«ደጀ ብርሃን» ማናት?



«ብርሃን ዘበአማን ዘያበርህ ለኩሉ ዓለም»

ክርስቶስ ብቸኛው የሕይወታችን ብርሃን ነው!
መንገድ ጠራጊው መጥምቁ ዮሐንስ ስለብርሃን ኢየሱስ  አስቀድሞ አዋጅ ሲናገር «ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ» ዮሐ ፩፤፯ ሲል እንደተናገረው «ዴዴ ብርሃን» መካነ ጦማራችንም ስለብርሃን ልትመሰክር እነሆኝ ትላለች። በእርግጥ ስለእውነተኛው ብርሃን መስበክ ቀላል መንገድ አይደለም። ብዙ ብርሃናት ባሉበት ዓለምና ብዙ ብርሃናትን በሚሰብኩ ሰዎች ፊት ስለአንዱና ስለብቸኛው እውነተኛው ብርሃን መስበክና አዋጅ መናገር ዋጋ ያስከፍላል። አሁንም ዋጋ እየከፈልንበት ቢሆንም ዋጋ መክፈላችን ስለሌላ ስለማንም ሳይሆን ስለእውነተኛው ብርሃን በመናገራችን ብቻ በመሆኑ ደስ እያለን «ደጀ ብርሃን» ሆነን እንቀጥላለን።
«በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን ተናገሩ፤ በጆሮም የምትሰሙትን በሰገነት ላይ ስበኩ። ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ» ማቴ ፲፤፳፯-፳፰
ብዙዎች ስለእውነተኛው ብርሃን በመናገራቸው ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። ዛሬም እየከፈሉ ናቸው። በብርሃን ስለተናገሩና በሰገነት ላይ ስለሰበኩ ብቻ ተገርፈዋል፤ ተሰደዋል፤ ተገድለዋል። ዳሩ ግን ሥጋን እንጂ ነፍስን ማግኘት ስላልቻሉ ስለብርሃን የሚናገሩ ጽኑዓን በቁጥር እየበረከቱ እንጂ እንደስደትና መከራው መብዛት እየቀነሱ አልሄዱም። እየቀነሱም አይሄዱም። ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው፤ ፍጹም አምላክ መሆኑን ከመስበክና አዋጅ ከመናገር ወዲያ ስለሰው ልጆች በምድርም ሆነ በሰማይ የሚቀርላቸው ሌላ ስም የለምና በስሙ መከራን የሚቀበሉ አሸናፊዎች ናቸው። ስለብርሃን መመስከር የሚቻለው ከእግዚአብሔር በመወለድ የእምነት ጸጋ ስለሆነ አሸናፊው እምነታቸው ነው። «ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው» ፩ኛ ዮሐ ፭፤፬ እንዳለው።
ክርስቶስ ብቻውን የሕይወታችን ቤዛ ነው!
እምነት ማለት ደግሞ አምላክ ሰው ሆኖ መምጣቱን ማመንና በእሱ የተገኘችውን ሕይወት ብቻ መመስከር ማለት ነው። አንዳንዶች ስለብርሃን ክርስቶስ አምላክ መሆን ያምናሉ። አምላክ ሰው መሆኑንም ይቀበላሉ። ይህ በራሱ ጥሩ ነው። ነገር ግን እውነተኛ አማኝ ለመባል በቂ አይደለም። እውነተኛ እምነት፤ አካላዊ ቃል (ወልድ)፤ ሥጋ መልበሱን በማመንና እሱ ብቻ የሕይወታችን ቤዛ መሆኑን በመመስከር ይታወቃል።  የዓለም ቤዛ ኢየሱስ ብቻ ነው። «ራሱንም ለሁሉ ቤዛ ሰጠ፥ ይህም በገዛ ዘመኑ ምስክርነቱ ነበረ» ፩ኛ ጢሞ ፪፤፮  ሌሎች ተጨማሪ የዓለም ቤዛዎች እንዳሉ የሚሰብኩ ሰዎች የክርስቶስን ፍጹም አምላክነትና ፍጹም ሰው መሆን  ስለተናገሩ ብቻ ወደዱም፤ ጠሉ አማኝ ሊባሉ አይችሉም። ወንጌል እንዳለው «ራሱን ለሁሉ ቤዛ ሰጠ» ሲል «ሁሉ» በሚለው ቃል ከዚህ ቤዛ ስር  ሌላ ቤዛ እንደሌለ አስረግጦ መናገሩን ሊያምኑ ጭምር ይገባል።  በሰማይም በምድርም ሌላ ቤዛ ለክርስቲያኖች እንደሌለ ሊመሰክሩ ይገባል። በብዙ አማልክት የሚታመኑ ሰዎች ዓለማችን አሏት። ስለኃጢአተኞች ቤዛ መሆን የቻለና ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት በትንሣዔው የሰበከ ህያው እንደክርስቶስ ማንም የለም።  ድንግል ማርያም ንጽሕትና ብጽእት እናቱ በመሆኗ ብቻ «ቤዛዊተ ዓለም» የሚሏት ክርስቲያኖች ብዙ ናቸው። እሷን መውደድ አንድ ነገር ነው፤ እሷን የዓለሙ ሁሉ ቤዛ ማድረግ ደግሞ ሌላ ነገር ነው። «ነፍስየሰ ትትሐሰይ በአምላክየ ወበመድኃኒትየ» ነፍሴ በአምላኬና በመድኃኒቴ ሃሴት ታደርጋለች ያለችውን ቃል ሽሮ «ቤዛዊተ ዓለም» ማለት አግባብ አልነበረም። ቃላቸውን በሰባራ ቃላት እያስደገፉ «ቤዛዊተ ዓለም» ቢሏት ድንግል ማርያም እኔ የዓለሙ ሁሉ ቤዛ ነኝ አትልም። ሰባት ጊዜም ቢሆን ልሙት ብላለች ሲሉ ይከሷታል። ቅድስት ማርያም ሰባት ጊዜ በመሞቷ ለዓለሙ ቤዛ የሆነውን የልጇን፤ የወዳጇን የማዳን ሥፍራ አትተካም። እሷም አላለችም። አትልምም። ዳሩ ግን ጠላት ለክብሯ የቀና መስሎ በሰዎች አድሮ ያልሆነውንና ያልተባለውን እያወራ ከእውነት ቃል እንድንወጣ ይፈልጋል። ቅድስት ማርያምም የእውነት እናት ስለሆነች ለእሷ ክብር የቀኑ ከሚመስሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ሃሳውያን ጋር ኅብረት የላትም። ቅዱሳንን ማክበርና ማምለክ ለይተው ስለማያውቁ እኛም ይህንን በብርሃን ቃል ስንገልጠው ውሸታሞች ይሉናል። ጳውሎስም በአንድ ወቅት የእውነት ቃል ሲናገር ሳለ ውሸታም ይሉት ነበር። በእሱ ውሸታም መባል የእውነት ቃል በእሱ በኩል ስለእግዚአብሔር ይነገር ነበር። ነገር ግን በሰዎች ውሸታም በመባሉ እንደኃጢአተኛ የሚፈረድበት ሰው አይደለም። «በእኔ ውሸት ግን የእግዚአብሔር እውነት ለክብሩ ከላቀ ስለምን በእኔ ደግሞ እንደ ኃጢአተኛ ገና ይፈርድብኛል?» ሮሜ ፫፤፯ ሲል ይጠይቃል። ደጀ ብርሃን መካነ ጦማር ቤዛ የሆነን ሌላ ማንም እንደሌለ ስትናገር ውሸታም ስላሉ ብቻ የእግዚአብሔር ቃል ወደብርሃን ከመምጣቱ አይታገድም። እውነተኛውን ቃል  ስንገልጥ ውሸታም በመባላችን ብቻ እግዚአብሔር የሚፈርድብን ይመስላቸዋል። እኛ ግን ብርሃን ክርስቶስ ፍጹም አምላክ፤ ፍጹም ሰው እንደሆነና እሱ ብቻ በማይጠፋ ብርሃን የሚኖር ብቸኛው ቤዛችን እንደሆነ ስንመሰክር ስለመዳናችን ትልቅ ድፍረት አለን።
ብርሃን ክርስቶስ፤ አምላክ መሆኑን ለማመን ቃል አንሸቅጥም!
«ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በሚታመን ሁሉ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል» ፩ኛ ፬፤፲፭ ኢየሱስ ማን ሆነና ነው የእግዚአብሔር ልጅ የሚባለው የሚሉም አሉ። ወደ ብርሃኑ ያልመጡ ነገር ግን በብርሃኑ ያሉ የሚመስላቸው ብዙ ለጆሮ የሚከብዱ ነገሮች ያጋጥሟቸዋል። ይህንን ሁሉ እንደተሰጠን ኃይል መጠን በብርሃን ቃሉ እንገልጣለን። «የርኅራኄ አባት የመጽናናትም ሁሉ አምላክ የሆነ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ» ፪ኛ ቆሮ ፩፤፫ ይህም ቃል ኢየሱስን የሚያሳንስ አድርገው የሚያስቡ አሉ። ሲያነቡት እንጂ ሰዎች ሲያስተምሩበት ጆሮአቸውን ያሳክካቸዋል።  የኢየሱስን ፍጹም ሰው መሆን ትተው፤ የዚህን ዓለም ቅዱሳን በእሱ ቦታ በመተካት አምላክነቱን ብቻ ማንጸባረቅ የሚፈልጉት በልባቸው ከአምላክነቱ ሥፍራ ያነሰ ስለሚመስላቸው ብቻ ነው።  በአንድ በኩል ኢየሱስ አምላክ አይደለም የሚሉትን ለመከላከል በሌላ መልኩም ኢየሱስ የእርቅ መንገዳችንና የአዲስ ኪዳን መካከለኛ የሚሉትን ክፍሎች ያሸነፉ ወይም መልስ ያሳጡ መስሏቸው በቅናት ካባ ጠላትን እያገለገሉ ቃል እስከመሸቃቀጥ ድረስ ሄደዋል።

 በኢትዮጵያ ዕስራ ምእት የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ የዚያ ውጤት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይቻላል። ፊደል በማጣመም ወይም በማቃናት ቅዱሳን የክርስቶስን ሥፍራ እንደወሰዱ ለማሳመን የሚታገሉትም ለዚህ ነው። (፪ኛ ቆሮ ፭፤፳) «እንደሚማድ» የሚለውን «እንደሚማድ» በማለት ፊደል እስከማጣመም የሚሄዱት ወንጌል እንደዚያ ስለሚል አይደለም። ያንን በማድረጋቸው አምላክነቱን የጠበቁና በእሱ ሥፍራ ቅዱሳንን ያስገቡ ስለመሰላቸው እንጂ። ግእዙ «ከመ ይተንብል በእንቲአነ» በእኛ እንደሚማልድ ይላል። አራማይኩ  Աստուած կ՚աղաչէր»- አስቱዋአስ ኬግኧ’ችኤር/ በእኛ እንደሚማልድ ይላል።  ጽርዑም («παρακαλοῦντος δι' μῶν»- parakaloúntos di' i̱mó̱n ፓራካለውቶስ ዲ ኢሞኒው)  በእኛ እንደሚማልድ ይላል። እንግሊዝኛውም «did beseech you by us» በእኛ እንደሚማልድ ይላል። የሁሉም መጻሕፍት ትርጉም በአንድ ቃል እውነታውን ሲገልጡት ፊደል በማጣመም ሰዎች «ል» ን ወደ «ለ» የሚቀይሩት ለምን ይሆን?
መጽሐፍ እንዲህ ይላል። «እስመ ዘእኩይ ምግባሩ ይጸልእ ብርሃነ፤ ወኢይመጽእ ኀበ ብርሃን፤ ከመ ኢይከሰት ምግባሩ» «ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም» ዮሐ ፫፤፳
ስለዚህ «ዴዴ ብርሃን« (ደጀ ብርሃን) መካነ ጦማር በብርሃን ቃል የጨለማውን ሥራ ትገልጥ ዘንድ እነሆ መጣች።