጉም፤ ስለአፈጣጠራቸው፤ ስለፈቃዳቸውና ተልእኰአቸው በጥቂቱ ለማየት ሞክረን ነበር። በክፍል ሁለት ጽሁፋችን ደግሞ ቀሪውን ነጥብ እግዚአብሔርን እንደፈቀደ መጠን ለማየት እንሞክራለን።
ቅዱሳን መላእክት የፈጣሪያቸውን ትእዛዝ ሳይጠብቁ  የትም እንደማይንቀሳቀሱ እርግጥ ነው። በዚህም የተነሳ እግዚአብሔር በወደደውና በፈቃደው ቦታ ቅዱሳኑን መላእክት ለእርዳታና ለትድግና ይልካቸዋል። 

«የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል» መዝ 34፤7

እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ሰዎች የእግዚአብሔር ጥበቃና እርዳታ ዘወትር ይደረግላቸዋል ማለት መላእክቱ በራሳቸው ፈቃድ ይንቀሳቀሳሉ ማለት አይደለም። አንዳንዶች ይህንን ጥቅስ በመጠቀም «መላእክት በተጠሩ ጊዜ በተናጠል መጥተው ያድኑናል» ወደሚል ድምዳሜ በመድረስ ከመላእክት አማላጅነት ጋር ለማያያዝ የሚፈልጉ ወገኖች አሉ። ነገር ግን ዳዊት በመዝሙሩ በግልጽ እንደተናገረው
 «በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል» ካለ በኋላ ሰው ሁሉን በሚችል በእግዚአብሔር ፈቃድ ስር ካደረገ «እግዚአብሔርን፦ አንተ መታመኛዬ ነህ እለዋለሁ አምላኬና መሸሸጊያዬ ነው» በማለት እግዚአብሔር ታዳጊ አምላክ እንደሆነ በማሳየት፤  ከእግዚአብሔር ዘንድ ደግሞ ለእንደዚህ ዓይነቱ አማኝ የተሰጠው የጥበቃ ተስፋ በቅዱሳን መላእክቱ በኩል መሆኑን ከታች ባለው ጥቅስ ይነግረናል።

«ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፥ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም። በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና» 
 ይላል በዝማሬው። መዝ 91፤ 1-16 (ሙሉውን ያንብቡ)
በተመሳሳይ መልኩ እግዚአብሔርን መታመኛቸው ላደረጉ ሰዎች የእግዚአብሔር ጥበቃ በመላእክቱ በኩል ሲፈጸም እንመለከታለን።

«ጴጥሮስም ወደ ልቡ ተመልሶ፦ ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ አለ» የሐዋ 12፣11

 ጴጥሮስን ሄዶ እንዲያድን የላከው ጌታ ነው። መልአኩ የተላከውም ጴጥሮስን እንዲያድን ነው። ቅዱሳን መላእክት እንደስማቸው ለሚገዙለት ጌታ ይላካሉ። አድኑ የተባሉትን ያድናሉ። ለመዓትም ይሁን ለምህረት መላእክቱ የሚላኩት በእግዚአብሔር ትእዛዝ እንጂ ሰዎች ስለጠሯቸው ወይም ስለፈለጓቸው አይደለም።
 በብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ ወደቴስቢያዊው ኤልያስ መልአኩ በተላከ ጊዜም  አካዝያስ ስለህመሙ ምክንያት እግዚአብሔርን በጸሎት ከመጠየቅ ፈንታ ወደአቃሮን ብዔል ዜቡል ፊቱን ባዞረ ጊዜ መልአኩ «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» በማለት የመጣበት ጉዳይ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ትእዛዝ ለመፈጸም እንደሆነ አስረግጦ ሲናገር፤

 «የእግዚአብሔርም መልአክ ቴስብያዊውን ኤልያስን፦ ተነሣ፥ የሰማርያን ንጉሥ መልእክተኞች ለመገናኘት ውጣና። የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ትጠይቁ ዘንድ የምትሄዱት በእስራኤል ዘንድ አምላክ ስለሌለ ነውን? ስለዚህም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ትሞታለህ እንጂ ከወጣህበት አልጋ አትወርድም በላቸው አለው። ኤልያስም ሄደ» 1ኛ ነገ 1፤3-4

«እግዚአብሔር እንዲህ ይላል» ማለቱ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተቀብሎ ለመፈጸም መምጣቱን ያስረዳል። ወደኤልያስ መልእክቱ ይመጣ ዘንድ ያስፈለገውም ኤልያስ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ይከተል ስለነበር መሆኑ እርግጥ ነው። በሌላ ቦታም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ይፈጽሙ ከነበሩ ደጋግ ሰዎች መካከል አንዱ ወደሆነው ወደቆርኔሌዎስም ዘንድ ሲልክ  እንመለከታለን።

«ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው፦ በዚች ሰዓት የዛሬ አራት ቀን የዘጠኝ ሰዓት ጸሎት በቤቴ እጸልይ ነበር፤ እነሆም፥ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው በፊቴ ቆመና። ቆርኔሌዎስ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ ምጽዋትህም ታሰበ»  የሐዋ 10፤ 30-31

የቆርኔሌዎስ ስለጸሎቱ መሰማትና ስለምጽዋቱም በእግዚአብሔርን ዘንድ መታሰብ የሚናገር መልእክተኛ መላኩን ስንመለከት ዳዊት በዝማሬው እንዳመለከተው በልዑል መጠጊያ ለሚኖሩ ሁሉ መላእክቱ እንደሚላኩላቸው በግልጽ ያረጋግጥልናል። በዚሁ ተመሳሳይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስረጂ በማቅረብ የመላእክቱን ተራዳዒነትና አጋዥነት መግለጽ  ይቻላል። ነገር ግን አስረግጠን ማለፍ የሚገባን ቁም ነገር መላእክቱ የሚመጡት በእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ ስር ላሉ ሲሆን ሰዎች የፈለጉትን መልአክ ስለጠሩ ወይም በልባቸው አምሮት የመረጧቸውን  መላእክት ስም ስለተናገሩ አለመሆኑን መገንዘብ ይገባናል። በሰዎች ጥሪ እገሌ የተባለ መልአክ መጣልኝ የሚል አንዳችም አስረጂ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ አይገኝም። በተራዳዒነትና አጋዥነት እንደተላኩ የሚነገርላቸው አብዛኛዎቹ መላእክትም በስም ተለይተው አይታወቁም። ቁም ነገሩ የትኛው መልአክ በታላቅ ኃይል ትእዛዙን ይፈጽማል በማለት በኛ ምርጫ የሚወሰን ሳይሆን በስም የተገለጹም ይሁን ያልተገለጹትን እግዚአብሔር መላእክቱን ልኮ የወደዳቸውን እንዴት ይታደጋል? የሚለውን ከመረዳቱ ላይ ልናተኩር ይገባል። ስለዚህም ተልከው ስላገዙን መላእክት የምንሰጠው ክብር እግዚአብሔር ለኛ ያደረገውን ታላቅ ሥራ ቀንሰን የምናካፍለው መሆን የለበትም። በርናባስና ጳውሎስ ከእናቱ ማህጸን ጀምሮ እግሩ የሰለለውን ሰው በፈወሱበት ወቅት የሊቃኦንያ ከተማ ሰዎች «አማልክት ከሰማይ ወደእኛ ወርደዋል» በማለት መስዋዕት ሊያቀርቡላቸው በወደዱ ጊዜ እነጳውሎስ ያደረጉትን ማየቱ ተገቢ ነው።

«ሐዋርያት በርናባስና ጳውሎስ ግን ይህን በሰሙ ጊዜ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል እየጮኹ ሮጡ፥ እንዲህም አሉ። እናንተ ሰዎች፥ ይህን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን፥ ከዚህም ከንቱ ነገር ሰማይንና ምድርን ባሕርንም በእነርሱም ያለውን ሁሉ ወደ ፈጠረ ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዘወር ትሉ ዘንድ ወንጌልን እንሰብካለ»                የሐዋ 14፤14-15

ጳውሎስና በርናባስ ቅዱሳን በአገልግሎታቸው ሐዋርያት ሆነው ብናከብራቸውና ብንወዳቸውም ቅሉ በእነሱ እጅ በተሰራው አምላካዊ  ድንቅ ሥራ ግን ምስጋናንና ክብርን በጋራ ሊቀበሉ አይችሉም። ክብርና ምስጋና ሁሉ ለእግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ ራሳቸው እንደመሰከሩት የእግዚአብሔር  የብቻው የሆነውን ወደፍጡራን መስጠት ተገቢ እንዳልሆነ ማወቅ ይገባናል።

4/ የእግዚአብሔር መላእክት ሳይላኩ በሰዎች ጥሪ ሥፍራቸው ለቀው ይሄዳሉን?

ቅዱሳን መላእክትን ቅዱሳን ያሰኛቸው ዋናው ቁም ነገር የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ማክበር መቻላቸው ነው። ከእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ ውጪ የሆኑትማ  ከማዕርጋቸው ተሰናብተዋል። ስለዚህ ቅዱሳን መላእክቱ ሰዎች ስለጠሯቸው ወይም ስማቸው ነጋ ጠባ ስለተነሳ ተጠርተናል በሚል ሰበብ ወደየትም አይሄዱም። ከላይ በማስረጃ ለማስረዳት እንደተሞከረው ቅዱሳኑ መላእክት የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለፈጸሙ ወይም እግዚአብሔር ፈቃዱ ይፈጸም ዘንድ በወደደበት ቦታ መላእክቱን ከሚልክ በስተቀር የትኛውም መልአክ ስሙ ስለተጠራ ወይም ስለተወሳ ተከብሬአለሁና ልሂድ፤ ልውረድ በማለት ከተማውን ለቆ የትም አይሄድም። አንዳንድ ሰዎች የመላእክቱን ስም ለይተው በመጥራት ናልኝ የሚሉት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ካልሆነ ትምህርት የተገኘ ልምምድ ውጤት ነው።
 ስሙ ተጠርቶ ይቅርና ገና ሳይጠራ ስፍራውን ለቆ የትም የሚዞረው ሰይጣን ብቻ ነው። ሰይጣን ቦታውን ለቆ የትም የሚዞረው ከእግዚአሔር ፈቃድ ውጪ ያፈነገጠ ሽፍታ ስለሆነ ነው። ቅዱሳን መላእክቱ ያለእግዚአብሔር ትእዛዝ ስማቸው ስለተጠራ ብቻ ሥፍራቸውን ለቀው እንደማይንቀሳቀሱ የሚያውቀው ሰይጣን ራሱን የብርሃን መልአክ አስመስሎ ሊያታልል እንደሚችል ወንጌል ያስረዳናል።
«ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና» 2ኛ ቆሮ 11፤14

ሰይጣን በራሱ ፈቃድ የሚተዳደር ዐመጸኛ ስለሆነ በዓለሙ ሁሉ እየዞረ ሰዎችን ሲያሳስት ይውላል። በተለይም የእግዚአብሔርን ፊት በሚሹ ሰዎች ዙሪያ የጥፋት ወጥመዱን ሊዘረጋ አጥብቆ ይተጋል። ጻድቅ የሆነው ኢዮብንም ያገኘው በዚህ የጥፋት አደናው ወቅት ዓለምን ሲያስስ እንደነበር ከንግግሩ ታይቷል።

«እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም። ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፥ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ»ኢዮብ 1፣7

ስለዚህ ክርስቲያኖች እንደእግዚአብሔር ፈቃድ እየኖሩ ለትእዛዙ በተገዙ ጊዜ በመልካም ትሩፋታቸው ይሁን በችግራቸው ወይም በመከራቸው ወቅት እንዲራዷቸው ቅዱሳኑ መላእክት ከሚላኩ በስተቀር ሰዎች በቀጥታ መላእክቱን ስለጠሯቸው ወይም በስማቸው ስለተማጸኑ የሚመጡ ባለመሆናቸው ከመሰል ስህተት ልንጠነቀቅ ይገባል። ይልቁንም ከእግዚአብሔር ተልእኮ ውጪ ቅዱሳኑ እንደማይንቀሳቀሱ የሚያውቁት የሰይጣን ሠራዊት የብርሃን መልአክ በመምሰል ራሳቸውን ቀይረው ከሚፈጽሙብን ሽንገላ ልንጠነቀቅ ይገባል።

እንደማጠቃለያ፤

 ቅዱሳን መላእክት ሰዎችን ይራዳሉ፤ ያግዛሉ ማለት በሥልጣናቸው የራሳቸውን ክብር ስም ለማስጠበቅ ይሠራሉ ማለት አይደለም። በተፈጥሮአቸውም ውሱን ስለሆኑ በዓለም ላይ በአንድ ጊዜ በስፍሐትና በምልዓት የመገኘት ብቃት የላቸውም። በሁሉም ሥፍራ ተገኝተው ሰዎች ሰለጠሯቸው መልስ አይሰጡም።  ይሁን እንጂ በዓለም ላይ በስማቸው ተሠራ በሚባለው ቤተ ጸሎት በአንድ ጊዜ በስፍሐትና በምልዓት ተገኝተው ጸሎት እንደሚቀበሉ ተቆጥሮ ስማቸው ሲጠራ ይታያል። በቅዱሳን መላእክት ተራዳዒነት እናምናለን ማለት ቅዱሳን መላእክት በራሳቸው ፈቃድ ስለጠራናቸው ይደርሱልናል ማለት አይደለም። ቅዱሳን መላእክት ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ሳይደርሳቸው አይንቀሳቀሱም። የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማም ቅዱሳኑን መላእክት ስናከብራቸው አስተሳሰባችንን በመለጠጥ የምንጓዝበት የእምነት ጽንፍ ወደስህተት እንዳይጥለን ለማስገንዘብ ነው። ቅዱሳኑን ያለትእዛዝ ስለጠራናቸው ብቻ በማይመጡበት ሥፍራ ሰይጣን የብርሃን መልአክ መስሎ ከሚፈጽመው ማታለል ለመጠበቅ ነው።
በአንዳንድ የእምነት ተቋማት ዘንድ ስለመላእክት ያለው አስተምህሮ የተዛባ ምስልን እንደያዘ መገንዘብ ይቻላል። 

   በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አንዳንዶች የመላእክቱን ተፈጥሮ ዘንግተው ሁሉን የመስማት፤ የማወቅና በሁሉ ሥፍራ የመገኘት ችሎታ እንዳላቸው ሲቆጥሩ መታየቱ ተለምዷል። መላእክት በተጠሩ ጊዜ መልስ እንደሚሰጡና እንደሚራዱ የሚሰጠውም ግምት ያለትእዛዝ በራሳቸው ፈቃድ እንደሚንቀሳቀሱ ያደርጋቸዋል። ይህም ወደ እግዚአብሔር ሳይሆን በተራዳዒነት ሰበብ ወደ መላእክቱ ጸሎት የሚያደርሱ ሰዎችን አስገኝቷል። «እንደአናንያ፤ እንደአዛርያ፤ እንደሚሳኤል አድነን ገብርኤል» እያሉ መዘመር እንደተገቢ ከተቆጠረ ውሎ አድሯል። ሠለስቱ ደቂቅን ያዳነው ገብርኤል ነው ከሚለው የትርጉም ፍልሰት ጀምሮ «ገብርኤል አዳኝ ነው» ወደሚለው መልአኩን  ለይቶ የማመስገን የፍቺ ጽንፍ ድረስ ስለመላእክት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ምስል መስጠት ጉዳዩን አደገኛ ያደርገዋል። እኛ የሚያድኑን እግዚአብሔር ፈቃዱን የፈጸመባቸው መላእክቱ ወይስ የእግዚአብሔር ኃይል? በሚለው ሃሳብ ላይም መቀላቀል የታየበት ሁኔታ ሕዝቡ መላእክቱን በተናጠል ወደመጣራት ሲገፋው ይስተዋላል። ከሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ሚካኤል አንተ ታውቃለህ? ብሎ የመጸልይ ልምምድ ስለመላእክቱና ስለእግዚአብሔር ፈቃድ የተቀላቀለ ትምህርት ውጤት ነው።
አንድ ክርስቲያን በአንድ ጊዜ ወደእግዚአብሔርም፤ ወደመላእክቱም ጸሎት ማድረስ አይችልም። ይህ መተላለፍ ነው። እግዚአብሔር ደግሞ ከክብሩም፤ ከምስጋናውም ለማንም አያጋራም። ቀናተኛ አምላክ የሚባለውም ለዚህ ነው። ኢያሱ ወልደነዌ ለህዝቡ እንዲህ አለ።
«ኢያሱም ሕዝቡን፦ እርሱ ቅዱስ አምላክ ነውና፥ እርሱም ቀናተኛ አምላክ ነውና እግዚአብሔርን ማምለክ አትችሉም መተላለፋችሁንና ኃጢአታችሁን ይቅር አይልም» ኢያ 24፤19
ስለዚህ ስለመላእክት ተፈጥሮ፤ ተልዕኰና አገልግሎት በደንብ ማወቅ የሚገባን የእግዚአብሔርን ለመላእክት፤ የመላእክትንም ለእግዚአብሔር በመስጠት የእምነት ሥፍራውን  እንዳናቀላቅል ሲባል ነው። ተፈጥሮአቸውን፤ ተልእኰአቸውንና ተግባራቸውን ለይተን እንወቅ። ከስህተትም ላይ እንዳንወድቅ እንጠንቀቅ። ለዚህም እግዚአብሔር ይርዳን። አሜን!

Wednesday, September 17, 2014

በምድራችን ላይ በክፉ መንፈስ ተነድተው ሕዝብን ያሳሳቱ ሀሰተኛ ክርስቶሶች!

ክፍል ሁለት )

ዘመኑ የቀሳጥያን፤ የሀሰተኛ ትምህርትና የክህደት መፍለቂያ መሆኑን የበለጠ ለማስረዳት ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩትን ማሳየት ጠቃሚ ይመስለናል። የሰው ልጅ በወንጌል ላይ የተገለጠውን ክርስቶስን ሳይሆን በሰው ብልሃት የተቋቋመችውን ምድራዊ ተቋም፤ የሰዎች ድርጅት፤ የአስተምህሮ መንገድና ስብከት እየተከተሉ ከእውነት ሲያፈነግጡ ማሳየት ተገቢ እንደሆነም ይሰማናል። ዛሬም ቢሆን ሰዎች የድርጅት፤ የተቋምና የሰዎች ተከታዮች ሆነው ይታያሉ። እውነታው ግን ክርስቶስ በዚህ ምድር ላይ የመሠረተው አንድም የእምነት ድርጅት ወይም ተቋም  አለመኖሩ ነው። ጲላጦስ ከመሰቀሉ በፊት ኢየሱስን «እውነት ምንድር ነው?» ብሎ ስለሆነው ነገር ጠይቆት ነበር። ( ዮሐ 18፤38) እውነቱ ግን ሰዎች «እስኪ ራሱን ያድን» እያሉ እየተዘባበቱበት የሰቀሉትን ኢየሱስን ማመን ነበር። አይሁዳውያን ሰዎች ራሷን ማዳን የማትችል ምድራዊት የእምነት ተቋም ስለነበራቸው ከእምነት እንጂ ከተቋም ስላልሆነችው የኢየሱስ ስብከት ጆሮአቸውን አልሰጡም። ስለዚህም እውነቱ አመለጣቸው። ዛሬም ሰዎች ክርስቶስን እናምናለን ቢሉም ከተቋምና ከድርጅት ስብከት አልወጡም። በዓለም ላይ በተለያየ ስም የተከፋፈለው የእምነት ተቋም መሠረቱ በሰዎች አስተምህሮ ላይ የተንጠላጠለ ነገር ግን ክርስቶስ ያጠለቀ በሚመስል ድርጅት የሚጠራ መሆኑ ነው። እውነቱ ግን «እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም» ባለው ቃል ጸንቶ መገኘት ብቻ ነው። የምናምነውን ነገር በወንጌል መነጽር እንመርምረው። ወንጌል ካስተማረው ውጪ የሆነው ሁሉ ከሰይጣን የተገኘ ነው።

 
ሚዝራ ጉላም አህመድ (1835-1908)

 ይህ በሃይማኖቱ እስላም የሆነ ሕንዳዊ ዜግነት የነበረው ሰው በአንድ ወቅት ራሱን እንዲህ ሲል ገልጾ ነበር። እስላሞች በመጨረሻው ቀን ከሰማይ ይመጣል ብለው የሚጠብቁት «ማህዲ» የተባለውን ነብይና ክርስቲያኖች ለፍርድ ዳግም ይመጣል ብለው የሚጠባበቁት «ኢየሱስ»ን የምወክል ስሆን እነሆ ሁለቱም በእኔ ውስጥ በሥጋ ተገልጸዋልና ተከተሉኝ በማለት ሲለፍፍ ቆይቷል። ማሳሳት ጥንተ ግብሩ የሆነው ሰይጣን በህንዳዊው አህመድ ውስጥ አድሮ እሱን ብቻ ሳይሆን ለብዙዎች መሳሳት ምክንያት ሆኖ ከእስልምና ሴክት/ክፍል/ አንዱ የሆነውን «አህመዲያ» የተባለው ቅርንጫፍ ፈጥሮ በማለፍ ዛሬም ድረስ ከ20 ሚሊዮን ያላነሱ አባላትን በዓለም ዙሪያ ማፍራት ችሏል።

ሎ ደ ፓሊንግቦኸር (1898- 1968)

በዜግነቱ ኔዘርላንዳዊ የሆነው ፓሊንግቦኸር በሙያው የተዋጣላት ዓሳ አጥማጅ ነበር። በዓሳ አጥማጅነት ሥራው ከሱ ዘንድ ዓሳ ለመግዛት ለሚመጡ ሸማቾች በትንሹ የጀመረውን ስብከት አሳድጎ በስህተት ሰው ወደ ማጥመድ ሥራ አሳደገው። ተከታዮችን ማፍራቱን እንዳረጋገጠ የዓሳ ጀልባውን በመሸጥ ስብከቱን የሙሉ ጊዜው ሥራው በማድረግ የቀጠለ ሲሆን ዓለም ከክፉ ነገር ሁሉ የምትድነው እኔን በማመን ነው እያለ በየጎዳናው ይለፈልፍ ነበር። ትምህርቱን እንደትክክለኛ አድርገው የተቀበሉ ተከታዮቹ ትልቅ የመኖሪያ ቤት ገዝተው የሰጡት ሲሆን በስተመጨረሻም እኔ «ኢየሱስ» ነኝ በማለት ስብከቱን ገፍቶበታል። አንዳንዶች ይህ ሰው ከሀዲ ነው ብለው ቢያወግዙትም ፓሊንግቦኸር «እግዚአብሔር» ወደመሆን ይለወጣል በማለት ይከራከሩለት የነበሩ ተከታዮችን ማፍራት ችሏል። ይሁን እንጂ ብዙ ጊዜ አግብቶ በመፍታት የሚታወቀው ይህ ቀሳጢ እንኳን ሌሎችን ሊያድን ይቅርና ራሱን ከሞት ማዳን ሳይችል ቀርቶ እስከወዲያኛው አሸልቧል።

ኃይለሥላሴ (1892-1975)

 የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት የነበሩት አፄ ኃይለ ሥላሴ ራሳቸውን እንደመሲህ አድርገው ባይቆጥሩም መሢህ ናቸው የሚሏቸው ወገኖች አሉ። ንጉሡ በአንድ ወቅት በሳቸው ዙሪያ ስለሚባለው ነገር ተጠይቀው «እኛ ሰው ነን እንጂ መሲህ አይደለንም» ብለው የመለሱ ቢሆንም ተከታዮቻቸው በንጉሡ ምላሽ ዙሪያ የሰጡት ማስተባበያ «የኛ መሲህ ያለውን ትህትና ተመልከቱ» በማለት የንጉሡን ምላሽ ከአትህቶ ርእስ ጋር በማያያዝ ለማሳመን ቢሞክሩም እውነታው ግን አፄው መሲህ አለመሆናቸው ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለውለታ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አፄ ኃይለ ሥላሴ ለመታሰቢያቸው አርኬ እና መልክእ በመድረስ በነግህና በሰርክ ጸሎት ታስባቸው ነበር። አንዳንዶች የዋሃን አፄው አይሞቱም የሚል ግምት የነበራቸው ቢሆንም ደርግ የገደላቸው መሆኑ ይታወቃል። ከጃማይካ ህዝብ 5% የሚሆነው የራስ ተፈሪያን እምነት ተከታይ ሲሆን በአሜሪካም ብዙ አባላት አሉት።

ኤርነስት ኖርማን (1904-1971)


  አሜሪካዊ የኤሌክትሪካል ኢንጂነር ባለሙያ የነበረና (ዩራንየስ አካዳሚ ኦፍ ሳይንስ) መስራች የሆነ ሰው በአንድ ወቅት ከሙያው ውጪ እብደት መሰል ስብከት ጀምሮ ነበር። ከዚህ በፊት በዚህ ምድር ላይ የተገለጸው «ኢየሱስ» እኔ ነበርኩ። ወደሰማይ ባርግም በዚህ ምድር ላይ በሊቀ መልአክ ሩፋኤል አምሳል ነበርኩኝ እያለ ቢቀላምድም ተከታዮችን ከማፍራት የከለከለው ነገር አልነበረም። ይሁን እንጂ ይህ የዘመኑ ቀሳጢ እንኳን ለሌሎች ሊተርፍ ይቅርና ለራሱም መሆን ሳይችል ቀርቶ በጉሮሮ ህመም ሲሰቃይ ቆይቶ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

ክሪሽና ቬንታ (1911-1958)

 ቬንታ በሳንፍራንሲስኮ የተወለደው ሲሆን በሁለተኛው ዓለም ጦርነት የአሜሪካ ወታደር በመሆን አገልግሏል። ከተመለሰም በኋላ ቀደም ሲል አቋቁሞት የነበረውን ተቋም በማንቀሳቀስ 1948 ዓ/ም «የጥበብ፤ የእውቀት፤ የእምነትና የፍቅር ፏፏቴ» የተሰኘ የክህደት ድርጅት ሥራውን ጀምሯል። ቬንታ የክህደት ደረጃውን በማሳደግ «እኔ ኢየሱስ ነኝ» ከማለቱም ባሻገር የማኅበሩ አባል ለሚሆኑ ሰዎች «ያላችሁን ሀብትና ንብረት ለማኅበሩ ገቢ አድርጉና ሰማያዊ መዝገብ አከማቹ» በማለት ሀብታቸውን በመሰብሰብ ለበጎ አድራጎት ሥራ ለማዋል የሞከረ ቢሆንም ሀብታቸውን ተሞልጨው፤ ሚስቶቻቸውን በቬንታ የማማገጥ ተግባር የተፈጸመባቸው ሁለት ተከታዮቹ በቂም በቀል ተነሳስተው ቦንብ በማፈንዳት አብረው ሊሞቱ ችለዋል። የክሪንሽና ቬንታ የክህደት ተግባርም እስከወዲያኛው በዚያው አክትሟል።

አህን ሳንግ ሆንግ (1918- 1985)

 በደቡብ ኮሪያ የተወለደ ይህ ሰው  በ1964 ዓ/ም «የአዲስ ኪዳን ፋሲካ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን» የሚል የሃይማኖት ተቋም መስርቶ ነበር። በኋላ ላይ ደግሞ «ዓለም አቀፍ የተልእኮ ማኅበር የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን»  የሚል ሁለተኛውን ድርጅት አቋቁሟል። ሳንግ ሆንግ እሱ የኢየሱስ ዳግም ምጽአት ምልክት መሆኑን ይሰብክ ነበር። በአዲስ ኪዳን ፋሲካ ቤተ ክርስቲያኑ እንደመምህር ሲቆጠር በዓለም አቀፍ የተልእኮ ቤተክርስቲያኑ ደግሞ እንደእግዚአብሔር ይቆጠራል።  የቤተክርስቲያኒቱ ዋና አመራር የሆነችው ዛንግ ጊልጃህ የተባለችው ሴት በገላትያ 4፤26 ላይ የተመለከተውን ትንቢት የምታሟላ እሷ ናት ስለሆነች «የኢየሩሳሌም እናት» ወይም «የእግዚአብሔር እናት» ተብላ ትጠራለች።
የቤተ ክርስቲያኑ መሥራች ሳንግ ሆንግ ደግሞ «እግዚአብሔር አብ» ተብሎ ይጠራል።


ሱን ሚዩንግ ሙን (1920- 2012)


 በሰሜን ኮሪያ ተወልዶ በደቡብ ኮሪያ ያደገው ሙን «የውህደት ቤተ ክርስቲያን» መሥራች ሲሆን ራሱን ሁለተኛው ኢየሱስ እንደሆነና  ከዚህ ቀደም ኢየሱስ በሥጋ ተገልጦ ሳለ ሳይጨርሳቸው የሄደውን ጉዳይ የሱ መገለጽ ማስፈለጉን በአደባባይ የሚናገር ሰው ነበር። ሚስተር ሙን ባለቤቱን « ሃክ ጃን ሃን»ን የሚጠራት አዳምና ሔዋን ያበላሹትን ዓለም በማጽዳት መልካም ቤተሰብን በዓለም ላይ ለመመሥረት የተፈጠረች ናት በማለት ያሞካሻት ነበር። ሙን «የተባረከ የኅብረት ጋብቻ» በሚል ዘመቻ በአንድ ቀን እስከ 30 ሺህ የሚቆጠሩ ጥንዶችን  አሜሪካ ባለችው በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ጋብቻ በማስፈጸም ዝናው ይታወቃል። ሙን በአሜሪካን ሀገር ሳለ በፈጸመው የታክስ ማጭበርበር ወንጀል ተከሶ 18 ወራት ተወስኖበት፤ ከዚህ ውስጥ የ13 ወራት እስራቱን ቅሞ በአመክሮ ሊለቀቅ ችሏል። ሱን ሙን  ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ ሃብት ያለው ሲሆን የተለያዩ ኮርፖሬሽኖችንና የአክሲዮን ማኅበራት አሉት። ሃሳዊው ሙን በተወለደ በ92 ዓመቱ በኒሞንያ በሽታ ሞቶ እስከወዲያኛው ተቀብሯል። እሱ ቢሞትም በሱ የሀሰት ትምህርት የተታለሉ 4 ሚሊዮን አባላት በተለያዩ የዓለም ሀገራትን ለማፍራት ችሏል።

ይቀጥላል%

Wednesday, September 10, 2014

በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ!



እኛ ነን ወደአዲሱ ዓመት የደረስነው ወይስ ዘመኑም እንደእኛው እየሄደ ነው? 

  ቆሞ የሚጠብቅ ዘመን የለም። ዘመኑም እኛም በዘመኑ ውስጥ እየሄድን ነው። እግዚአብሔር በዓመት፤ በዓመቱ የሚሰራው አዲስ ዘመን የለም። እግዚአብሔር ዘመናትን የሠራው አንድ ጊዜ ነው።  በእግዚአብሔር አስቀድሞ የተሠራው ዘመን በራሳችን እድሜ ላይ ሲቆጠር «አዲስ ዘመን» ከማለታችን በስተቀር ዘመኑም ለማለቅ ራሱ ወደእርጅና እየተጓዘ ነው።  ሰውም ዘመናትም የማለቂያ እድሜ አላቸው። ዘመናት የተሠሩት፤ ለሰው ልጆች አገልግሎትና የእግዚአብሔርን ፈቃድ አውቀው መልካሙን ሁሉ ይሠሩባቸው ዘንድ ነው። እንኳን «ለአዲሱ ዘመን አደረሰን!» ስንል እኛ በዘመን ውስጥ መታደሳችንንና መለወጣችንን መናገራችን ነው። እንደዚያ ካልሆነማ ዘመናት የተሠጣቸውን ግዳጅ እየፈጸሙ ወደተሰጣቸው እርጅና እየሄዱ እንጂ መቼ ቆመው ይጠብቁናል? ክረምትና በጋ፤ ብርሃንና ጨለማ፣ ዘርና ማዕረርን ዘመናት ከመስጠት አለማቆማቸውና በዘመን ስሌት መፈራረቃቸው እስከጊዜው የተሰጣቸውን ግዳጅ እየተወጡ መሆናቸውን ልብ ልንል ይገባል። እድሜአቸው አልቆ እስኪጠቀለሉም ይህንኑ ግዳጃቸውን ይወጣሉ። 

  መዝ 102፤25-26 «አቤቱ፥ አንተ ከጥንት ምድርን መሠረትህ፥ ሰማያትም የእጅህ ሥራ ናቸው። እነርሱ ይጠፋሉ፥ አንተ ግን ትኖራለህ ሁላቸው እንደ ልብስ ያረጃሉ፥ እንደ መጐናጸፊያም ትለውጣቸዋለህ፥ ይለወጡማል»

ሐዋርያው ጴጥሮስም በመልዕክቱ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደምንጠባበቅ መናገሩ አሁን ያለን ሰማይና የምንኖርባት ምድር አርጅተው እንደሚለወጡ በግልጽ ያስረዳናል።

2ኛ ጴጥ 3፥13 «ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን»

 ስለዚህ በዘመን ውስጥ በእድሜ ጣሪያ የምንጓዝ እኛ የሰው ልጆች ምን ማድረግ ይገባናል?
በጎ መመኘት በጎ ነው። በጎ መመኘት ብቻውን በጎ ነገር አያመጣም። የተመኘነውን በጎ ነገር ለመሥራት በጎ ጥረት ያስፈልገናል። አዲስነት ከእኛነታችን ውጪ የሚገኝ አይደለም። ዘመን በተቆጠረ ቁጥር «እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ» መባባሉ ጥሩ ቢሆንም ባልተለወጠ ማንነታችን ውስጥ ምን አዲስ ለውጥ አይመጣም። መታደስ፤ መለወጥ ለሰው ልጆች ማንነት ልዩ ግኝት ስለሆነ መለወጥ ያለብን እኛ ነን።

 ቁጡና ቂመኛ ሆነን ስለአዲሱ ዘመን ማውራት ምን ይጠቅማል? በውሸትና በቅድስና ጉድለት እየኖርን ከጉዞው ጨብጠን ልናስቀረው ስለማንችለው አዲስ ዘመን መልካምነት መመኘት በራሱ የሚጨምርልን አንዳች ነገር የለም።
ይልቁንስ ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገረውንና ሁልጊዜ እያነበብን ለመተግበር የተቸገርነውን በጎ ነገር እየፈጸምን ስለአዲስ ዘመን በጎ ምኞት እናስብ። 

 «በእርግጥ ሰምታችሁታልና፥ እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል፤ ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ። ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፥ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም። ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ»  ኤፌ 4፤21-32

አለበለዚያ ዘመን ካልሰራንበት «እንኳን አደረሳችሁ ሲባባሉብኝ ጊዜያቸውን በከንቱ ፈጸሙ\ ብሎ በኋለኛው ቀን እንዳልሰራንበት ይመሰክራል።
«ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል» ስለዚህ ንስሐ እንግባ፤ በልባችንም መታደስ እንለወጥ! ለዚህም እግዚአብሔር ይርዳን! አሜን!

Saturday, September 6, 2014

በምድራችን ላይ በክፉ መንፈስ ተነድተው ሕዝብን ያሳሳቱ ሀሰተኛ ክርስቶሶችና ነብያት!


አን ኤልዛቤጥ  ሊ (1736-1784)
በእንግሊዝ አገር የተነሳችና «ተንቀጥቃጮች» የተሰኘ ሃይማኖት የፈለሰፈች፤ ተከታዮቿም «እናታችን» እያሉ የሚጠሯት ሀሳዊ ክርስቶስ ሆና ተነስታ ነበር። ስታስተምርም ራሷን የምትገልጸው እኔ በሴት መልክ የተገለጥኩ ሁለተኛው ኢየሱስ ነኝ እያለች ብትሰብክም እንኳን ለሌላው ልትተርፍ ይቅርና እራሷን ማዳን ሳትችል ቀርታ እስከምጽአት የመጨረሻውን ፍርድ ድረስ ላትነሳ ሞታ በድንጋይ ታትማለች።


        **************************************************


ጆን ኒኮላስ ቶም (1799-1838)
በእንግሊዝ ሀገር ኮርንዎል ተወልዶ ያደገና  የወይን ነጋዴ ሆኖ ሲሰራ የቆየ ሰው ነው። በሥራውም ላይ በታክስ ማጭበርበር ተከሶ እንደነበር የህይወት ታሪኩን የመዘገበው የኮርንዎል ቤተ መዛግብት ፋይል ያስረዳል። ቶም ሽቅርቅርና መዓዛው በሚያውድ ሽቶ ልብሱን ነክሮ፤ ጢሙን አሳድጎ የሚዞር ሰው ሲሆን የብዙዎችንም ቀልብ መሳብ የቻለ ነበር። ቶም ከወይን ነጋዴነት፤ ከጋዜጣ አዘጋጅነትና ገበሬዎችን ከአነስተኛ ንግድ ባለቤቶች ጋር በጥምረት የዐመጽ መሪነት ድረስ ሲ,ሰራ ቆይቷል። የሕይወት ስኬት ሲጎድለው ከእለታት አንድ ቀን ድንገት ተነስቶ «ሁለተኛው ኢየሱስ ሆኜ በሥጋ ተገልጫለሁ» በማለት ወደስብከት የገባ ሲሆን ተከታዮችን ካፈራ በኋላ በ1834 ዓ/ም ጀምሮ ወደቅዱስ መንፈስ ተቀይሬአለሁ ቢልም ባልተላቀቀው የዐመጽ መሪነቱ ተግባሩ ቀጥሎ በግንቦት 31/1838 ኬንት ከተማ ላይ በጥይት ተገድሎ እስከወዲያኛው ላይነሳ ያሸለበ ሰው ነው።

**************************************************


አርኖልድ ፖተር (1804-1872)
«የኋለኛው ቀን ቅዱሳን» የተባለው የክርስትና ክፍል መሪ የነበረ ሰው ነው። ፖተር በኒውዮርክ ተወልዶ፤ በኢንዲያና ውስጥ በኋለኛው ቀን ቅዱሳን በተባለ ቤተ ክርስቲያን የተጠመቀ ሲሆን በኢሊኖይስ ላይ ደግሞ የሞርሞን ቤተ ክርስቲያን መሥራች በሆነው በጆሴፍ ስሚዝ «ካህን፤ ሽማግሌና የቡራኬ አበው» ተብሎ ደረጃ በደረጃ የተሾመ ሰው ነበር። እስከአውስትራሊያ ድረስ ለስብከት የተጓዘው ፖተር «የኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ በኔ ውስጥ በመግባቱ ከዛሬ ጀምሮ እኔ ሌላው ኢየሱስ ነኝ» እያለ ሲያስተምርና ተከታዮችን ሲያፈራ ቆይቷል። በኋላ ላይ ወደካሊፎርኒያ ተመልሶ በ1872 ዓ/ም ወደሰማይ የማርግበት ሰዓት ደርሷል በማለት የአህያ ውርንጫ ተቀምጦ ከገደል አፋፍ ላይ በደመና ለማረግ ሲጋልብ ወደላይ መውጣቱ ቀርቶ ቁልቁል እስከነ አህያዋ በመምዘግዘግ  ፖተር ዳግም ላይመለስ እስከወዲያኛው አሸልቧል።

         **************************************************

ጆንስ ቬሪ 1813-1880
 ፀሐፊ ተውኔት፤ ገጣሚና በሐርቫርድ የግሪክ ቋንቋ መምህር የነበረ ሰው ነው። ቬሪ እጅግ የጠለቀ እውቀትና ሙያ ያለው ሰው ቢሆንም ከእለታት አንድ ቀን  ለተማሪዎቹ «በማቴዎስ 24 ላይ ዳግም ይመለሳል የተባለው ኢየሱስ እኔ ነኝ» በማለት የተናገረ ሲሆን ይህንኑ ስብከቱን ቀጥሎበት ቀይቷል። በኋላ ላይ  በአእምሮ በሽታ ክፉኛ በመጠቃቱ ለከፍተኛ ጭንቀት ህመም ተጋልጦ  እህቱ እሱን የማስታመም ኃላፊነት ወድቆባት ነበር።  ቬሪ «ኢየሱስ ነኝ» እያለ ቢሰብክና ብዙዎችንም ቢያታልል ከአእምሮው በሽታ ሳይድን  በ1880 ዓ/ም በተወለደበት በማሳቹሴትስ ሞቶ በትልቅ ሃውልት መቃብሩ ተደፍኖ ዛሬ ድረስ ይታያል።




******************************************



ባሃ ኡላህ (1817-1892)
የእስልምናው አንዱ ክንፍ ከሆነውና በዛሬይቱ ኢራን ያለው የሺአይት እስላም ቤተ ሰብ የተወለደው ባሃኡላህ በዚሁ እምነት ስር ያደገ ሲሆን ሃይማኖታዊ ፍልስፍናው በፈጠረበት ስሜት ተነሳስቶ ዓለም በአንድ እምነትና መተሳሰብ ስር መጠቃለል አለባት ብሎ በመነሳት ራሱን «የባቢ እምነት» ፍጻሜ ነብይ አድርጎ በመቁጠር ከሺአት ተገንጥሎ በስሙ የባሃኡላህ እምነትን የመሠረተ ሰው ነው። ትምህርቱንም በባግዳድ ጀምሮ በእስልምና ህግ ተይዞ በሃይፋ/ እስራኤል/ እስከተሰቀለበት ቀን ድረስ እኔ የመጨረሻው የእግዚአብሔር ነብይ ነኝ፤ በኋለኛውም ቀን ለፍርድ እመጣለሁ ሲል የነበረ ሰው ነው። ይህ የሃይፋው ዋናው የባሃኢ እምነት ማእከል በዓለም ላይ ላሉ የእምነቱ ተከታዮች ቅዱስ ስፍራ ሲሆን አጠቃላይ መመሪያው የሚመነጨው ከዚሁ ከሃይፋው ማእከል ነው። 
 እግዚአብሔር ራሱን በሰው አምሳል ከገለጸባቸው መንገዶች አንዱ ባሃኡላህ ሲሆን የሰዎችን ነፍስ በማጥራት ምድርን ወደገነት የመቀየር ተልዕኮ ያነገበ እሱ ብቻ መሆኑን ሲሰብክ ቆይቷል። ባሃኢዎች እንደመንፈስ አባታቸው ሲዖልና ገነት ተብለው በሰዎች አእምሮ የተሳሉ ግምቶች እንጂ በእውን ሰዎችን ለመቅጫ በእግዚአብሔር የተፈጠሩ አይደለም ይላሉ። ባሃኡላህ የሞተው በ1892 በስቅላት ነው።
ሃይፋ/እስራኤል የባሃኢ ዋና ማእከል


*******************************************


ዊሊያም  ዳቪየስ (1833-1906)
የሞርሞን ቤተ ክርስቲያን ቅርንጫፍ በሆነውና የኋለኛው ቀን ቅዱሳን በተባለው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሪ የነበረ ሰው ነው። በደቡብ የዋሽንግተን ስቴት ዋላዋላ ከተማ ላይ «የእግዚአብሔር መንግሥት» ማኅበርን መስርቷል። ተከታዮቹንም «እኔ ሊቀ መላዕክት ቅዱስ ሚካኤል ነኝ» በማለት ያስተማረ ሲሆን «አዳም፤ አብርሃም፣ ዳዊት» ሆኖ ከዚህ በፊት በምድር ላይ የመጣውም እሱ ራሱ መሆኑንም በድፍረት ይናገር ነበር። በኋላ ላይ ሚስት አግብቶ በየካቲት 11/1868  «አርተር» የተባለ ልጁን እንደወለደ  ልጁን «በሥጋ የተገለጠ የእግዚአብሔር ልጅ» ነው በማለት ሲናገር «ዴቪድ» የተባለ ሁለተኛ ልጁን ሲወልድ ደግሞ እኔ ወደ «እግዚአብሔር አብነት» ተቀይሬአለሁ እያለ ይሰብክ ነበር። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ሁለቱም ልጆቹ በጉሮሮ በሽታ ሲሞቱ ተከታዮቹ ባቀረቡበት ክስ የቤተ ክርስቲያኑን ንብረት ሸጦ በመክፈልና ከተማውን ለቆ ወደካሊፎርንያ በመሰደድ መልሶ ለመደራጀት ሞክሮ ሳይሳካለት ልጆቹን እንደቀበረ ሁሉ እሱም ሞቶ ድንጋይ ተጭኖት ይገኛል።



 ይቀጥላል%

Saturday, August 30, 2014

ስለመላእክት ያለው አስተምህሮ ምን ይመስላል?




(ክፍል አንድ)

በዓለማችን ላይ ባሉ በኦርቶዶክሳዊያንና በካቶሊካዊያን  ቤተ እምነቶች ውስጥ  ከሰማያውያን ፍጥረቶች ውስጥ መላእክት በእምነት ህግጋቶቻቸው ከፍተኛውን ስፍራ ይዘው ይገኛሉ።  እንደጥንታውያኑ ቤተ እምነቶች አይሁን እንጂ በወንጌላውያን ቤተ እምነቶችም ውስጥ ከተወሰኑቱ በስተቀር ስለመላእክት ያላቸው እምነትና እውቀት ጥቂት አይደለም።   የሰው ልጆች ስለቅዱሳን መላእክት ያለን እውቀት ከፍ እንዲልና ትኩረት እንድንሰጥ የሚያደርገን ምክንያት መኖሩ እርግጥ ነው። መጽሐፍ ቅዱሳችንም ስለመላእክት ምንነትና ተግባር  በብዙ ቦታ ላይ ጠቅሶ የሚገኘው ያለምክንያት ባለመሆኑ በዚያ መነሻነት ስለመላእክት ያለን ግምት ከፍ ቢል የሚያስደንቅ አይሆንም። እግዚአብሔር በቅዱስ ቃሉ ውስጥ ይህንን ዓይነት መልእክት ማስቀመጡም ስለመላእክት ያለን ግንዛቤ እንዲያድግ ስለፈለገ በመሆኑ ዘወትር ቃሉን በማንበብ እንመረመራለን። መንፈስ ቅዱስ በሚሰጠን መገለጥም ስለመላእክት ያለን እውቀት ከፍ ይላል። ምክንያቱም በሰው ልጆችና በመላእክት መካከል ያለው ግንኙነት እጅግ የጠበቀ በመሆኑ ስለመላእክት ማወቁ እጅግ ጠቃሚ ነው።
      በተመሳሳይ መልኩም ስለመላእክት ያለን እምነትና በቅዱስ ቃሉ ላይ ያልተመሠረተ እውቀት እንደዚሁ የሚኖረንን ግንኙነት ከማበላሸቱም በላይ የሰው ልጆችንም ይሁን መላእክትን በፈጠረው በእግዚአብሔር ላይ ያለንን የአምልኰ መንገድ ከመስመሩ ሊያወጣ ስለሚችል እጅግ ብርቱ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ነገር መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል። የአምልኰ ስህተት እንደጊዜያዊ እክል የማይታይና በቀላሉ ሊታረም እንደሚችል የሚታሰብ ባለመሆኑ ስህተቱ ዘላለማዊነት ባላት በነፍስ ላይ ዘላለማዊ ዋጋን የሚያስከፍል ጉዳይ ስለሆነ እጅግ ብርቱ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል። 
  ስለሆነም  የእግዚአብሔርን ቃል መሠረት ባደረገ መልኩ ስለመላእክት ያለን እውቀት መልካም የመሆኑን ያህል ቃሉን በሳተ መንገድ ያለን እውቀትም በተቃራኒው የጎደለ ከሆነ ጎጂነቱ የከፋ መሆኑን ለማስገንዘብ እንዲቻል በተለያየ አቅጣጫ ስለመላእክት የሚሰጠውን ትርጉምና የእምነት አስተምህሮን በተመለከተ ቅዱስ መጽሐፍን ዋቢ በማድረግ ለማሳየት እንሞክራለን።

1/ ስለመላእክት ማወቅ ለምን አስፈለገ?

እግዚአብሔር በቃሉ አማካይነት ያስተምረናል።  የቃሉ ምንጭ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለመላእክት እግዚአብሔር በብዙ ቦታ ተናግሯል፤ ተግባራቸውንም በተወሰነ መልኩ አሳይቶናል። እግዚአብሔር በቃሉ የሚነግረን ለእኛ እንዲበጀን ስለሆነ ስለመላእክት እንድናውቅለት ይፈልጋል ማለት ነው። በመሆኑም ስለመላእክት ማወቅ ያስፈለገን እግዚአብሔር በቃሉ አማካይነት ስለመላእክት እንድናውቅ ስለነገረን  ነው። ስለመላእክት ማንነትና ተግባር የነገረንን ካወቅን እግዚአብሔር ለምን እንደፈጠራቸው እንረዳለን። በዚህም የተነሳ ስህተት ላይ ከመውደቅ እንጠበቃለን። ስለመላእክት ነግሮን ሳለ በእኛ ስህተት የተነሳ ከእውቀት ብንጎድል እግዚአብሔር ስላልነገረን ሳይሆን ቃሉን ለመስማት ካለመፈለጋችን የተነሳ ይሆናል ማለት ነው። ማንም ስህተትን ቢያደርግ በተሰጠው ቃል መሠረት ተጠያቂነት አለበት። ስለሆነም ከተጠያቂነት ለመዳን ስለመላእክት ማንነት ማወቅ ያስፈልገናል። ችግሩ ስለመላእክት ያለን ስህተት የሚነሳው እግዚአብሔር በቃሉ ከተናገረው ውጪ የራሳችንን ግምትና ስሜት ስንጨምርበት ነው። ስለዚህ በዚህ ጽሁፍ የሚዳሰሰው ክርስቲያኖች ሁሉ በእጃቸው የያዙትን መጽሐፍ ቅዱስ ዋቢ በማድረግ ነው። ሌላ የትኞቹም ስለመላእክት የተጻፉ አስረጂዎች መነሻቸው ወይም መለኪያቸው ቅዱሱ መጽሐፍ ከሆነ ስለመላእክት የሚኖረው እውቀት ያልተዛነፈ ይሆናል።
«ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል አንተም እውቀትን ጠልተሃልና» ሆሴዕ 4፤6 እንዳለው እንዳንጠፋ ስለመላእክት ማንነትና ምንነት ማወቅ አለብን።

2/ የመላእክት ተፈጥሮ

የመላእክትን ተፈጥሮ በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ  ሰፊ የሆነ ማብራሪያ አይሰጠንም።    ያ ማለት ግን ስለመላእክት ተፈጥሮ ለአማኞች የሚበቃ ትምህርት የለውም ማለት አይደለም። በመሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ የዘመን መነሻና ፍጻሜ ከሌለው ከእግዚአብሔር እውቀት ውስጥ ለሰው ልጅ በሚመጥነው መልኩ የተሰጠው ቃል በመሆኑ ብዙ ማብራሪያ መስጠት አይጠበቅበትም። በዮሐንስ ወንጌል ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ዓለም ራሷ ሰሌዳ፤ ውቅያኖሶች ሁሉ የብርዕ ቀለም ቢሆኑ መያዝ እንደማይችሉ ያስረዳናል።
ዮሐ 21፥25 «ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል»
ስለዚህ የመላእክትን ማንነትና ተፈጥሮ ለማወቅ መጽሐፍ ቅዱስ የነገረንን ይዘን እየተማርን፤ ያልነገረንን ደግሞ በእምነት እንደተነገረን ያህል ተቀብለን እንጓዛለን እንጂ ያልተነገረውን ለመናገር የግድ የራሳችንን ስሜቶችና ፍላጎቶች በመናገር በማንወጣው አዘቅት ውስጥ ገብተን አንዳክርም። «ለጠቢብሰ አሐቲ ቃል ትበቍዖ» እንዲሉ።
 ስለዚህ መላእክት በቁጥር ስንት ናቸው? አፈጣጠራቸው እንዴት ነው?  ሥልጣናቸው?  ስማቸው? ወዘተ የተመለከተውን ነጥብ ከተወሰኑት በስተቀር  መጽሐፍ ቅዱስ ዝም ስላለ እኛም ዝም እንላለን እንጂ  መጽሐፍ ቅዱስ ያልጠራቸውን በጕስአተ ልብ አንጠራቸውም።  ይልቅስ መጽሐፍ ቅዱስ የነገረንን መረጃ እንመልከት። በመዝሙረ ዳዊት ላይና በዕብራውያን መልእክት ላይ የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ስለመላእክት ተፈጥሮ  ያስተምረናል።
መዝ 104፥4  «መላእክቱን መንፈስ የሚያደርግ፥ አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል»
 ዕብ 1፥7 «ስለ መላእክትም። መላእክቱን መናፍስት አገልጋዮቹንም የእሳት ነበልባል የሚያደርግ» ይላል።
ከዚህ የእግዚአብሔር ቃል ተነስተን መላእክቱ መንፈስና የእሳት ነበልባል መሆናቸውን እንረዳለን።  መናፍስትም፤ የእሳት ነበልባልም ያደረጋቸው እግዚአብሔር ነው። እነዚህ መንፈሳውያንና እሳታውን መላእክት ከፍጥረታት መካከል አንዱ ክፍል ናቸው ማለት ነው። መላእክቱ መናፍስት (ረቂቃን) እና እሳታውያን  መሆናቸው የሚያሳየን ነገር ቢኖር እግዚአብሔር የሰውን ልጅ በፈጠረበት መንገድ አልፈጠራቸውም ማለት ነው። መንፈስም፤ እሳትም በመሆናቸው  መላእክት እንደሥጋውያን  እርጅናና ሞት አያገኛቸውም።
ኢዮብ 34፥15 «ሥጋ ለባሽ ሁሉ በአንድነት ይጠፋል፥ ሰውም ወደ አፈር ይመለሳል» እንዳለው።
በሌላ ቦታም  መላእክት ሕያው መንፈሳዊ ፍጥረታት መሆናቸውን ቅዱስ ቃሉ ሲነግረን፤ ሥጋውያን የሆንን  እኛ ትንሣዔ ሙታን እንደማይመለከታቸው እንደመላእክት እንደምንሆን ተነግሮናል።
ማር 12፥25  «ከሙታንስ ሲነሡ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፥ አይጋቡምም»
    ስለመላእክት አፈጣጠር የሚናገር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ  በተለምዶ «አክሲማሮስ» ወይም  በመጠሪያው «ሔክሳሄሜሮስ» የተባለ መጽሐፍ አለ። በስድስት ቀን ውስጥ እግዚአብሔር ስለፈጠራቸው ሃያ ሁለቱ ስነፍጥረታት አመጣጥ የተነገረበት ይህ መጽሐፍ በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ ያልተነገረውን  በዝርዝር ይተርካል።  በጽርዕ ቋንቋ «ሔክሳ» ማለት «ስድስት» ማለት ሲሆን «ሄሜር» ማለት «ቀን» ማለት ነው። ይህም የስድስቱ ቀናት ሥነ ፍጥረትን ለማመልከት የገባ ቃል ነው።  ሔክሳ ሄሜሮስን የበረሺት መጽሐፍ ባለቤቶች የሆኑቱ  ዕብራውያን የማያውቁትን ይህን ከ4ኛው ክ/ዘመን በኋላ የተጻፈውንና ስለሥነ ፍጥረት የሚናገረውን መጽሐፍ መጠቀም ሳያስፈልግ እግዚአብሔር በቅዱስ ቃሉ በገለጠው በመጽሐፍ ቅዱስ  ብቻ መላእክት ሞት የማያገኛቸው፤ እሳታውያንና መንፈሳውያን ፍጥረቶች ናቸው ብሎ አፈጣጠራቸውን በአጭር ቃል መግለጽ ይቻላል።

3/ የመላእክት ጠባይና ግብር

ከላይ ባነሳናቸው ርእሶች ላይ ስለመላእክት ማወቅ የሚገባንን ምክንያትና የመላእክትን ተፈጥሮ ከተረዳን ዘንዳ በቀጣይነት ሥራቸውን ልናውቅ ይገባል። ይህም ማንነታቸውንና ከሰው ልጆች ጋር ያላቸው ግንኙነት ምን እንደሆነ እንድናውቅ ያግዘናል። በዚህ መጠይቃዊ ርእስ ስር የሚካተቱ ንዑስ ርእሶች አሉን።

        ሀ/ የመልአክ ስማዊ ትርጉም 

ቁጥራቸውን ብዙ መሆኑን ለማመልከት «መላእክት» የምንላቸው ፍጥረቶች በነጠላ  ስያሜ «መልአክ» ስንል ምን ማለታችን ነው? የሚለውን መረዳት ይገባናል። ይህም የመላእክትን ሥራ ለማወቅ ይጠቅመናል። ሥራቸውን ካወቅን መላእክት ከእኛ ጋር እኛም ከመላእክቱ ጋር ያለንን ግንኙነት ለመለየት ያግዘናል። ያለበለዚያ ከላይ ስናነሳ የቆየንባቸው የማወቅ እድላችን እርስ በእርሱ ይምታታና ባለማወቅ ውስጥ ሆነን የምናውቅ ሊመስለን ይችላል። ይህም ትልቅ ጉዳት ያስከትላል።
 አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (በማኅበረ ቅዱሳን ተሃድሶ ተብለዋል) «መጽሐፈ፡ሰዋስው፡ወግስ፡ወመዝገበ፡ቃላት፡ሐዲስ» በተሰኘው መጽሐፋቸው ገጽ 549 ላይ እንዲህ ሲሉ  ስለ«መልአክ» ግሳዊ ትንታኔን  አትተዋል።
ድርጊቱን ሲገልጡልን «ልኢክ፤ ልኢኮት(ለአከ፤ይልእክ) መላክ፤መስደድ»  ማለት  እንደሆነ በመግለጽ አድራጊውን ሲነግሩን «ለአኪ ማለት ላኪ ወይም ሰዳጅ ማለት ነው ይሉናል። ተደራጊውን ደግሞ «መልአክ ማለት በቁሙ ሹመኛ፣ አለቃ ሲሆን  የእግዚአብሔር መላእክቶችን  ነጠላ የወል ስም  «መልአክ» የሚለው እንደሚወክል ያብራሩልናል።
በሌላ ቦታም የሰባ ሊቃናት ትርጉም እንደሚያስረዳን «ἄγγελος» የሚለው የልሳነ ጽርዕ ትርጉም «ኤንጄሎስ» ማለት «መልእክተኛ» ማለት እንደሆነ እናገኛለን። ዕብራይስጡም «מלאך אלהים » «ሜሌኽ ኤልሂም» ይለዋል። የእግዚአብሔር መልዕክተኛ ማለት ነው።
 ከዚህ የትርጉም  ጽንሰ ሃሳብ የምንረዳው መላእክት ማለት የሚላኩ፣ የሚታዘዙ ፍጥረታት ሲሆኑ ላኪያቸው ወይም ሰዳጃቸው የፈጠራቸው እግዚአብሔር ነው ማለት ነው።  ስለዚህ መልአክ ማለት የሚላክ፤ የሚታዘዝ፤ ተላኪ፤ አገልጋይ፤ አመስጋኝ ማለት ነው።  የአለቃ ኪዳነ ወልድ ትርጉም ከጽርዑና ከዕብራይስጡ ጋር ይስማማል። 

     ለ/ መላእክት በሁሉም ሥፍራ በአንድ ጊዜ መገኘት ይችላሉን?

መላእክት ፍጡራን ናቸው ካልን ከፍጡርነት ባህርይ አንጻር ውሱንነት መኖሩ እርግጥ ነው። በዚያ ላይ የሚላኩ፤ የሚታዘዙ፤ አገልጋዮች መሆናቸው በራሱ መነሻና መድረሻ እንዳላቸው ያሳያል። መልእክት ከሚቀበሉበት መንበረ ጸባዖት ተነስተው ከሚደርሱበት የተልእኰ ሥፍራ ድረስ መውጣትና መውረድ አለባቸው ማለት ነው።  መላእክት የሚወጡበትና የሚወርዱበት መሰላል የእግዚአብሔር ኃይል እንደመሆኑ መጠን መላእክቱን የፈጠረ አምላክ እንዲህ ሲል ይነግረናል።
ዮሐ1፥52  «እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ አለው»
በሁሉም ሥፍራ በአንድ ጊዜ የመገኘት ብቃት ስለሌላቸው የመውጣትና የመውረድ አገልግሎት ይፈጽማሉ ማለት ነው። መላእክቱ ከታዘዙበት ሲወጡ ከነበሩበት ሥፍራ  ለቀው ወደሌላ ሥፍራ ይሄዳሉ። ስለዚህ  ለቀው ከወጡ በኋላ በምስጋና ከተማቸው ውስጥ በመልአካዊ ባህርያቸው አይገኙም ማለት ነው። ከተልእኮአቸውም ሲመለሱ ከፈጸሙበት ሥፍራ ወደቀድሞ ቦታቸው ይመለሳሉ እንጂ በምስጋና ከተማቸውም ሆነ በተልእኰ ስፍራቸው በአንድ ጊዜ የመገኘት ብቃት የላቸውም። ይህንን በደንብ የሚገልጽን የትንቢተ ዳንኤል መጽሐፍ ነው።
አንድ ስሙ ያልተገለጸ የእግዚአብሔር መልአክ በጤግሮስ ወንዝ ዳርቻ ሳለ ወደነብዩ ዳንኤል በተላከ ጊዜ የፋርስ መንግሥት አለቃ (የፋርስ መንግሥትን የያዘ ተቃዋሚ መንፈስ ማለት ነው) ከተላከው መልአክ ጋር ለ21 ቀናት በመዋጋት ከዳንኤል ዘንድ ቶሎ እንዳይደርስ አግዶት ነበር። በኋላም ቅዱስ ሚካኤል ሊረዳው ከመጣ በኋላ ከሌሎች የፋርስ መንግሥታት መናፍስት ጋር ሚካኤልን በዚያ ትቶት ወደተልእኰ ሥፍራው ወደ ነብዩ ዳንኤል መሄዱን ይነግረናል።
ዳን 10፤12-14  «እርሱም እንዲህ አለኝ። ዳንኤል ሆይ፥ አትፍራ ልብህ ያስተውል ዘንድ፥ ሰውነትህም በአምላክህ ፊት ይዋረድ ዘንድ ካደረግህበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ቃልህ ተሰምቶአል እኔም ስለ ቃልህ መጥቻለሁ። የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሀያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ እነሆም፥ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ እኔም ከፋርስ ነገሥታት ጋር በዚያ ተውሁት። ራእዩም ገና ለብዙ ዘመን ነውና በኋለኛው ዘመን ለሕዝብህ የሚሆነውን አስታውቅህ ዘንድ አሁን መጥቻለሁ»
 (የፋርስ መንግሥት አለቃ ማለቱ በፋርስ መንግሥት ላይ አድሮ ዳንኤልንና ወገኖቹን የሚዋጋው መንፈስ አለቃ ማለት ነው) የዚህን እንዴትነት ወረድ ብለን በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ እንመለከታለን።
ነገር ግን ከላይኛው ጥቅስ ውስጥ የምንረዳው ቁም ነገር፤
የተላከው መልአክ ለ21 ቀናት በውጊያ ላይ በመዘግየቱ ወደተላከበት ሥፍራ ለመድረስ አለመቻሉ፤
 * ሚካኤል ለእርዳታ ከመጣለት በኋላ ወደዳንኤል ከመሄዱ በስተቀር  ከሚካኤል ጋር በውጊያውም እየተሳተፈ፤ ወደዳንኤልም መልእክት እያደረሰ ባንድ ጊዜ በሁለቱም ሥፍራ አለመገኘቱ የመላእክትን ውሱንነት ይገልጥልናል።
«ሚካኤልን በዚያ ተውኩት» ማለቱ የነበረበትን ሥፍራ ለቆ መሄዱን ይገልጣል። ስለዚህ መላእክት በሁሉም ሥፍራ አይገኙም። መእክተኛ እንደመሆናቸውም መጠን ሳይላኩ አይሄዱም።  በሁሉም ሥፍራ በአንድ ጊዜ መገኘት /Omnipotent/ የእግዚአብሔር የብቻው ባህርይ ነው።
መላእክት የእግዚአብሔር ፍጥረት እንደመሆናቸው መጠን ሁሉን የማወቅ ሥልጣን አልተሰጣቸውም፤ በሁሉም ሥፍራ በአንድ ጊዜ የመገኘት ብቃትም የላቸውም። በፈጣሪያቸው ሲላኩ ወይም ሲታዘዙ ለአገልግሎት የሚሄዱት እግዚአብሔር ብቻ ስለሚያውቀው ሃሳብና ዓላማ ብቻ በመሆኑ ነው።  የእግዚአብሔርነት ሙላት በሆነው ባህርይ መሠረት ሁሉን የመስማት፤ ሁሉን የማየት፤ ሁሉን የማወቅ ብቃት የላቸውም።  ይልቁንም መላእክቱን በነዚህ ሦስት ጥቅሶች ምስጋናን፤ ተአዝዞንና ተልአኪነትን ሲፈጽሙ እናያለን።
v  መዝ 148፤2  «መላእክቱ ሁሉ፥ አመስግኑት ሠራዊቱ ሁሉ፥ አመስግኑት»
v  መዝ 91፥11 «በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋል»
v  ማቴ 13፥41  «የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ»

    ሐ/ የመላእክት ሥልጣንና ተልእኰ

መላእክት ተፈጥሮአቸው አንድ ዓይነት ቢሆንም በክብርና በሥልጣን ልዩነት እንዳላቸው  ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል። ስለዚህ በክብር፤ በሥልጣንና በአገልግሎት የተለያዩ እንደመሆናቸው መጠን የመላእክቱ ተልዕኰና ሥልጣንም የተለያየ ነው። ለምሳሌ ቅዱስ ሚካኤል የመላእክት አለቃ እንደሆነ በይሁዳ መልእክት (ምዕ 1፤ቁጥር9) ላይ ሚካኤል ከዲያብሎስ ጋር ስለመከራከሩ በተጠቀሰበት አንቀጽ ላይ «የመላእክት አለቃ» ተብሎ ሥልጣኑ ተጠቅሷል።
 በሌላ መልኩም  ምንም እንኳን ስሙ በትክክል ባይገለጽም ለእግዚአብሔር በማይታዘዙ፤ በበደልና በኃጢአት ሙት በሆኑ በዚህ ዓለም ልጆች ላይ ለሚሠራው መንፈስ አለቃ የሆነ በአየር ላይ ሥልጣን የተሰጠው አለቃ እንዳለም ቅዱስ ወንጌል ይነግረናል።   ( ኤፌ 2፤1-2 ) በሌላ ቦታ «ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፤ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና»  1ኛ ዮሐ 3፤8  ስለሚል በስም የተጠራውና በኃጢአት ላይ የሰለጠነው ይህ አለቃ ዲያብሎስ ነው ማለት ነው።
ከዚህ ቃል ተነስተን መላእክትን ሥልጣንና ተግባራቸውን በመመልከት የሚያመሰግኑ፤ የሚላኩትንና የሚታዘዙትን «ቅዱሳን» መላእክት ስንል፤  ለእግዚአብሔር በማይታዘዙ ላይ የሰለጠኑትና በኃጢአት ላይ ሥልጣን ያላቸውን ደግሞ «ርኩሳን» ብለን ልንከፍላቸው እንችላለን። ቅዱሳን መላእክት እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝበትን አገልግሎት የሚፈጽሙ ሲሆኑ ርኩሳኑ መላእክት ደግሞ በጥፋት ላይ የተሰማሩ ናቸው ማለት ነው።
 ንስሐ በሚገባ አንድ ኃጢአተኛ የተነሳ በሰማይ ባሉ መላእክት ዘንድ ደስታ እንደሚሆነው ሁሉ ( «እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል» ሉቃ 15፤10 )
 እንደዚሁ ሁሉ ኃጢአተኛ ሲቀጣ ለተልዕኰው የሚወጡ ክፉዎች መላእክት ስለመኖራቸውም («የመዓቱን መቅሠፍት በላያቸው ሰደደ መቅሠፍትን መዓትንም መከራንም በክፉዎች መላእክት ሰደደ » መዝ 78፤49  ) ሲል ክፉዎች መላእክት መኖራቸውን እንረዳለን።
ስለዚህ በሰው ልጆች ወደእግዚአብሔር መመለስ የሚደሰቱ  ቅዱሳን መላእክት እንዳሉ ሁሉ መቅሰፍትን፤ መዓትንና መከራን የሚያመጡ ክፉዎች መላእክትም አሉ ማለት ነው። ከዚህ ተነስተን መላእክትን በሁለት ልንከፍል እንችላለን።

   መ/ ቅዱሳን መላእክትና ክፉዎች መላእክት 

« ንቁም በበኅላዌነ እስከ ንረክቦ ለአምላክነ» በማለት ያረጋጋው ገብርኤል ነው፤ የካደውና እኔ ፈጣሪ ነኝ ብሎ የታበየው ሣጥናኤል ነው የሚል አስተምህሮ አለ።  በሌላ ጊዜም ይህ ገብርኤል መልአክ የወረወረው ሰይፍ እስከምጽአት ድረስ ወደመሬት ውስጥ እየተምዘገዘገ እየወረደ ነው የሚልም ትምህርት ይሰማል። ገብርኤል «ንቍም በበኅላዌነ» ማለቱን በወቅቱ የሰማና ጽፎ ያቆየልን የለም። መጽሐፍ ቅዱሳችንም ይህን ስለማለቱ አልገለጸውም። ስለዚህ እግዚአብሔር በፈቃዱ ሳይነግረን ወደተወው ጉዳይ ገብተን አንዳክርም። ነገር ግን በክፋትና በኃጢአት ላይ የሰለጠነው ዲያብሎስ በትዕቢት ከማዕርጉ መውረዱን መጽሐፍ ስለሚነግረን ያንን በመቀበል «አለቃ» እንደመባሉ መጠን በአለቅነቱ አብረውት የተሰለፉ ሠራዊት መኖራቸውንም እንገነዘባለን  
   ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ቅዱሳን መላእክት የእግዚአብሔርን ፈቃድና ደስ የሚያሰኘውን አገልግሎት ፈጻሚዎች ሲሆኑ ክፉዎቹ መላእክት ደግሞ የጥፋትና የዐመጻ ኃይሎች ናቸው። ቅዱሳኑ መላእክት ቅዱሳን ያሰኛቸው ዋናው ምክንያት እግዚአብሔርን በመፍራት የሚያገለግሉ፤ ፈቃዱንም ለመፈጸም ፈቃደኞች የሆኑ፤ በተቀመጡበትን ሥፍራ በአምልኰ ጸንተው የተገኙ ናቸው። ክፉዎቹ መላእክት ደግሞ በእግዚአብሔር ሥልጣን ሥር ቢሆኑም ከእግዚአብሔር ፈቃድ ያፈነገጡ፤ የተቀመጡበትን ሥፍራ ትተው የወጡ የጥፋት ኃይሎች ናቸው።
ይሁዳ 1፤6 «መኖሪያቸውንም የተዉትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል»
በቅዱሳኑ መላእክት ላይ የአለቅነት ሥልጣን ያለው ቅዱስ ሚካኤል ነው።
ራእይ12፥7 «በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፥ አልቻላቸውምም»
ዳን 12፥1 «በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል ሕዝብም ከሆነ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን ይሆናል በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል»
በክፉ መናፍስት ላይ ሥልጣን ያለው ደግሞ ሰይጣን (ተቃዋሚ)፤  እባብ (ጠላት)፤ ዲያብሎስ (ከሳሽ) የተባለው ዓለሙን ሁሉ የሚያስተው ዘንዶ ነው። ( ራእይ 12፤9 )  ከቅዱሳኑ መላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልና ከመላእክቶቹ ጋር ይኼው ዲያብሎስ  ተዋግቶ ተሸንፏል።
ስለዚህም ይህ የተሸነፈው ዲያብሎስ በዚህ ዓለም ላይ ከነሠራዊቱ አሳች ሆኖ ይገኛል። በዚህ ምድር ላይ ለሚፈጸመው ጥፋት፤ ኃጢአትና ዐመጻ ሁሉ ዋናው አስፈጻሚ ይህ ሰይጣን የተባለውና ሠራዊቱ ናቸው።

3/ የቅዱሳን መላእክት አገልግሎት

ይቀጥላል%