Friday, August 31, 2012

በአሜሪካ ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ ለአቡነ ጳውሎስ የሀዘን መግለጫ አወጣ!


ቤተክርስቲያን ለሁለት የመከፈሏ ምክንያት የሥርዓት ለውጥ መከሰቱ እንደሆነ ይታወቃል። ከጊዜው ንፋስ ወዲህና ወዲያ የሚነፍሱ ወገኖች አንደኛውን ወገን የዚያ ሥርዓት ጥገኛ ሲል አንደኛውን ደግሞ የዚህ ቡድን ደጋፊ እያለ የገመድ ጉተታ ዓይነት ሃሳብ በመዘፈቁ የቤተክርስቲያን እርቅና ሰላም በሰመመን ውስጥ ሰጥሟል። አንዳንዶች ደግሞ ፓትርያርክ መርቆሬዎስ ማናቸው? የት ናቸው? በማለት ከ21 ዓመት በኋላ ጥያቄ የሚያቀርብ ጽሁፎቻቸውን በየድረ ገጾቻቸው ላይ ለጥፈዋል። ድምጽዎትን እንስማ፤ እዚህ ቦታ አለሁ በሉን! የሚለው ጥያቄ የፍቅር ከሆነ ይህንን ጥያቄ ለማቅረብ ዛሬ ምን ተገኘ? እንድልንል ያደርገናል። እንዲያውም ወደመንበራቸው ይመለሱ! የሚባሉት እርስዎ ማነዎት? የሚለው ፌዝ መሰል ጥያቄ ግልጽነትና ምክንያታዊነት የጎደለው በመሆኑ የቤተክርስቲያንን እርቅ ገና ብዙ ፈተና እንደሚጠብቀው ያመላክታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካው ሲኖዶስ በሀገር ቤቱ ሲኖዶስ ፓትርያርክ ሞት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል። ለቤተክርስቲያን አንድነትና ሰላም በጋራ እንስራ! የሚል መልእክቱንም አስተላልፏል።
ከቤተ ጳውሎስ ድረ ገጽ ላይ ያገኘነውን መረጃ አካፍለናችኋልና ከታች ያለውን ሊንክ በመጫን እንዲያነቡ ተጋብዘዋል።


( መግለጫውን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)

Wednesday, August 29, 2012

የደም ምስል ጨርቁ!


ሰልሞንና ካሌብ ሊሰልሉ ወጥተው
ከዔናቆች መንደር አጥር ከከበው፤
ኢያሪኰ ገቡ ዮርዳኖስን አልፈው።
ግዙፋን አህዛብ ጥብቅ ሆኖ በራቸው ፤
ጥንካራ የነበር መግቢያና መውጪያቸው።
                     መሹለኪያ በሌለው  መዝጊያ ገረገራ፤
                      ሰርጎ ይገባ ዘንድ ፤እስራኤል አመራ፤
                        ጸጉረ ልውጥ ሰው ቢታይ በመንደሯ
                       ከበባ ታወጀ ከዔናቆች ጭፍራ።
                         ሰልሞንና ካሌብ በነፍስ አድን ሩጫ
                          መሸሸጊያ ሲሹ ከገዳይ ማመለጫ
                           ፈጣሪ አዘጋጀ፤ የከተማ ዋሻ
                           ከዔናቅ ሰራዊት መዳኛ መሸሻ
አንድ ሴት ነበረች ዘማነቷን ፈታ
ባል አልቦ የሆነች፤ በሕይወት ከርታታ
ብለው የሚጠሯት ረዓብ ጋለሞታ።
ሰዎቹን ሸሸገች ከቤቷ ውስጥ ጓዳ፤
በተልባ እግር ሽፋን፤ አድርጋ መከዳ።

                           ገዳይ ወገኖቿ አልፈው እንደሄዱ
                          ካሌብ፤ ሰልሞንም  ውለታ እንዳይክዱ
                          ቃል ታስገባ ጀመር፤ ሀገሯን ሲንዱ።
                          ሰባ ነገሥታትን ከፊት ያደቀቀ
                          ዮርዳኖስን ከፍሎ  በየብስ ያደረቀ
                         ሕዝቡን እየመራ ለድል የጠበቀ
                        ነውና አምላካችሁ ክንዱ የታወቀ
                        ኢያሪኰን መጣል እንደሚችል አየሁ፤
                       ኃጢአት የከበዳት፤ ረዓብ እባላለሁ፤
                       እባካችሁ ያኔ፤ ታደጉኝ እኔን፤
                       አብሬ አልጥፋ፤ ምሕረት አርጉልኝ
                        ብላ ብታነባ፤ ሰባብራ ልቧን
                      ገረመው ካሌብን፤ ደነቀው ሰልሞንን
                        ከሴት አመንዝራ፤ ድንገት ማግኘቱን
                        የእስራኤልን አምላክ፤ የሚያውቅ አምላኩን

Tuesday, August 28, 2012

ሚዲያ ጥሩና ሌላ ዐቃቤ መንበር ሹሙ! ብጹእ አቡነ ናትናኤል

   ድግሷ እንዳማረላት የሴት ወይዘሮ የቤተክህነቱን ወጥ የሚወጠውጠው ማኅበረ ቅዱሳን ነገሮች ሁሉ እንዳሰበው  ሊሄዱለት እንዳልቻሉ ሁኔታዎች እያመላከቱ  ናቸው። መንፈስ ቅዱስን በስም እንጂ በእምነት የማያውቀው ማኅበር ሲኖዶሱ በመንፈስ ቅዱስ ይመራናል እያለ፤ የራሱን ዓላማና ግብ ለማስፈጸም ባሰባሰበው የሰሞኑ ሲኖዶስ ጉባዔ ላይ  ፍትጊያውና ሩጫው ያላማራቸው ዐቃቤ መንበር አቡነ ናትናኤል ፤ እኔ በስተርጅና ስምና ክብሬን አዋርጄ፤ ቤተክርስቲያንንም ለማንም መጫወቻ እንድትሆን አሳልፌ ሰጥቼ ታሪኬን አላበላሽም፤ ነገረ ሥራችሁም ደስ አላለኝም በማለት ዐቃቤ መንበርነቱን ተረከቡኝ ብለው ጉባዔውን ትተው መውጣት ከጀመሩ በኋላ በእድሜ የገፉ አባቶች ባቀረቡላቸው ልመናና ተማጽኖ ለመመለስ ችለዋል። 

ወጣቶቹ ጳጳሳት 7ቱ ኮሚቴዎች የምንመራበት የራሳችንን አዲስ ሕግ እናውጣ፤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህናትንም ለስብሰባ እንጥራ በማለት ማስቸገራቸው የተሰማ ሲሆን በብጹእ አቡነ እስጢፋኖስ በኩል ተሰጣቸው የተባለው መልስ እንደሚያስረዳው ሕግን በተመለከተ ከሲኖዶስ ሕግ ውጪ ዛሬ የምናወጣው ሕግ አይኖርም፤ አዲስ አበባ ሀ/ስብከትም  የራሱ ሊቀጳጳስ እያለው ጣልቃ በመግባት የካህናት ስብሰባ እኛ ማድረግ አንችልም በማለታቸው  የእነ አቡነ ነደ እሳት ጥያቄ ተቀባይነት ሳይኖረው ቀርቷል። በእድሜ የገፉትን እኒህን አባት ዐቃቤ መንበር ማድረግ ያስፈለገው እንዳሻን እንነዳቸዋለን፤ እየጠመዘዝን እንሰራለን ከሚል የሥጋዊ አእምሮ ስሌት የነበረ ቢሆንም ለጊዜው አቡነ ናትናኤል አይተው የማያውቁት ሩጫና ግርግር አስደንግጧቸዋል።  ደጀ ብርሃን ብሎግ  «የፓርትርያርክ የምርጫ ግርግር ለማኅበረ ቅዱሳንና ለወዳጅ ጳጳሳት ጥቅም እንዳይውል ያስፈራል!» በሚል ርእስ ያወጣችው ጽሁፍ በተግባር እየታየ መሆኑን አመላካች ነው።  በሌላ መልኩም አቡነ መልከ ጼዴቅ ከወደ አሜሪካ በአቡነ ጳውሎስ እረፍት ላይ ውግዘታቸው ሳይነሳ የሞቱ መሆናቸውን በመናገራቸው  መሳሳብ ማስከተሉ ተነግሯል። ሁለቱም ወገን መወጋገዛቸው አይካድም። የውስጥና የውጪው ሲኖዶስ የተወጋገዙት ቃል ሳይፈታ አቡነ ጳውሎስ ማረፋቸውም እውነት ነው። እንደእኛ እምነት አሁንም ቢሆን ለእርቁ መንገድ እንዲሆንና እንደተወጋገዙ ሌሎች አባቶችም በመሐል በሞት እንዳይለዩ ከሁሉም ቅድሚያ ውግዘቱን ማንሳት አለባቸው እንላለን። ወንጌሉም የሚለው ይህንኑ ነው። ሉቃ 1126 እናንተ ግን ይቅር ባትሉ በሰማያት ያለው አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።
ከዚህ አንጻር የአቡነ መልከ ጼዴቅ ተወጋግዘን በሞት ተለያየን የሚለው ቃል ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ እንጂ እንደስህተት ቃል ማስተባበያ የሚያስፈልገው አይደለም። እንደተወጋገዙ በሞት መለያየት ጥሩ ነው የሚል ይኖር ይሆን?
ለቀሪ መረጃ የዓውደ ምሕረትን ዘገባ እነሆ ብለናልና መልካም ንባብ ይሁንላችሁ።

 awdemihret.blogspot.com// awdemihret.wordpress.com)
ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የቅዱስነታቸው የቀብር ሥነ ስርዓት ከተፈጸመ በኋላ በነጋታው ሲኖዶሱ ወደ መደበኛ ሥራው ተመልሷል። ከተመለከታቸው ጉዳዩች አንዱም የእርቁ ሁኔታ ነበር። የቅዱስነታቸው የቀብር ሥነ ሥርዓት ቀን ማታ አቡነ መልከ ጼዴቅ ቅዱስነታቸው ተወግዘው ነው የሞቱት ብለው መናገራቸው የእርቁን ሀሳብ አደጋ ላይ ጥሎታል።
አርብ ዕለት በነበረው ስብሰባ የእርቁ ሀሳብ ሲነሳ በርካታ ጳጳሳት የአቡነ መልከጻዲቅን ንግግር ማዘናቸውን ገልጸዋል። በተለይም የአቡነ እስጢፋኖስ አቋም ጠንካራ እና የሁሉንም ልብ ማሸነፍ የቻለ ነበር። ብጹዕነታቸው ሲናገሩቀብቶ የሾመን ተወግዞ ሞተ ከተባለ እኛም የተወገዝን ነን ማለት ነው። ስለዚህ የምን እርቅ ነው የሚደረገው? እኛ የእርቅን ሀሳብ መነጋገር ከጀመርን ጀምሮ ከቅዱስነታቸው ጀምሮ ሁላችንም ስለ እነርሱ መወገዝ አንስተን አናውቅም። ምክንያቱም እርቅ የሚመጣው ያሉበትን አቋም ትቶ ነው እንጂ የወሰድኩት አቋም አይለወጥም ብሎ አይደለም። ስለዚህ ቅዱስነታቸው ሲያርፉ መነሳት የሌለበትን ርዕስ አቡነ መልከጻዲቅ ሰላነሱ በአደባባይ የተናገሩትን ንግግራቸውን በአደባባይ እስካላስተባበሉ ድረስ የእርቅ ሀሳብ አይኖርምበማለት በአጽንኦት ተናግረዋል። ይህንንም ሀሳብ አብዛኛዎቹ ጳጳሳት ተቀብለውታል።

Sunday, August 26, 2012

የፓርትርያርክ የምርጫ ግርግር ለማኅበረ ቅዱሳንና ለወዳጅ ጳጳሳት ጥቅም እንዳይውል ያስፈራል!


ቅዱስ ፓትርያርኩ ቢቻል ከስልጣናቸው በሆነ መንገድ ቢነሱ፤ ባይቻል እንኳን ባሉበት ተሽመድምደው መስራት የማይችሉበት ገጠመኝ ቢከሰት ብዙ የደከመው ማኅበር፤ ማኅበረ ቅዱሳን እንደነበረ ይታወቃል። በየሲኖዶስ ጉባዔያት ፓትርያርኩም ይሁኑ ጽነት የሞላባቸው ጳጳሳት የየራሳቸውን ዓላማ የማስጠበቅ ህልም ለማሳካት ሲሉ ጥቅምትና ግንቦትን በቤተክርስቲያን አካባቢ የውጥረት ወራት አድርገው እንደሚያሳልፉ የምንረሳው አይደለም። ማኅበሩም ለውጥረቱ መባባስ አንዱ ምክንያት ሆኖ ለመቆየቱ ማሳያዎቹ፤ የሲኖዶስ ነደ እሳትና ጀግና እየተባሉ በስም የሚደገፉት ጳጳሳት ብዙ ጊዜ ከአቡነ ጳውሎስ ጋር እሳትና ጭድ ሆነው በጉባዔው ላይ ውጥረት ፈጣሪዎች በመሆናቸው ነበር። ውጥረት ፈጣሪዎቹን ጳጳሳት ስንመለከት በእርግጥ ከአቡነ ጳውሎስ ጋር እሳትና ጭድ ሆነው ጥቅምትና ግንቦትን የሚያጨሱት ለቤተክርስቲያን የሚቆረቆርና የሚመሰከርላቸው ሃይማኖታዊ፤ ሞራላዊና  ክርስቲያናዊ ማንነት ስላላቸው አልነበረም።  ስለምናውቀው ማንነታቸው፤ የኅሊና ጸጸት ስላላቸው ሳይሆን፤ ይልቁንም በውጥረቱ ውስጥ ብርቱ አሳቢና የቤተክርስቲያን ታጋይ ሆነው በመታየት የራሳቸውን ስብእና ለመገንባትና የስልጣን ጫናቸውን ለማሳረፍ ሲሆን በሌላ መልኩም ማንነታቸውን እንደመጽሐፍ የሚያነባቸውን ማኅበር ዓላማዎች በማስጠበቅ ውጪያዊ ስእላቸውን ለማሳመር ብቻ እንደነበር እንረዳለን።  አሁንስ?  አሁን እንግዲህ በማኅበሩም ሆነ በውጥረት ፈጣሪ ጳጳሳት ዘንድ የሚጠሉት ፓትርያርክ ጥሩም ሰሩ መጥፎ፤ ፍርዱን ለታሪክና ለትውልድ ትተው ላይመለሱ ሄደዋል። የቀሩት እነዚህ ሁለቱ የአንድ ሳንቲም ገጾች ብቻ ናቸው።
   ማኅበሩና ውጥረት ፈጣሪ ነደ እሳት ጳጳሳት ከእንግዲህ ባዶ ቦታውን ለመሙላት ምን ማድረግ እንደሚገባቸው የእኛ ምክር የሚያስፈልጋቸው አይመስለንም። ልንናገረው የምንችለው ነገር ቢኖር  ከዚህ በፊት 7 ኰሚቴ አዋቅረው የፓትርያርኩን እጅ ለማሰር የሞከሩት እንቅስቃሴ የነበረ ቢሆንም  በፓትርያርኩ ብርቱ እርምጃ ተቀምተው የነበረውን ክፍተት ዛሬ ከሞታቸው በኋላ ያለ ከልካይና ተቃውሞ መሙላት መቻላቸውን ነው። ይህ አንድ ድል ሆኖ ሊመዘገብላቸው ይችላል። በእርግጥ የሲኖዶስን ውሳኔ የሚያስፈጽም በየሦስት ወሩ የሚመረጥ ቋሚ ሲኖዶስ አባላት እያለ ዛሬ  የ7 ኰሚቴ መኖር አስፈላጊቱ  ግልጽ አይደለም። ፓትርያርኩ በሕይወት እያሉ ያስፈለገበት ምክንያት ግን ስልጣን ለመንጠቅ ነበር። ዛሬ የሚነጠቅ ስልጣን ስለሌለ በቋሚ ሲኖዶስ ላይ ተደራቢ 7 የኮሚቴ  ሲኖዶስ መመደቡ አስፈላጊ አልነበረም። ይሁን እንጂ ይነጠቅ ዘንድ የተፈለገው ሥልጣነ ፓትርያርክ ባዶ ቢሆንም ይህንን  የሚጠብቅና የሚከላከል ኃይል ስለሚያስፈልግ እንዲቋቋም ተደርጓል። በመጪው ጊዜ ስልጣነ መንበሩንም ለመሙላት ይህ ኰሚቴ አመቻች ኃይል ሆኖ ያገለግላል ማለት ነው። ከዚያም በላይ የዚህ ኰሚቴ አስፈላጊነት በፓትርያርኩ መንበር ላይ የተፈለገውን ሰው ለመሰየም ይቻል ዘንድ ፍርሃትና ጥርጣሬን ለመከላከል ብሎም በሃይማኖታዊ ነጻነታችን ውስጥ ጣልቃ መግባት ይቁም የሚል ተዋጊ ኃይል ሆኖ የተቋቋመ ስለመሆኑም እንገምታለን።  ጣልቃ ሊገባ ይችላል ተብሎ የሚፈራው ወገን ደግሞ አንድም ከውጪው ዓለም በፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ የሚመራው ሲኖዶስ ከሕዝብና ከመንግሥት ጋር በሚያደርገው ድርድር ምክንያት ሊመለስ ይችላል የሚል ፍርሃትና ስጋት አለ። በሌላ መልኩም ሁለቱ ቡድኖች ማለትም ማኅበሩና የማኅበሩ ታማኝ የጳጳሳቱ ኰሚቴዎች ያዘጋጁት እጩ በመንግስት ጣልቃ ገብነት ወደ መንበሩ እንዳይመጣ ሊደረግ ይችላል የሚልም ፍርሃት ታሳቢ ነው።  ስለዚህ ይህንን ውጥረት በማርገብ  ዓላማቸውን ለማስጠበቅ አስቀድሞ በሚዲያ ስራ የማንቃትና፤ የማደራጀት ላይ መስራት አስፈልጓቸዋል። ከዚህ ውስጥ አንዱ ማሳያ የማኅበሩ አፈ ብሎግ ደጀ ሰላም ደጋግማ የምታወጣው ጽሁፎች ሊጠቀሱ ይችላሉ። እስኪ ለአብነት እንመልከት።
“ቤተ ክርስቲያናችን አዲስ ፓትርያርክ ከመምረጧ አስቀድሞ አሁን ከገባችበት ዝብርቅርቅ ሁናቴ ለማገገም፣ ከሐዘኗም ለመጽናናት እና አሠራሯን በሥርዓተ አበው መሠረት ለማከናወን ጊዜ ያስፈልጋታል።”
መቼም ማኅበረ ቅዱሳን በአቡነ ጳውሎስ ኅልፈት  እንደሰውኛ ሃሳብ በሞት ደስ ባይሰኝም ሀዘን ላይ ወድቆ፤ ድንኳን ጥሏል ማለት መቀለድ ይሆናል።  ጥቅምትና ግንቦት በመጣ ቁጥር ነደ እሳቶቹ  ጳጳሳት በጉባዔ ላይ ፓትርያርኩን ከማብገን ወጥተው ከሞታቸው በኋላ  በአቡነ ጳውሎስ ሞት ደረታቸውን እየደቁ ሀዘን ተቀምጠዋል ቢባልም ማሾፍ ነው። ታዲያ እነደጀ ሰላም ከሀዘናችን ለመጽናናትና ከዝብርቅርቁ ለማገገም ጊዜ ያስፈልገናል ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? አዎ ሁኔታዎችን እስክናመቻች አታስቸኩሉን የማለታቸው ነገር የሚያሳየን፤ አስቸኩለው ኮሚቴ ማዋቀራቸውና ከፓትርያርኩ ሥርዓተ ቀብር በኋላ ይደረጋል የተባለውን ዐቃቤ መንበር በማስቀመጥ ማጣደፋቸው፤ አታስቸኩሉን፤ ሁሉን እስክናመቻች የምትዘናጉበትን ጊዜ ስጡን ማለታቸው ነው። 
     ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርነው የቤተክርስቲያን አንዱ መጥፎ ገጽታ ባለፉት ዘመናት በሁለት ተከፍላ በአቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ የውጪ ሲኖዶስ መኖሯ ነው። ይህ አንድነት ሳይመጣ ኅልፈተ አቡነ ጳውሎስ መሆኑ ቢያሳዝንም አቡኑ በሕይወት እያሉ ለአንድነቱ አለመምጣት የእሳቸው ስልጣን ላይ መቆየት ምክንያት እንደሆነ ሲያሳጧቸው የኖሩት ኃይሎች ከሞታቸው በኋላ ማንነታቸው ገሃድ እየወጣ ነው። ማኅበሩና ነደ እሳቶቹ ጳጳሳት እንደቀደመው ጩኸታቸው እርቁ በአስቸኳይ ይፈጸም የሚል ድምጻቸው ጠፍቷል። እንቅፋት ናቸው የተባሉት ፓትርያርክ እንቅፋት መሆናቸው በሌለበት ሁኔታ አሁንስ ምን ይጠበቃሉ? ከጥልቁ ሀዘን ለመጽናናትና በአቡነ ጳውሎስ ሞት የተሰበረ ልባቸው እስኪያገግም ጊዜ አስፈልጓቸው ይሆን?  ነገሩ እውነትነት ባይኖረውም እንኳን እንደእውነት ብንቀበለው በሥርዓተ አበውም ይሁን በሲኖዶስ ሕግ ከቋሚ ሲኖዶስ ውጪ፤ ኰሚቴ የሚባል የሲኖዶስ አባላት ቡድን ይዋቀራል የሚል ስለሌለ ፓትርያርክ ሳይመጣ የፓትርያርኩን ስልጣን የመቀማት ስራ አስቀድሞ እየተሰራ ስለሆነ ጊዜ ያስፈልጋል የሚባለው የሀዘንና የመጽናናት ቃላት ተራ ማታለያ መሆናቸውን ተግባር ራሱ ያረጋግጣል።የራስን ፍላጎት ከግብ ለማድረስ እንጂ ቤተክርስቲያኒቱ ወደ አንድነት እንድትመጣ ወይም እምነትና ፍቅር የሚጣልበት አባት ወደ መንበር እንዲመጣ ተፈልጎ አይደለም ብለን መናገር እንችላለን። ወደፊትም ቢሆን ቤተክርስቲያንን ወደ አንድነት ለማምጣት የማይጠቅም ኰሚቴ ስልጣን ለመቀማት የተደራጀ መሆኑን ከማስመስከር በላይ አንዳችም መልካም መስራት የማይችል ነው።
ይልቁንም አፈ ብሎጉ ለዓላማው መሳካት የሚያስፈራውን ኃይል እንዲህ ሲል ይጠቁመናል።
«በአዲሱ ፓትርያርክ ምርጫ ላይ የራሳቸው “ጥቅም” እና ፍላጎት ያላቸው አካላት፣ ግለሰቦች እና ቡድኖች መኖራቸው እሙን ሲሆን ከነዚህ ሁሉ ኃይለኛው እና የረዥም ጊዜ ዕቅድ እና ሥልት ያለው ግን መንበረ መንግሥቱን የተቆናጠጠው የኢሕአዴግ አስተዳደር ነው»
እርግጥ ነው፤ በኢትዮጵያ የቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ  ቤተክርስቲያንን ያልተጠጋ አይነግስም፤ ንጉሡም ቤተክርስቲያንን ለዓላማው ስኬት ካልተጠጋ መውደቁ አይቀርም። አፄ ቴዎድሮስን ለሞት ያበቃቸው አንዱ ምክንያት ከቤተክርስቲያን መጣላታቸው እንደነበር ታሪክ ይናገራል። የሩቁን ትተን የቅርቡን ብንመለከት አፄ ኃ/ሥላሴም ቤተክርስቲያን አንድ ክንዳቸው ነበረች። ፓትርያርክነትን በማስመጣትና ለሥልጣን በማብቃትም ውስጥ ንጉሡ እጃቸው ነበረ። ደርግም ቢሆን ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ባይችል፤ ከእጁ እንዳትወጣ የሚፈልገውን በማስሾምና የማይፈልገውን በመግደል ሚና ነበረው። የኢህአዴግም ረጅም ዓላማና እቅድ እንደፖለቲካ ጫወታ ሕግ ቤተክርስቲያንን በቁጥጥር ስር ማስገባት የሚጠበቅ እንጂ እንግዳ ነገር አይደለም። መረሳት የሌለበት ነገር በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መርህ ሳትቆጣጠረው በነጻ የምትለቀው ማኅበር ወይም ድርጅት እንደሌለ ነው። ስለዚህ በየትኛውም መንገድ ሚሊዮኖች አባላት ያሏትን የረጅም ዘመን ተቋም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን በነጻ ይለቃታል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። ይልቁንም የመንግሥት እጅ በሰፊው እንዲናኝ እድል የሚከፍቱት ጳጳሳትና የቤተክርስቲያኒቱ ኃላፊዎች ራሳቸው ናቸው። ታሪክ የሚያሳየን ያንን እውነት ነው። አቡነ ቴዎፍሎስ ሲገደሉ የጳጳሳት እጅ ነበረበት፤ አቡነ ተ/ሃይማኖት ሲሾሙም ከመንግሥት ድጋፍ ነጻ አልነበሩም፤ የአቡነ መርቆሬዎስም ሹመትና ስደት የመንግሥትና የጳጳሳት የጋራ እጅ እንዳለው ይታወቃል። በአቡነ ጳውሎስም እንዲሁ!

Friday, August 24, 2012

የተወጋ ሲረሳ (ክፍል አንድ)


        የጽሁፍ ምንጭ፤ betefikir.blogspot.com
የወደደንን መውደድ፣ የጠላንን መጥላት፣ ለዋለልን መስጠት፣ ለነፈገን መንሣት፣ ላሰበልን መራራት፣ ለዘነጋን መክፋት የብዙኃኑ የሰው ልጅ የአኗኗር መመሪያ ነው፡፡ ምንም እንኳን በጸጋ ዘመን ላይ ብንገኝም ዓለም ገና ዓይን ስለ ዓይን፣ ጥርስ ስለ ጥርስ፣ እጅ ስለ እጅ ከሚለው ምላሽ አልጸዳችም፡፡ እንዲያውም በዚህ ሕግ ግልጽ ሆኖ ከሚስተዋለው ለጠሉኝ እሬት አይነት አካሄድ በበለጠና በረቀቀ መንገድ ሰዎች የልባቸውን ፈቃድ እያረኩ ነው፡፡ ለብዙ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን እሾህን በእሾህ፣ ደምን በደም የመመለስ ኑሮ ከእምነት ጋር አቻችሎ ማስኬድ አልከበዳቸውም፡፡ ክፉውም ጋር ደጉም ጋር ቋሚ ተሰላፊ የሆኑ ጥቂት ሆድ ሲብሳቸውያስቀመጥኩትን ቆንጨራ እንዳላመጣው?” በማለት የሚዝቱ ሁሉን ትተው ሳይሆን ሁሉን ለክፉ ቀን አስቀምጠው የተከተሉት አይናችን ስር ናቸው፡፡
         አብዛኞቻችን ሰው በሚለውና ክርስቲያን በሚለው መጠሪያ መካከል ያለውን ልዩነት ልብ አንለውም፡፡ ሰው ከምድራዊው ጥሪ ተካፋይ የሆንበት መንገድ ሲሆን፤ ክርስቲያን የሚለው ደግሞ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋይ የሆንበት መንገድ ነው፡፡ ሰው በመሆን ውስጥ በምድራዊ ስፍራና በሥጋዊ በረከት መርካት ሲስተዋልበት፡፡ (ማለትም በዚህ ምድር የምንሰበስበው ሁሉ ከፀሐይ በታች ሲሆን) ክርስቲያን በመሆን ውስጥ ደግሞ በሰማያዊ ስፍራና በመንፈሳዊ በረከት መባረክን እናስተውላለን (ኤፌ. 1÷3)፡፡
         ሰው በመሆን ልደት ይህንን ዓለም በሥጋና በደም አቋም ሆነን እንቀላቀላለን፡፡ ክርስቲያን በመሆን (ዳግም በመወለድ) ደግሞ የዘላለም ሕይወትን መቀላቀል ደግሞም የተዋረደው ሥጋችን የጌታን ክቡር ሰውነት መስሎ በሰማይ ከእርሱ ጋር እንነግሳለን፡፡ ስለዚህ ክርስቲያን ሁሉ ሰው መሆንን ቢጋራም ሰው ሁሉ ግን ክርስቲያን አይደለም፡፡ በዚህም ክርስቲያን መሆን ሰው ከመሆን በእጅጉ ከፍ ያለ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡
         ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፣ እንዲከስህም እጀ ጠባብህን እንዲወስድ ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፣ ማንም ሰው አንድ ምእራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ” (ማቴ. 5÷38-42)፡፡ ጌታ በዚህ ክፍል  ላይ ያስተማረው ትምህርት ሰው በሚለውና ክርስቲያን በሚለው ስያሜ መካከል ያለውን ተግባራዊ ልዩነት ግልጽ ያደርግልናል፡፡ በመጀመሪያ እግዚአብሔር ለሚያዘን ነገር ሁሉ የምንፈጽምበትን ኃይል እንደሚሰጠን መተማመን በዚህ ክፍል የተገለጸውን ትምህርት በቅንነት ለመረዳት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ቀኝ ጉንጭን በጥፊ መመታት ውስጥ ያለው ክርስትና ሳይሆን ሰው መሆን ነው፡፡
            እጀ ጠባብን ለሚወስድ ያንኑ መተው ሰው በመሆን ደረጃ የሚከናወን ተግባር እንጂ ክርስቲያን መሆንን አይጠይቅም፡፡ አንድ ምእራፍ በመሄድ ውስጥም እንዲሁ ከክርስትና ይልቅ ያለው ሰው መሆን ነው፡፡ የክርስትናው የአኗኗር ልኬት የሚጀምረው ታዲያ የቱ ጋር ነው? ካልን ሁለተኛውን ጉንጭ በመስጠት፣ መጎናጸፊያን በመጨመር፣ ሁለተኛውን ምእራፍ በመሄድ የሚል ይሆናል፡፡ ከዚህ ያነሰው ግን ማንም ሰው ከሰብአዊ ርኅራኄ በመነሣት አልያም ከሥጋ ሕግ በመነጨ ሁኔታ የሚከውነው ነው፡፡የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን?” (ማቴ. 5÷46)፡፡
         የነከሰንን ማጉረስ፣ የበደለንን መካስ፣ የተጣላንን ገፍቶ መታረቅ፣ የረገመንን ከልብ መመረቅ ተወግቶ እንደ መርሳት ነው፡፡ ጉዳቱ እያለ በደልን አለመቁጠር፣ ስቃዩ እየታየ ጥፋትን መተው፣ ጉድለቱ እየተስተዋለ ኪሳራን አለማስላት መንፈሳዊ የኑሮ ልዕልናን ይጠይቃል፡፡ ክርስትና የተወጋ ሲረሳ ነው!
         ከብሉይ ኪዳን በዳዊትና በሳኦል መካከል የነበረው የገፊና ተገፊ፣ ያሳዳጅና ተሰዳጅ፣ የጠዪና ተጠይ ታሪክ ለተነሣንበት ርእስ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ሳኦል ወደ ንግሥና የመጣበትን መንገድ የስነ መለኮት አዋቂዎች ሲያስረዱእግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር የተስማማበት ሂደት ነውይላሉ፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ሳኦል የእስራኤል ንጉስ የሆነው እንደ እግዚአብሔር ፍላጎት ሳይሆን በሕዝቡ ፍላጎት ተመርጦ በእግዚአብሔር አጽዳቂነት መሆኑ ነው፡፡
          እግዚአብሔር ሳሙኤልንእንደጠየቁ ቀባላቸውበማለት ከሕዝቡ አሳብ ጋር ተስማማ፡፡ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብቸኛው ክፍል እንደሆነ ይነገራል (1 ሳሙ. 15)፡፡ ምን ጊዜም ቢሆን እግዚአብሔር ከአሳባችን ጋር ከተስማማ ኪሳራው የሰው ነው፡፡ ወደኋላ መለስ ብለን ያለፈውን ፍላጎታችንን እና ዛሬ በዚያ ፍላጎት ላይ ያለንን አተያየት ብንመለከተው ለየቅል ነው፡፡ ያኔ እግዚአብሔር በፊቱ ካቀረብነው አሳብ ጋር ተስማምቶ ቢሆን፤ እንደጠየቅነው ሁሉን ቢሰጠን ኖሮ ዛሬ ከምናፍርበት ነገር ጋር ለመኖር  በተገደድን ነበር፡፡
          እግዚአብሔር ሲሰጥ ብቻ ሳይሆን ሲከለክል፣ ሲመልስ ብቻ ሳይሆን ዝም ሲል፣ ሲያኖር ብቻ ሳይሆን ሲገድልም አይሳሳትም፡፡ የእርሱ ጌትነት ምቾትን ብቻ ሳይሆን ጉስቁልናንም ያጠቃልላል፡፡ ክርስትና መብዛትን ብቻ ሳይሆን መዋረድን፣ መጥገብን ብቻ ሳይሆን መራብን፣ ከፍታን ብቻ ሳይሆን መጉደልንም ማወቅ ጭምር ነው (ፊል. 4÷12)፡፡ 

Thursday, August 23, 2012

የቅዱስነታቸው ቀብር በደማቅ ሁኔታ ተፈጸመ።


የጽሁፍ ምንጭ፤ ዓውደ ምሕረት

76 ዓመታቸው ያረፉት የብጹዕ ወቅዱስ / አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የአለም የአብያተክርስትያናት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዝዳንት የዓለም ሰላም አምባሳደር ስርዓተ ቀብር ዛሬ ነሐሴ 17 2004 .. ከቀኑ 730 ላይ በደማቅ ሁኔታ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡
የቅዱስነታቸው ስርዓተ ቀብር ላይ ቁጥሩ እጅግ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ የተገኘ ሲሆን ጊዚያዊ ጠቅላይ ሚኒስቴሩን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ የእህት አብያተ ክርስቲያናት አባቶች የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ የህዝብ ተወካች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አባ ዱላ ገመዳ ምክትል አፈጉባዬ / ሽታዬ ምናለ፤ አምባሳደሮች፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበትና በአክሱም ካሕናት እምቢልታ የታጀበ የቀብር ስነ ስርዓት ተደርጎላቸዋል።
አቡነ ገሪማ የህይወት ታሪካቸውን ያነበቡ ሲሆን የእህት አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች እና የመንግስት ባለስልጣናትም ንግግር አድርገዋል። ሥነ ስርዓቱ በፖሊስ ማርሽና የሰንበት ተማሪዎችም ዝማሬ የታጀበ ነበረ።
በትናንትና ዕለት የጀመረው እጅግ ደማቅ የነበረው ስነስርዓትም በዛሬው ዕለት ፍጻሜውን አግኝቷል። ትናንትና ከቅዳሴ በኋላ የቅዱስነታቸው አስከሬን በሰረገላ ሆኖ ከመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ወደ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል በርካታ ብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት የእህት አባተ ክርስታናት ተወካዮች፤ የመንግስት ባለስልጣናት የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች በሊቃውንተ ቤተክርስትያን በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በአዲስ አበባ ፖሊስ ሰራዊት ባንድ በምዕመናንና በምዕመናት በክብር ታጅቦ በደመቀ ስነስርዓት የተካሄደውን የሽኝት ስነስርዓት ተመልካችን እጅግ አስደሳች ነበረ።
ከምሽቱ 200 ጀምሮ እስከ ንጋቱ ድረስ ለሊቱን በሙሉ ጸሎተ ማህሌት ሲከናወን አድሯል ንጋት 1230 ላይ አስከሬኑ ባለፈበት በቅድስት ስላሴ ካቴድራል በብጹአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና አኅት አብያተክርስትያን ተወካዮች ባሉበት ስርዓተ ቅዳሴው ተከናውኗል ጸሎቱ እንዳበቀ የቅዱስነታቸው አስከሬን በክብር ታጅቦ ወደ አውደ ምህረት ወጥቷል በተዘጋጀለት ቦታ ላይ ለሰዓታት አርፏል፡፡
ይህን ተከትሎም ስነስርዓቱ የጀመረ ሲሆን የደመቀ የሚለው ቃል ሊገልጸው ከሚችለው በላይ ባማረ ሁኔታ የቀብሩ ስነስርዓት ተፈጽሟል።

Wednesday, August 22, 2012

የብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሥርዓተ ቀብር ሐሙስ ይፈጸማል፤ መጪው ዘመንስ ምን ይመስል ይሆን?


ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ እነሆ አንድ ሳምንት ሊሆናቸው ነው። የሚወዷቸው አዝነዋል፤ የሚጠሏቸውም ደስ ተሰኝተዋል። አንዳንዶች ቢጠሏቸውም እንኳን ሞት የጋራ ርስት መሆኑን በማመን እግዚአብሔር እረፍቱን ይሰጣቸው ዘንድ ከልባቸው ተመኝተዋል።
አብዛኛው ሕዝብ ደግሞ መጪው ዘመን ለቤተክርስቲያንም ሆነ ለሀገሪቱ ምን ይመጣ ይሆን? በሚል ሃሳብ ረጅሙን ጊዜ በማስላት ይጨነቃል። በእርግጥም ሟቾች ጥፋትም ይስሩ ልማት ላይመለሱ ሄደዋል። የነበሩበት ቦታ ትልቅ የመንፈሳዊና የሥጋዊ ሥልጣን ደረጃ በመሆኑ ቤተክርስቲያኒቱን በመንፈሳዊ አባትነት ሊመራ የሚችልን ሰው በማግኘት አንጻር ቢያሳስበን አይገርምም። በስጋዊ ሥልጣን ደረጃም እንደዚሁ በሀገር መሪነት ደረጃ የሚመጣው ሰው የነበሩ ድክመቶችን በማስተካከል፤ የታዩ ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል ስለመቻሉ ቢያሳስበን እንደዜጋ ከተገቢነቱ የወጣ አስተሳሰብ አይደለም።
 ቀና ቀናውን አስበን፤ መጪውን ጊዜ ብንፈራ ሰው ነንና ተገቢ ነው።
ይሁን እንጂ ክፉም ሆነ ጨካኝ ገዢ የሚመጣብንና የመጣብን መሪዎች ክፉ ወይም ደግ ለመሆን ስለፈለጉ ሳይሆን ለእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ተላልፎ የተሰጠ አምልኰ ስላለን መሆኑን አምነን ልንቀበል ይገባል።
እግዚአብሔር ለዳዊት በተናገረው ቃል ላይ ከወገቡ የሚወጣው ልጅ እንደሕጉ ከሄደ መልካም የሆነው ነገር ሁሉ ከፈጣሪው እንደሚሆንለት፤ ክፋትን በፈጸመ ጊዜ ደግሞ የሰው መቅጫ በትር እንደሚላክበት በመጽሐፍ ቅዱስ ተገልጾ ይገኛል።
2 ሳሙ 714
እኔም አባት እሆነዋለሁ፥ እርሱም ልጅ ይሆነኛል ክፉ ነገርም ቢያደርግ፥ ሰው በሚቀጣበት በትርና በሰው ልጆች መቀጫ እገሥጸዋለሁ
እኛ ደጎችና የእግዚአብሔር ፈቃድ ፈጻሚዎች ሆነን ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር በቅጣት ወይም በመከራ ውስጥ አይተወንም ነበር። ስለዚህ ለሆነውና ለሚሆነው ሁሉ ጥፋተኞች እኛ እንጂ ሌላ ማንም አይደለም። 
ኢዮብ 3412    
በእውነት እግዚአብሔር ክፉ አይሠራም፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ ፍርድን ጠማማ አያደርግም።
የሚያሳዝነው ነገር ኢትዮጵያውያን በማንነታችን ስንመዘን ፊታችንን ወደእግዚአብሔር ለመመለስ ፈቃደኞች ያልሆንን እልከኛ ህዝቦች መሆናችን ሲታይ መከራ የምንለው ነገር ማብቂያው ገና ረጅም ነው። ከጣዖት አምልኰ ገና አልተላቀቅንም። አምልኮቶቻችን ብዙዎች ናቸው። እግዚአብሔርን በከንፈሩ የሚያከብር በልብ ግን ከፊቱ የራቅን ሕዝቦች ነን። ከመበላላት ገና አልወጣንም። ሥልጣንን ጠልፎ ለመውሰድ ከሚደረግ የሽንገላና የተንኮል ተግባር ገና አልተላቀቅንም። ቤተክህነቱም ሆነ ቤተመንግሥቱ ለእግዚአብሔር ይገዛ ዘንድ ለፈቀደ ሕዝብ ገና ዝግጁ አይደለም።  ሁሉም ያሰፈሰፈው ለወንበሯ ነው። ሀገሪቱ በሃሳብ ነውጥ ተወጥራለች። ሰላም ነን እያልን ራሳችንን ካልሸነገልን በስተቀር አየሩ በሁከትና በሃሳብ ተበክሏል። ይህ ካልጸዳ የሀገሪቱ ችግር አላባራም ማለት ነው። አዎ መጪው ዘመን ያስፈራል። አመላችንና አኗኗራችን ገና አልተስማማም።